በርካታ የፖሊስ ኮሚሽኑ አባላት በኮቪድ 19 መያዛቸው ተሰማ

0
455

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ባልደረባ የሆኑ የፖሊስ አባላት በኮቪድ 19 መያዛቸውን የአዲስ ማለዳ ምንጮች አስታወቁ።
በኮቪድ 19 የተያዙት አባላት ለጊዜው ቁጥራቸው ባይታወቅም በርካታ እንደሆኑ አዲስ ማለዳ በኮሚሽኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ በሥራ አጋጣሚ በተገኘችበት ወቅት ከፖሊስ አባላት አንደበት ሰምታለች።

የፖሊስ አባላት በኮቪድ 19 የመያዝ እድላቸውና ተጋላጭነታቸው ከሚሠሩት ሥራ አንፃር ከፍተኛ መሆኑን የጠቆሙት በኮሚሽኑ የአዲስ ማለዳ ምንጮች፣ በአሁኑ ጊዜ በኮቪድ-19 የተጠቁ የፖሊስ አባላት በኮሚሽኑ የመዝገብ ቤት አካባቢ ያሉ አባላት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በመሆኑም የመዝገብ ቤት ክፍል ለጊዜው የታሸገ ሲሆን፣ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ከመዝገብ ቤት ፋይሎች ጋር ንክኪ ስላላቸው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት እንደሆነም ተመላክቷል። በጊዜዊነት ታሽጓል የተባለው የኮሚሽኑ መዝገብ ክፍል የፀረ ተዋሕስያን ኬሚካል እርጭት ተደርጎለት ላልተውሰነ ጊዜ ከሰዎች ንክኪ ነፃ እንዲሆን መደረጉንም አዲስ ማለዳ ከምንጮቿ አረጋግጣለች።

አባላቱ በኮቪድ-19 መያዛቸው የታወቀው ከአንድ ሳምንት በፊት መሆኑንም እነዚሁ ምንጮች አረጋግጠዋል። አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ የአባላቱን በኮቪድ 19 የመያዝ ሁኔታ በተመለከተ ባገኘችው መረጃ፣ አባላቱ ወደ ለይቶ ማቆያ እየተወሰዱ መሆኑ ከኮሚሽኑ የፖሊስ አባላት አንደበት ሰምታለች።

የኮሚሽኑ መዝገብ ቤት ለጊዜው አዲስ ገቢ መዝገቦችን በዚሁ ምክንያት መቀበል ማቆሙንና አዲስ መዝገብ ተቀባይና ነባር መዝገብ አስተናጋጅ አባላት አዲስ መዝገብ እንዳንቀበል ኮሚሽኑ አዞናል በማለት አዲስ ገቢ መዝገቦችን ሲመልሱ አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ ታዝባለች።

በሰዓቱም ‹ለምን ይሄ ይሆናል?› በማለት አዲስ መዝገብ አስገቢ ባለጉዳዮች ጉዳያቸውን ይዘው ወደ ኮሚሽኑ ልዩ ጽሕፈት ቤት በማምራራት መዝገባቸውን በልዩ ሁኔታ እያስገቡ እንዳሉ ተመልክታለች። ነገር ግን ወደ ኮሚሽኑ ልዩ ጽሕፈት ቤት አምርተውም ‹አንቀበልም ከተባለ ተባለ ነው› ተብለው የተመለሱ ባለጉዳዮችም እንዳሉ አዲስ ማለዳ አስተውላለች።

ለምን ይሄ ይሆናል ብለው መብታቸወን ለማስከበር የጠየቁ ባለጉዳዮች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ መዝገብ ቤቱን በመዝጋቱ ልዩ መዝገብ መቀበያ አዘጋጅቶ እየተቀበለ መሆኑን እንደተገለጸላቸው ጠቁመዋል። በአጠቃላይ የአባላትን ተጋላጭነት ለመቀነስ መዝገብ ቤት አካባቢ ንክኪ ላለማድረግ እና ጥንቃቄ መደረግ ስላለበት የተወሰደ አማራጭ መሆኑ ተመላክቷል።

በአዲስ አበባ በሥራ ላይ የሚንቀሳቀሱ የፖሊስ አባላት ሥራቸውን በሚከውኑበት ጊዜ በጤና ባለሙያ ከሚመከሩት ጥንቃቄዎች ውስጥ የኮቪድ 19 መከላከያ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል (ፌስ ማስክ) በአግባቡ እንደማይጠቀሙ አዲስ ማለዳ ታዝባለች። አንዳንድ የፖሊስ አባላት ሕግ ለማስከበርና ሕዝብን የአፍ መሸፈኛ ጭንብል እንዲያደርግ ለማድረግና ለመቆጣጠር ሲሠሩ እንኳን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብሉን በከፊል አድርገው ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ።

በኢትዮጵያ የቫይረሱ ስርጭት ከእለት እለት እየጨመረ ሲሆን፣ በአጠቃላይ እስከ ሐምሌ 23/2012 ድረስ ከ16 ሺሕ በላይ ሰዎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል። ከ260 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። እንደ አገር በኮቪድ-19 ከተጠቁት ውስጥ ከ10 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ተጠቂዎች ከአዲስ አበባ መሆናቸው ደግሞ ይበልጥ በአዲስ አበባ ያለውን የቫይረሱን ስርጭት አስጊ ያደርገዋል።

ነገር ግን በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚስተዋለው መዘናጋት በኢትዮጵያ ኮቪድ-19 የተከሰተ እስከማይመስል ድረስ ከዕለት ዕለት እየተጋነነ መጥቷል። ጤና ሚኒስቴር በኅብረተሰቡ ዘንድ እየተስተዋለ ያለው የተጋነነ መዘናጋት ወደፊት ከፍተኛ ችግር እንዳይፈጥር ስጋቱን በመግለጽ ጥንቃቄዎች መዘንጋት እንደሌለባቸው በተደጋጋሚ ተገልጿል።

ቅጽ 2 ቁጥር 91 ሐምሌ 25 2012

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here