አስቀጣሪ ኤጀንሲዎች ከቀጣሪዎች ከሚያገኙት ክፍያ 75 በመቶ ለተቀጣሪዎች እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ረቂቅ ተዘጋጀ

0
548

ኤጀንሲዎች ከሦስተኛ ወገን ጋር ስምምነት በመፈፀም ከሚያገኙት ኮሚሽን አስተዳደራዊ ወጪውን ሸፍኖ ከሚቀረው ገቢ ላይ 75 በመቶውን ለሰራተኛው እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ረቂቅ መመሪያ በሰራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳዮች ሚንስቴር ተዘጋጀ።
የግል ሥራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በአገር ውስጥ የሥራ ስምሪት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ በተዘጋጀ የዳሰሳ ጥናት ላይ እንደተገለጸው በጥናቱ ከተጠቃለሉት ሰራተኞች መካከል 61 በመቶ የሚሆኑት መብታቸው እንደሚጣስና በስራው ላይ ሊያገኟቸው የሚገቡ ጥቅማጥቅሞች እንደማይከበሩላቸው ተጠቁሟል። በተለይ በጥናቱ ተለይተው ከተቀመጡት ችግሮች መካከልም በተመሳሳይ ሥራ መደብ በኤጀንሲ በሚቀጠሩ እና በቋሚነት በመስሪያ ቤቱ በሚቀጠሩ ሰራተኞች መሃል የለው የደሞዝ እና የጥቅማጥቅም ልዩነት መኖር ተነስቷል።
በተጨማሪም የሕግ ማዕቀፍ እና መመሪያዎች ሳይዘጋጁ ወደ ተግባር መገባቱና ከተገባም በኋላ የአገር ውስጥ የግል ሥራና ሰራተኛ ስምሪት ላይ ግልፅ የሆነ ሕግ ካለመኖሩ የተነሳ ኤጀንሲዎች ትርፋቸውን ብቻ በማሰብ ላስቀጠሯቸው ሰራተኞች ጥቅም እንዳይቆሙ ሆንዋል እንዲሁም ሕጉ ትኩረት የሚያደርገው በውጭ አገራት የስራ ስምሪት ላይ በመሆኑ የተነሳ ብዙ ክፍተቶች እንዳለበት በጥናቱ ተጠቅሷል።
ያሉትን ክፍቶች ለመሙላት አዲስ የተዘጋጀው የግል ሥራና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችን የሚቆጣጠር ረቂቅ መመሪያ በኤጀንሲዎች ለሚቀጠሩ መብታቸውን ማስጠበቅ ያስችላልም ተብሏል። ለውይይት የቀረበው ረቂቅ መመሪያ፤ ማንኛውም ኤጀንሲ ለሰራተኛው መብት ዋስትና ማስከበርያ የሚውል ገንዘብ፤ ይህም እስከ 100 ለሚደርሱ ሰራተኞች 30 ሺህ ብር፣ ከ101 እስከ 500 ለሚደርሱ ሰራተኞች 40 ሺህ ብር እና ከ500 በላይ ለሚደርሱ ሰራተኞች ደግሞ 50 ሺህ ብር በባንክ በዝግ ሂሳብ እንዲያስቀምጥ የሚያስገድድ ሲሆን በተጨማሪም የሕይወትና የአካል ጉዳት ኢንሹራንስ እንዲገባ ግዴታዎችን ያስቀምጣል።
በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት እንዳሻው ፈቀደ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ለሰራተኛው ሊከፈል ከሚገባው ከግማሽ በመቶ በላይ የሚሆነውን ኤጀንሲዎቹ ራሳቸው ስለሚወስዱ ሰራተኛው ተጎጂ እንጂ ተጠቃሚ አይደለም ብለዋል። ሌሎች የስብሰባው ተሳታፊዎች እንደገለጹት ረቂቅ መመሪያው ከዚህ በፊት ሕጉ ድፍን ያለ ስለሆነ ለአተገባበር አመቺ አለነበረም ፤ በዚህ ረገድ ጥናቱ ያሉትን ክፍተቶች በደንብ የለየ ነው ሲሉ ተናግረዋል።
ረቂቅ መመሪያው ከዚህ በፊት ክፍተት የሚታይበትን የኤጀንሲዎች ፍቃድ አሰጣጥ እና ክትትል እንዲሁም ፍቃድ ለማግኘት ማሟላት ስለሚጠበቅባቸው መስፈርቶች ያካተተ ሲሆን ማንኛውም ኤጀንሲ ሆኖ መሥራት የሚፈልግ ወገን አግባብነት ካለው አካል ፍቃድ ማውጣት ይኖርበታል።
ኤጀንሲው ከአንድ ክልል በላይ መስራት ቢፈልግ መሥራት በፈለገበት በእያንዳዱ ክልል ፍቃድ ማውጣት የሚጠበቅበት ሲሆን ፍቃድ ባገኘበት ክልል ተጨማሪ ቢሮ መክፈት ቢፈልግ ጥያቄውን አቅርቦ ፍቃድ ሊያገኝ እንደሚገባም ረቂቅ መመሪያው አካቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here