የሕግ ልዕልና ይከበር!

0
485

በኢትዮጵያ ምድር አዲስ የለውጥ ንፋስ መንፈስ ከጀመረበትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንበረ ሥልጣኑን ከጨበጡበት መጋቢት 24/2010 ጀምሮ በኢትዮጵያ ብዝኃነትን ለማስተናገድ፣ የዴሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋትና ዴሞክራሲን በተግባር ለማዋል በመንግሥት በኩል በርካታ አበረታች እርምጃዎች ተወስደዋል። ይሁንና ግልጽነትን ለማዳበር እና የሕግ የበላይነትን ለማስጠበቅ የሚፈለገውን ያህል እርምጃ አልተሄደም።
ከተወሰዱት በጎ እርምጃዎች አንዱ በፖለቲካ ርዕዮት ልዩነታችን ምክንያት ሠላማዊው የመታገያ መሥመር “ተዘግቷል” በሚል ነፍጥ አንስተው የነበሩ የፖለቲካ ድርጅቶች በሙሉ ወደ አገራቸው ተመልሰው በሰላማዊ ትግል እንዲሳተፉ በመንግሥት ጥሪ መደረጉ ተጠቃሽ ነው። በተለይ አርበኞች ግንቦት 7 ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ንቅናቄ፣ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ)፣ የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) በመንግሥት ተጥሎባቸው የነበረው የሽብርተኝነት ፍረጃ በይፋ እንዲነሳ ተደርጎ ወደ አገራቸው ተመልሰው ለውጡን እንዲደግፉ፣ ትግላቸውንም በሠላማዊ መንገድ እንዲቀጥሉ ከመንግሥት ጋር በመሥማማት አገር ቤት እንዲገቡ ተደርጓል።
ይሁንና በመንግሥትና በእነዚህ ኃይሎች መካከል ምን ዓይነት ሥምምነት ላይ እንደተደረሰ በዝርዝር የታወቀ ነገር የለም። መንግሥት ግልጽነትን አንደ ግዴታው አድርጎ አለመመልከቱ ዜጎችን ለጥርጣሬ ከመዳረጉም በላይ፣ ቃል ከተገባው የለውጥ እመርታ አንፃር መንግሥትን ነጥብ እንዲጥል አድርጎታል ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከቅርብ ጊዚያት ወዲህ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትን በሚያስተዳረው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና ኦነግ መካከል ውስጥ ውስጡን ሲብላላ የነበረው የእርስ በርስ መወነጃጀል ወደ ቃላት መወራወርና ከዚህም ከፍ ብሎ ወደ ‘ኃይል መውሰድ’ እና ‘መከላከል’ ደረጃ በማምራት ላይ መሆኑን ከድርጅቶቹ መግለጫዎች መረዳት ችለናል።
ከዚህ በፊት በይፋ እንደታወጀው፣ ከጥቂት ወራት በፊት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) እና በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ለማ መገርሳ የሚመራ ልዑክ ወደ ኤርትራ ተጉዞ ከኦነግ ጋር ሥምምነት ማድረጉ ይታወሳል። በወቅቱ የተደረጉ ሥምምነቶች ዝርዝር በግልጽ ለሕዝብ ይፋ መደረግ ነበረበት፤ ነገር ግን አልተደረገም። አሁንም ነፍስ እየነጠቁ ያሉ ግጭቶች በክልሉ ውስጥ ሲከሰቱ እና በኹለቱ ድርጅቶች እሰጥ አገባ ሲጀመር እውነተኛ መንስዔው በግልጽ አልተነገረም። ይህ ዓይነቱ በታፈነና በተድበሰበሰ ሥምምነት እና ድርድር አገር የመምራት አካሄድ አደገኛ ነው በሚል ግልጽነት ከመንግሥት ኃላፊነቶች እና ግዴታዎች አንዱ መሆኑን አዲስ ማለዳ ማስታወስ ትፈልጋለች። ይህ ዝግ አሠራር እና የችግር አፈታት ዘዴ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል ያለውን መተማመን እንዳይሸረሽረው ስጋቷንም ትገልጻለች።
“በሁለት ዝሆኖች ጠብ የሚጎዳው ሳሩ ነው” እንደሚባለው በኦዴፓም ሆነ በኦነግ መካከል የሚደረገው የኃይል መለካካትም ይሁን እሰጥ አገባ ዞሮ ዞሮ ሕዝቡን ለእንግልት፣ ለአካል ጉዳት፣ ሞት እና መፈናቀል ሲዳርግ ኢትዮጵያንም ወደ መልሶ አለመረጋጋት አዙሪት ሊወስዳት ይችላል፡፡
ችግሩ ግን የግልጽነት የሆነውን ያህል የሕግ የበላይነትም አለመከበር ነው!
የኦነግ ሊቀ መንበር ዳውድ ኢብሳ በተለያዩ መግለጫዎቻቸው እንዳመለከቱት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሠራዊት ‘ወደ መከላከል’ ገብቷል። ይህ የሚያመለክተው ሁለት የታጠቁ ኃይሎች መኖራቸውን ነው፤ የመንግሥት እና የኦነግ ሠራዊት። ይህ በአንዲት ሉዓላዊት አገር ፈፅሞ ተቀባይነት የሌለው ነገር ነው። ከሊቀመንበሩ ንግግር ውጪም በተለይ በምዕራብ ወለጋ አካባቢ ከኦነግ አመራር ቁጥጥር ውጪ የሆነ የታጠቀ ኃይል መኖሩን አዲስ ማለዳ የደረሳት መረጃ ያመላክታል። ጉዳዩ በኦነግ ዕውቅናም ሆነ ከዕውቅናው ውጪ፣ እንዲሁም በኦነግ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ሥምምነት ሆነም አልሆነም ሠራዊት ሊኖረው የሚችለው አገርን የሚመራ መንግሥት ብቻ ነው። ግልጽነት በጎደለው የመንግሥት እና የኦነግ ሥምምነት ኦነግ ከነትጥቁ ይንቀሳቀስ የሚል ሥምምነት ይኖራል ብላ አዲስ ማለዳ አታምንም፤ ነገር ግን እንደዚያ ዓይነት ሥምምነት እንኳን ቢኖር ሕጋዊ ተቀባይነት ስለማይኖረው ሥምምነቱ ዋጋ ሊኖረው አይገባም።
በሌላ በኩል የኦነግ አመራር የኢትዮጵያ ሠራዊት ለኢሕአዴግ ወገንተኛ ስለሆነ ለእኔም ሠራዊት ያስፈልገኛል የሚል ትርክት እንደሚያራምድ ይታወቃል። ይሁን እንጂ፣ ጋዜጣችን ስህተትን በስህተት ማረም አግባብ ነው ብላ አታምንም። ሠራዊቱ የገለልተኝነት ችግር ካለበት በበቂ ሥልጠና እና መልሶ በማዋቀር ገለልተኝነቱን፣ ሕዝባዊ እና ሕገ መንግሥታዊ ተቆርቋሪነቱን ብቻ እንዲያረጋግጥ ማድረግ እንጂ ለጦርነት በሚጋብዝ መልኩ ሌላ ሠራዊት ከጎኑ ማኖር በየትኛውም የሕግ፣ የሞራል፣ ወይም የፖለቲካ ፍልስፍና ተቀባይነት የለውም። በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያ ለአገር ዐቀፍ ምርጫ እየተዘጋጀች ባለችበት በዚህ ጊዜ ይህ ጉዳይ አስቸኳይ መፍትሔ ካላገኘ ወደ ግጭት እና ቀውስ ውስጥ ለመግባት ሰበብ መሆኑ አይቀሬ በመሆኑ ከወዲሁ ይታሰብበት።

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here