አረፋ እንደምን አለፈ?

0
674

በመላው ዓለም በሚገኙ የእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ድምቀት ከሚከበሩና ልዩ ስፍራ ከሚሰጣቸው ዓመታዊ ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላት መካከል አንዱ እና ዋነኛው ነው። ፆም፣ ጸሎትና መልካም ሥራን የሚያሳዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የሚከወኑበት ይህ በዓል የመታዘዝ፣ የመስዋዕት እና የእዝነት በዓል ተደርጎ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ በተለያዩ ሃይማኖታዊ እና ትውፊታዊ ክዋኔዎች በልዩ ድምቀት ተከብሮ ይውላል፤ ዒድ አል አድሐ (አረፋ) በአል።

ዘንድሮም ለ1441ኛ ጊዜ የሚከበረው የአረፋ በዓል፣ በመላው ዓለም ብሎም በአገራችን ከፍተኛ ስጋት ሆኖ የተከሰተውና ከጊዜ ወደጊዜ የስርጭት መጠኑ በከፍተኛ ፍጥነት እየጨመረ የመጣው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስጋት በሆነበት ጊዜ ላይ ነው። ከዛም በላይ ወረርሽኙን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተላለፉ መመሪያዎች ርቀትን የሚጠይቁና መሰባሰብን የሚከለክሉ ናቸው። እናም ሕዝበ ሙስሊሙ ሃይማኖታዊ በዓሉን በየቤቱ ሆኖ እንዲያከብር ተገድዷል።

እናም የዘንድሮውን የኢድ አል አድሐ (አረፋ) በዓል እንደ ከዚህቀደሙ በመሰባሰብ፣ በጋራ መስገድና ዱዓን በማድረግ ማሳለፉ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ መላው የእስልምና እምነት ተከታይ በዓሉን በቤቱ ሆኖ ሶላቱን በመስገድና ዱዓ በማድረግ አሳልፎታል።

በዓሉ እንዴት አለፈ?
የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ገና በማለዳው ያልተለመደ ጭርታ ሰፍኖባቸዋል። አውደአመት በመሆኑ እንደወትሮው ወደሥራ ለመሄድ ትራንስፖርት የሚጠብቁ፣ ለንግድ እና መሰል እንቅስቃሴዎች ወዲህ ወዲያ የሚሉ ሰዎች አይታዩም። ሱቆች ተዘግተዋል። የመንግሥትም ሆነ የግል ድርጅቶች ለኢድ አል አድሐ በዓልም ሠራተኞቻቸውን አሳርፈዋል።

ለወትሮው የኢድ አል አድሐ (አረፋ) በአል ማለዳ እንዲህ አልነበረም፣ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ከየአቅጣጫው ለኢድ ሶላት ስግደት ወደ አዲስ አበባ እስታዲየም በሚያመሩ ሕዝበ ሙስሊሞች ይሞላ ነበር። ዘንድሮ ግን ይህ ሊሆን አልቻለም።

አብዱራህማን በድሩ በአዲስ አበባ ኮልፌ ቀራኒዮ አካባቢ ነዋሪ ሲሆን በጨርቃ ጨርቅ ምርት ሥራ ላይ የተሰማራ ወጣት ነው። በኮቪድ 19 ምክንያት የዘንድሮ የአረፋ በአል አከባበር እንደቀድሞው ጊዜ የደመቀ እንደማይሆን ቀድሞ አውቆ ራሱን አሳምኗል። እናም በቤተሰቦቹ ቤት ተገኝቶ ከቤተሰቦቹ ጋር ለበአል የተዘጋጁትን መሰናዶዎች በመቋደስ በደስታ ማሳለፉን ይገልፃል።

ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው ቆይታም፣ ከዚህ ቀደም በአረፋ በዓል ከለመድከው ምን ጎደለብህ የሚል ጥያቄ ቀርቦለታል። እርሱም አለ፤ ‹‹ዘንድሮ ለየት የሚለው እንደ በፊቱ ጀመአው ተሰብስቦ ወዳጅ ቤተሰብ በጋራ ተዘያይሮ የሚያከብረው አለመሆኑ ነው። በወረርሽኙ ምክንያት በተናጥል መከበሩ፣ በተጨማሪም የኢድ ሶላት አለመኖሩ እና ሁሉም በየቤቱ መስገዱ ለየት እንዲል አድርጎታል።›› ብሏል።

እንዲሁም ወደ ኢድ ሶላት በሚኬድበት ወቅት በየቦታው ላይ ምዕመኑ የሚያደርገው ‹ተክቢራ› አለመኖሩ የበአሉን ሥነስርዓት እንዳቀዘቀዘውም አብዱራህማን ይገልፃል።

