ኮርፖሬሽኑ ታሪፍ ባለመኖሩ 947 ሚሊየን ብር መሰብሰብ አልቻለም

0
703

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ታሪፍ ባለመውጣቱ ምክንያት ከስኳር ኮርፖሬሽን 947 ሚሊየን ብር አለመሰብሰቡ ታወቀ።
በስኳር ኮርፖሬሽን ሥር ለሚገኙ ፋብሪካዎች ግብዓት ይሆን ዘንድ የመስኖ ውሃ የሚያቀርበው ኮርፖሬሽኑ፤ ለባለፉት ዓመታት በቢሊየን ብሮች የሚያወጡ መስኖዎችን ቢገነባም ታሪፍን በሚመለከተው ባለማውጣቱ የተሰጠውን ተልዕኮ መወጣት አለመቻሉን ለአዲስ ማለዳ በሰጠው መግለጫ አስታወቀ።
ኮርፖሬሽኑ በተንዳሆ፣ ቀሰም፣ ወለንጪት፣ ኩራዝ እንዲሁም የስኳር እና ጣና በለስ መስኖዎችን በመጠቀም ለስኳር ኮርፖሬሽን ውሃ ቢያቀርብም አገልግሎት የሰጠበትን ክፍያ ባለማግኘታችን ሥራዎቻችንን ላይ ክፍተት እየታየበት ስሆን ክፍተቱም በመንገድና በውሃ መሠረተ ልማት በኩል በብዛት ይታያል። በመሆኑም ትልቅ አገራዊ ፋይዳ ያላቸውን አርጆ ዴዴሳ እና ወልቃይት ግድቦችን በተያዘው ጊዜ እንዳንፈፅም አድርጎናል በማለት ገልጿል።
የኮርፖሬሽኑ ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ሥራ አስከያጅ ጥንፉ ሙጬ ኮርፖሬሽኑ ትልቅ ሰው ሰራሽ የውሃ መሄጃ ቦይ ርዝመቱ 134 ኪ.ሜ፣ ስፋቱ 46 የሆነውን ደቡብ ኦሞን በመገንባት ላይ ሲሆን ይህንንም ለማስፈፀም ከመንግሥት 906 ሚሊየን ብር እንደተበደረ አስታውቀዋል። ኮርፖሬሽኑ ከዚህ በፊት ሲንከባለሉ የነበሩትን የርብ ግድብ ጥቅምት 18 ማስመረቁ ይታወሳል። ሞጆ ደረቅ ወደብ ማስፋፊያ ምዕራፍ ሁለት እና ሶስት ፕሮጀክቶችን በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ ሰፊ ርብርብ እያደረገ ይገኛል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ታኅሣሥ 27/ 2011 ጊዳቦን እንደሚያስመርቅ ታውቋል።
በ2010 ሰባ ስድስት ነጥብ አምስት ከመቶ እቅዱን በማሳካት አትራፊ በመሆኑ ለሠራተኞቻችን የሁለት እርክን ጭማሪ እና የአንድ ወር ደመወዝ ጉርሻ እንዲሰጥ ተወሰኖ የነበረ ቢሆንም ሠራተኞቹ ለካምፕ ቆይታ ማካካሻ አበል የተመደበው 950 ሚሊየን ብር እንዳልተከፈላቸው ቅሬታቸውን ገልፀዋል። ኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች ላነሳው ጥያቄ ‹‹ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ ማካካሻ አበል ከደመወዝ ጋር አብሮ እንዲከፈላቸው ውሳኔ ተሰጥቶበታል›› ሲሉ ጥናፉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን ቀደም ሲል የተለያየ ሥያሜ የነበራቸው ሦስት ተቋማት ማለትም የኢትዮጵያ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን እና የሕንፃ ቴክኖሎጂ ኮንስትራክሽን ዘርፍን በማዋኃድ ሥራ መጀመሩ ታውቋል።
መዋቅሩን በተመለከተ ሦስቱ ተቋማት በመጡበት ጊዜ ዕውቅትና ክህሎት ባላቸው ሰዎች ሰፊ ጥናት ተደርጎ ሲሠራ የቆየ ቢሆንም መዋቅሩ ወቅታዊ ሁኔታን ያገናዘበ መሆን ስላለበት እንደገና መፈትሽ አለበት በሚል ኮሚቴ ተዋቅሮ እየተሠራ መሆኑም ታውቋል። ኮንስትራክሽኑ የተቋቋመው በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 366 በ2008 ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ20 ሺሕ በላይ ሠራተኞችን ያስተዳድራል።

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here