በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጥቃት ከፈጸሙት ውስጥ 5 ታጣቂዎች ተገደሉ

0
834

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጥቃት የፈጸሙ አምስት አጥቂዎች ሲገደሉ 20 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ቢሮ አስታወቀ።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ጉባ ወረዳ ጃዲያ ቀበሌ በተፈጸመ ጥቃት የ13 ዜጎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ ከጥቃቱ ጋር ተያይዞ 20 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ሲውሉ፣ አምስት ሽፍታዎች መገደላቸውን ቢሮው ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ሰኞ ሐምሌ 20/2012 ምሽት አካባቢ በ ጃዲያ ቀበሌ ከአገር ውጪና ከውስጥ ተልዕኮ የተሰጣቸው የጥፋት ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት የ13 ንጹሃን ዜጎች ሕይወት ማለፉን ተከትሎ በተደረገ ያላሰለሰ የክትትል እና የቁጥጥር ሥራ የጥፋት ቡድኖቹ ላይ እርምጃ ሊወሰድ መቻሉን የቢሮው ኃላፊ መለስ በየነ ገልፀዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የጥፋት ቡድኖቹ ይጠቀሙባቸው የነበሩ 12 ክላሽ እና አንድ መትረየስ የጦር መሣሪያዎች የተያዙ ሲሆን፣ የክልሉ የጸጥታ ኃይል ከመከላከያ ሠራዊትና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን ቀደም ብሎ በአካባቢው ሰላምን ለማረጋገጥ እርምጃ ሲወሰድ መቆየቱን፣ በቀጣይም የማጣራት እና ወንጀለኞቹን ለሕግ የማቅረብ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግሯል።

‹‹ይሄ ጉዳይ የአሁን አይደለም። ለረጅም ጊዜ ታቅዶበት የተለያዩ የውስጥም የውጪም አካላት በሥልጠናም ጭምር የታገዘ ነው›› ያሉት መለስ፣ ከዚህ በፊትም የመጀመሪያ ተልእኮ ያደረጉት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እቅድን ለማስተጓጎል ነበር። የጥፋት ድርጊቱንም የጀመሩት እዛው የክልሉ ተወላጅ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን እና ትላልቅ ሰዎችን በማፈን እና ጫካ ውስጥ በመውሰድም ጭምር ነው ብለዋል።

የመግረፍ እና ሰብአዊ መብታቸውን የመጣስ ሁኔታዎች እንደነበሩም አስታውቀዋል። ያን ተከትሎም መደበኛ ፖሊስ፣ የክልሉ ልዩ ኃይል፣ ከመከላከያ ሠራዊትና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በጋራ በመሆን ቀደም ብሎ ይሄንን የጥፋት ኃይልና ቡድን በማጥፋት እና በመደምሰስ በአካባቢው ሰላምን ለማረጋገጥ ከፍተኛ እርምጃዎች ሲወሰድ መቆየቱንም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደምም በተለያዩ ጊዜያት ወንበራ ወረዳ ላይ ተመሳሳይ ትንኮሳዎችን ጀምረው የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ከጥፋት ኃይሉ ጋር ባደረገው ፍልሚያ የፀጥታ መዋቅሩ ላይም ሆነ የጥፋት ቡድኑ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ኃላፊው አስታውሰዋል። በዚህ መሀል ይሄ የጥፋት ሐሳባቸው ሲከሽፍባቸው እና ኃይላቸው እየተመናመነ በመምጣቱ ምክንያት እነዚህ ከክትትል ሥራ የተረፉ ኃይሎች ባልታሰበ ሁኔታ ንፁሀን ዜጎች ላይ ይሄን ጥቃት ሊፈፅሙ መቻላቸውንም ገልፀዋል።

የክልሉ መንግሥትም አሁን የጀመረውን የማጥራት ሥራ ከመቼውም ጊዜ በላይ ትኩረት ሰጥቶ እርምጃ ለመውሰድና እነዚህን ሽፍቶች አድኖ ለሕዝብና ለመንግሥት ማቅረብ እንዳለበት አቅዶ በመሥራት ላይ ይገኛል ሲሉም አብራርተዋል።

መለሰ ጨምረውም አሁን ባለበት ሁኔታ የክልሉ ሰላም ግንባታ ቢሮ ኃላፊን፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጨምሮ እንደዚሁም ሌሎች ከፍተኛ የዞንና የክልል አመራሮች በቦታው ተገኝተው ማኅበረሰቡን የማረጋጋትና ወደ ቀደመው መደበኛ ሥራው እንዲገባ ለማድረግ ጥረቶች እየተደረጉ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከተያዙ ሰዎች ውስጥ የቁጥጥር ሥራ ሲደረግ እጅ የሰጡም አሉ። በተጨማሪም ተልእኮ ያላቸው እና ይሄን የጥፋት ቡድን በዋናነት በመምራት የሚያሰማሩ ኃይሎችም ላይ በሕግ የማጣራት ሥራዎችን ታሳቢ በማድረግ በጥርጣሬ እየተያዙ ነው። እነዚህ ተጠርጣሪዎች የተያዙት ጥፋቱን በማስተባበርም ሆነ አብረው በመሳተፍም ወንጀል ሊሆን ይችላል። እሱን የምርመራ ውጤቱ ይፋ ሲደረግ የምናየው እና ለሁሉም የምናሳውቅ ይሆናል ሲሉም ኃላፊው ገልፀዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here