‹‹እንግዶች ለበአሉ በቤታችን ባይገኙምና ጎረቤትም ሆነ የቅርብ ሰው ባይመጣም፣ በሽታውን ለመከላከል በመሞከር ከቤተሰብ አባላት ጋር በጋራ በመሆን በጥሩ ሁኔታ አሳልፈናል።›› ብሏል። ኢድ አል አድሐ የእርድ በዓል እንደመሆኑም የተቸገሩ እና በዓሉን ለማክበር አቅም የሌላቸውን ሰዎች በማሰብ እና ከታረደው በግ ላይ የተወሰነውን በመላክ በመተሳሰብና በጥሩ መንፈስ እንዳከበረው ተናግሯል።

በጉራጌ ዞን የቸሀ ወረዳ ተወላጅ የሆነው ኑረዲን ናስር በአዲስ አበባ ወሰን ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ ላይ ተሰማርቶ በመሥራት ላይ ይገኛል። ኑረዲን ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረገው ቆይታ እንደተናገረው፣ አረፋን በአዲስ አበባ አሳልፎ የሚያውቅበትን ዓመት አያስታውስም። ይልቁንም በተወለደበት አካባቢ ሄዶ ከቤተሰቦቹ ጋር ነበር የሚያከብረው።

በዚህ የአረፋ በዓል ወቅት በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ሳቢያ ግን ወደክፍለ አገር ሄዶ ከቤተሰብ ጋር አለመገናኘቱ ከፍተኛ የሆነ ሀዘን እና ድብርትን ፈጥሮበታል። በዓሉን ለብቻው ሆኖ እንዲያከብር እንዳስገደደውም ነው የገለጸው።

‹‹ከዚህ በፊት በአረፋ በዓል ወቅት ለወላጆቼ የተለያዩ ስጦታዎችን በመያዝ ከቤተሰቦቼ ጋር በዓሉን ለማክበር ወደትውልድ መንደሬ እሄድ ነበር። በዛን ጊዜም ቤተሰብ ጋር ተገናኝቼ በትውልድ አካባቢዬ ከሚገኙ አብሮ አደግ ወዳጅ ጓደኞችና ዘመዶቼ ጋር ተሰባስበን በጋራ የምናከብረው በዓል፣ ደስ የሚል እና ልዩ ጊዜ የምናሳልፍበትም ነበር።›› ሲል ያስታውሳል።

‹‹አሁን ግን…›› ይላል ኑረዲን ‹‹አሁን ግን በዓሉን በዓል ስለሆነ ብቻ ነው አክብሬው ያሳለፍኩት። ከዚህ ቀደም ከቤተሰቤ ጋር በጋራ በመሆን እንደማሳልፈው ጊዜም ደስተኛ ሳልሆን ነው ያሳለፍኩት።››

ታድያ የአረፋ በዓል የመስጠት፣ የደግነትና የቸርነት በዓል በመሆኑ ከልግስና ግን ያጎደለ የለም። የእምነቱ ተከታዮች በየቦታው የተቸገሩና አንዳች ጥሪት የሌላቸው ወገኖችን በመርዳትና ሰደቃ በማብላት አክብረውታል።

እንደ ኑረዲን ሁሉ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደክልል እና ዞን ከተሞች በመሄድና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በዓሉን በልዩ ሁኔታ ለማክበር አስበው የነበሩ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ነበሩ። በዚሁ በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ግን የተለያዩ እንቅስቃሴዎች በመገታታቸው ለወትሮ ከዘመድና ቤተሰብ ጋር ለማክበር የሚንቀሳቀሱ የነበሩ ሰዎች፣ ለጊዜው ባሉበት እንዲያከብሩ ተደርገዋል። እንሄዳለን ካሉ ታድያ ለኹለት ሳምንታት በተዘጋጁ የአስገዳጅ ለይቶ ማቆያዎች እንደሚቆዩ ቀድሞ ተገልጾ እንደነበር ይታወሳል።

ስለዒድ አል አድሐ
ዒድ አል አድሐ ማለት በዓረብኛ ‹የመሥዋዕት በዓል› ማለት ነው። የእስልምና እምነት የታሪክ ድርሳናት እንደሚያስረዱት፣ የዒድ አል አድሐ (አረፋ) በዓል በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ ልዩ ስፍራ ከሚሰጣቸው ነቢዩ ኢብራሂም ጋር ይገናኛል። እንዲህ ሆነ፤ ከብዙ ሺሕ ዓመታት በፊት በብዙ ፆም፣ ጸሎት እና ምልጃ በስተርጅና እድሜያቸው ያገኙትን የበኩር ልጃቸው እስማኤልን በመስዋዕት እንዲያቀርቡ በፈጣሪያቸው (ሱብሀነሁ ወተአላ) ነቢዩ ኢብራሂም ታዘዙ። እርሳቸውም ለፈጣሪያቸው ትዕዛዝ በመታመን፤ ይኖሩበት ከነበረው መካ ከተማ 20 ኪሎ ሜትር ርቆ ወደሚገኘው እና አረፋ በመባል ወደሚታወቀው ተራራ ልጃቸውን ይዘው አመሩ።

