የመሬት ወረራ ፈፅማችኋል በሚል ቤታቸው በላያቸው ላይ በመፍረሱ ሜዳ ላይ መውደቃቸውን በሰበታ ከተማ አስተዳደር የወለቴ አካባቢ ነዋሪዎች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በፈረሰው መኖሪያ ቤታቸው ከ15 ዓመት በላይ እንደኖሩ የሚናገሩት ተፈናቃዮች የዓየር ላይ ካርታ ያላችው ሰዎች ቤታቸው አይፈርስም ቢባልም ቤታቸው ፈርሶ እንዲፈናቀሉ መደረጉን በመጥቀስ የከተማ መስተዳድሩን ይወቅሳሉ።
በተጨማሪም ‹‹አግባብነት በሌለው መልኩ አፍራሽ ግብረ ኃይሉ በሌሊት በመምጣት ንብረታችንን መከላከል በማንችልበት ሁኔታ ነው እንድንፈናቀል ያደረገው›› ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታቸውን አሰምተዋል።
ከእነሱም ባለፈ ሁኔታውን ለመዘገብ በቦታው በተገኙ ጋዜጠኞች ላይም እንግልት ደርሶባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅትም 405 አባ ወራዎች መጠጊያ አጥተው በከፋ ችግር ውስጥ እንዳሉና በአቅራቢያው በሚገኘው ቅዱስ ፋኑኤል ቤተክርስቲያን ተጠልለው እንደሚኙ አመልክተዋል።’
በጉዳዩ ላይ ለአዲስ ማለዳ ምላሽ የሰጡት የሰበታ ከተማ ከንቲባ ለገሰ ነጋዋ ‹‹በምንም ዓይነት መስፈርት ሕገ ወጥነትን አንደግፍም›› ብለዋል። ‹‹ተፈናቅለናል በሚል ቅሬታቸውን ለሚያሰሙትም አካላት ቢሆን ከዚህ ቀደም በሕጉ መሠረት ማስታወቅያ ለጥፈንና ማስጠንቀቅያ ሰጥተን ነው የማፍረስ ሥራውን የጀመርነው›› ሲሉም አክለዋል። የነዋሪዎቹን በአካባቢው የመኖር ጊዜ ቆይታም በተመለከተ የተጠቀሰው 15 ዓመት ሐሰት ነው ያሉት ከንቲባው ከ2005 በፊት የተገነቡ ቤቶች በአካባቢው እንደሌሉ ተናግረዋል።
ሁኔታውን ለመዘገብ ቦታው ላይ የነበረችው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ባልደረባ ሃምራዊት ብርሃኑ ለአዲስ ማለዳ እንዳለችው ጋዜጠኞቹን ማዋከቡ ሆን ተብሎ የተከናወነ እንዳልሆነና እነርሱ ለመዘገብ የደረሱበት ሰዓት በተነሺዎቹ እና በፀጥታ ኃይሉ መካከል አለመግባባት በተፈጠረበት ግዜ በመሆኑ ነው። በጋዜጠኞች ላይ ለተፈጠረው መዋከብ እና ግርግርም የሰበታ ከተማ ከንቲባ በስልክ ይቅርታ እንደጠየቋት ተናግራለች።
ከተፈናቃዮቹ መካከል አንዱ የሆነው ኢሳህ ‹‹ከዚህ በፊት እዚያ ቦታ ላይ መሬት ገዝተን ስንሰፍር ማስቆም ይቻል ነበር፤ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ እኛ አካባቢውን እያለማን ጥርጊያ መንገድ በመሥራታችን ጭምር ላበረከትነው መልካም ተግባር የልማት አርበኛ በማለት ሰርተፍኬት እያበረከተና እውቅና እየሰጠን ዛሬ ላይ ደርሶ የመሬት ወረራ ፈፅማችሁ እንጂ ሕጋዊ አይደላችሁም ማለት ትክክል አይደለም›› ሲል ቅሬታውን ይገልጻል። የቤት ፈረሳው ቀድሞውኑ በትውውቅ እንደተፈጸመና የሚታወቁ ሰዎች ቤት እንደታለፈ የሚገልጹ ባለ ቅሬታዎችም አሉ።
ማንም ሰው አካባቢውን ያለማል የሚሉት ከንቲባው በበኩላቸው እንደ ከተማ ግን ቤቶቹ በተገነቡበት አካባቢ ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት እንዳልተገነባ ያክላሉ። አካባቢው ለመኖሪያ የማያመች ከመሆኑም በላይ ቤቶቹን ለማፍረስም በራሱ ብዙ አፍራሽ ግብረ ኃይል አስፈልጎ እንደነበር ይጠቅሳሉ። ቤቶቹን ማፍረስ የተጀመረው ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት በኋላ እንደሆነ የሚናገሩት የሰበታ ከንቲባ የፈረሰብን በሌሊት ነው የሚለውን ቅሬታ እንደማይስማሙበትም ይገልጻሉ።
አዲስ ማለዳ በቦታው ተገኝታ እንደታዘበችው በአካባቢው የነበሩ አብዛኛዎቹ ቤቶች የፈረሱ ቢሆንም የቀሩ ሦስት አካባቢ ቤቶች አሉ። ስለቀሩት ቤቶች ጉዳይ የተጠየቁት ከንቲባው፤ ‹‹በወረራ የተያዙ ቤቶችን ማፍረስ ገና መጀራችን እንጂ አልጨረስንም ብለው የዓየር ላይ ካርታውን በማየት ግን ለጊዜው ያልፈረሱ ጥቂት ቤቶች መኖራቸውን›› ተናግረዋል። የአካባቢውን ነዋሪዎች ስብሰባ ጠርተው በተደጋጋሚ የሰፈሩት በወረራ እንደሆነ እና አፍራሽ ግብረ ኃይል መጥቶ ከማፍረሱ በፊት አስቀድመው ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቅያ ሲስጡ እንደነበርም ከንቲባው ያነሳ።
የከተማ አስተዳደሩ የመሬት ወረራውን ለፈፀሙ አካላት ምንም የሚያደርገው ነገር እንደሌለ የገለጹት ለገሰ ‹‹ምን አልባት የአካባቢው ተወላጅ ሆነው በዚህ ድርጊት ውስጥ የተሳተፉ ካሉ ጉዳያቸውን በአግባቡ አይተን መፍትሔ የምንሰጥበት ሁኔታ ይኖራል›› ብለዋል። ‹‹ከሌላ አካባቢ በመምጣት የመሬት ወረራ ለፈፀሙት ግን ምንም የምናደርገው ነገር አይኖርም›› ሲሉም ተናግረዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011