በተራራው አናት ላይም በተዘጋጀው መሰዊያ ላይ ልጃቸውን በመስዋት ለማቅረብ በተዘጋጁበት ወቅት ትእዛዙን ለመፈፀም በጽናት ቆርጠው መነሳታቸውን የተመለከተው ፈጣሪያቸው እዝነትን አደረገላቸው። በልጃቸው ምትክም የበግ ሙክት መስዋዕት ተተካበትና ኹለቱም በተደረገላቸው ምህረት እየተደሰቱ እና ፈጣሪያቸውን እያመሰገኑ ወደ መካ ተመለሱ። አረፋም ያንን እለት በማስታወስ የሚከበር በዓል ነው።
ታዲያ በዚህ የበአል እለት የሚከናወነው የእርድ ሥነስርዓትም በዛን ወቅት በአረፋ ተራራ እስማኤል ለመስዋእትነት ከቀረበበት ኩነት ጋር ተያይዞ የእምነቱ ተከታዮች ለፈጣሪያቸው ያላቸውን ክብር እና ታዛዥነት ለማሳየት የሚደረግ ነው። ይህም የእርድ ሥነስርዓት ‹ኡድሒያ› የሚል ስያሜ እንዳለውም መዛግብት ያስረዳሉ።

ይህ የእርድ ሥነስርዓት የነብዩ ኢብራሂምን መስዋዕት (ሱና) ሕያው ከማድረግ በተጨማሪም የተቸገሩ እና በድህነት አረንቋ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ለመርዳት የሚከናወን ነው። ይህም የሚከናወነው ከኢድ ሶላት ሥነስርአት በኋላ ሲሆን የሐጅ ጸሎትን በሚገባ የሚያጠናቅቁ ምዕመናን በአረፋ ቀን ‹ኡድሒያ› የማድረግ ግዴታ አለባቸው።

ወደ ሐጅ ያልተጓዙና ፆም ጸሎቱን ያላከናወኑ ደግሞ በበዓሉ ዕለት በየቤታቸው አቅማቸው በፈቀደው መጠን እንስሳትን በማረድ ‹ኡድሒያ› ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። ይህም እርድ ከተከናወነ በኋላ ባለእርዱን ወይንም ‹ኡድሒያ› አድራጊው ለራሱ (ለቤተሰቦቹ)፣ ለስጦታ (ለወዳጅ ዘመዶቹ) እንዲሁም ለሰደቃ (ለችግረኛ ደሀ ወገኖቹ) ሦስት ቦታ ከፋፍሎ ይሰጣል። በዚህም በእምነቱ አስተምህሮት መሠረት እውነተኛ እና ትክክለኛው ‹ኡዱሒያ› ተደረገ ይባላል።

ኢድ አል አድሐ በዓል የሚከበረው በሂጅራ ዘመን አቆጣጠር አረፋ የሚውልበት ወር በገባ ዐስረኛው ቀን ሲሆን፣ የዙልሂጃ ወር በገባ በመጀመርያዎቹ ዐስር ቀናት የፆም እና የፀሎት ቀናት ይሆናሉ።

ይህን የፆም ጊዜ ታዲያ እንደረመዳን የፆም ጊዜ ሁሉ ግዴታ ሁሉም ምእመን እንዲፆመው ባይጠበቅም በፈጣሪ ዘንድ ግን ትልቅ እርዝቅ የሚያስገኝ መሆኑ ግን በብዙዎች ይታመንበታል። ይህም የፆም ጊዜ ሲያበቃ የዒድ አል አድሐ (አረፋ) በዓል ተብሎ በዓሉ በተለያዩ የአረፋ እርድ እና መሰል ዝግጅቶች ደምቆ መከናወን ይጀምራል። እርድ ለማከናወን አቅሙ ለሌላቸው ምዕመናን ደግሞ በዚህ እለት ሰደቃ በመስጠት በዓሉን በጋራ በደስታ እና ፍቅር ማሳለፍ እንደሚገባም በሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ በፅኑ ይታመንበታል።

በአገራችን ኢትዮጵያም ይህ የኢድ አል አድሐ (አረፋ) በአል በልዩ ድምቀት እና ሀይማኖታዊ ስርአቶች የሚከበር ሲሆን የእምነቱ ተከታዮች የበዓሉ ዕለት ማልደው በመነሳት ሰውነታቸውን በመታጠብ፣ ለበዓሉ ያዘጋጁትን ንፁህ ልብስ ለብሰውና የሚሰግዱበትን አነስተኛ የመስገጃ ምንጣፍ በመያዝ ከቤታቸው ይወጣሉ። በመንገድም በጀመዓ በጀመዓ (በኅብረት) በመሆን ተክቢራ (የውዳሴመዝሙር) እያሰሙ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሶላት ስግደት ወደሚከናወንበት ስታድየም ያቀናሉ።

ለሶላትስ ግደት በተዘጋጀው ስፍራ ሲደርሱም ወንዶች ለብቻ ሴቶች ለብቻ በመሆን የስግደት ሥነስርአቱን ያከናውናሉ።
ይህ የጀመዓ ሶላት ምንም እንኳን በኮሮና ምክንያት ለጊዜው ባይኖርና በጥንቃቄ ቢደረግም፣ በየቤቱ ግን የማይቀሩ ተግባራት አሉ። ለወትሮው ምዕመኑ ወደየቤቱ በመግባት ለዕለቱ የተዘጋጀውን የአረፋ ዕርድ ይፈጽማል። ለበዓሉ ድምቀት የተዘጋጁ እንደዳቦ፣ ቆሎ፣ ብስኩቶች፣ ፍራፍሬዎች፣ ቃሪቦና ብርዝ እንዲሁም ሌሎች ለበአሉ የሚሆኑ ግብአቶችን ሁሉ ከየማጀቱ እየወጡ ለበአሉ ታዳሚ ይቀርባሉ። ከዛም ይበላል፣ ይጠጣል። በዓሉም በሳቅ በጨዋታ ደምቆ መከናወኑን ይቀጥላል።

ኮሮና 19 እና በዓል
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በዓሉን አስመልክቶ ሁሉም ምዕመን በየቤቱ ሶላቱን እንዲሰግድ፣ እርዱንም በየቤቱ እንዲያከናውን የሚል መልእክት ማስተላለፍ የጀመረው ቀድሞ ነው። የምክር ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ሼሕ አሊ መሐመድ ሺፋ እንደተናገሩትም፣ ኮቪድ 19 እየተባባሰ እና ችግሩም እየጨመረ በመሆኑ፣ ሕዝበ ሙስሊሙ ጥንቃቄ እንዲያደርግ የሚል መልእክት አስተላልፈው ነበር።

እንዲህ ሲሉም ተናገሩ፤ ‹‹ስሜቱ በጣም ከባድ ነው። በተለይ የአረፋ በዓል ለየት ያለ እንደመሆኑ መጠን ሰዎች ወደክፍለ አገር እየሄዱ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚያከብሩት በዓል ነበር። አሁን ደግሞ በኮቪድ 19 ምክንያት ያ ነገር ስለሌለ ትንሽ ከበድ ይላል። ቢሆንም ግን ከሕይወት የሚበልጥ ምንም ነገር የለም። ሰላሙን አላህ ከሰጠን፣ ጤና ከሆንን እና አገራችን ደኅና ከሆነች ወደፊት አረፋ ይመጣል። አረፋን በድጋሚ እናገኘዋለን። የሰው ልጅን ሕይወት ግን ማግኘት አንችልም። በወረርሽኙ ምክንያት ከሞተ መልሰን ማግኘት አንችልም።›› ብለዋል።

እርሳቸውም በበኩላቸው በዓሉን በቤት ውስጥ በሚዘጋጀው ክዋኔ፣ በቤት ውስጥ ተወስነው እንዳከበሩት ነው የገለጹት። ‹‹በዓሉን በቤት ውስጥ ሳከብር ከየትኛውም ካሉኝ ምዕመናን ጓደኞቼ ጋራ አብሬ አላከበርም። ከባለቤቴ እና ልጆቼ ጋር ብቻ ሆኜ ነው ቤት ውስጥ ያከበርኩትም። ያ ካልሆነ ዝም ብለን በቤት ውስጥ ሰው የምንጠራ ከሆነ፣ ባልንጀራ የሚመጣ ከሆነ እህት ወንድም አጠቃላይ ቤተሰብ የሚሰባሰብ ከሆነ፣ ለሌላ ችግር የሚያጋልጥ መሆኑ ይታወቃል።›› ብለዋል።

ለምዕመኑ ሁሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ ሼሕ አሊ መሐመድ፣ በዓሉና ሰሞኑ የሰላም እና የአንድነት፣ የአብሮነት እንዲሆንም ተመኝተዋል። ‹‹እንዲሁም ደግሞ በአገራችን ላይ እያየነው ያለነው ልማት የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት ላይ እንደመሆኑ መጠን ሕዝበ ሙሰሊሙም ሆነ ሌላው የማኅበረሰብ ክፍል እስከዛሬ ሲያደርግ የነበረውን ነገር ሁሉ ወደፊት የበለጠ አጠናክሮ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ይሰማኛል።›› ሲሉም አበክረው አሳስበዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here