የሴቶች ጥያቄ በወንዶች አገር

0
1151

ንትርክ የማይለየውን የሴቶች የእኩል ዕድል እና መብቶች ጥያቄ፣ ገና በኢትዮጵያ አልተጀመረም የሚሉት ዮናስ አሽኔ (ዶ/ር)፣ ‘የቢልለኔ ጥያቄ’ ላይ ተንተርሰው ከተለያዩ የግራ ዘመም ርዕዮት እና ‘የባሕል አተያዮች’ አንፃር የሚቀርቡ አቤቱታዎችን በመጠቃቀስ ሙግታቸውን ያቀርባሉ።

 

 

በ1903 የኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን በአውሮፓ ጉብኝት ወቅት የአገረ እንግሊዝ ሴቶች ጥያቄዎቻቸውን በአደባባይ ያቀርቡ ነበር። በጉዞ ማስታወሻቸው ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ ገጠመኙን እንዲህ አስቀምጠውታል፦
“ከዚያም ወደ ሰፈራችን ስንመለስ ከሺሕ የሚበልጡ ብዙ ሴቶች ባንዲራ አሲዘው፣ ጥሩምባ እያስነፉ አገኘን። እነርሱንም ለማየት የተሰበሰበው ሰው ልክ አልነበረውም። ደጃዝማችም ‘እነዚህ ምንድናቸው?’ ብለው ጠየቁ። በአውሮፓ ሴት እጅግ ይከበራልና ቢያከብሩዋቸው ከወንድ የበለጡ መስሏቸው ከሴቶች ወገን እየተመረጥን ወደ አማካሪነት እንግባ የሚሉ ናቸው። ለዚህም ነገር አሲረው የተነሱ 50 ሺሕ ይሆናሉ። ወንዶቹ ግን እጅግ ባለ አዕምሮ ናቸውና የማይቻለውን የተነመኘውን ሰው ዝም ሲሉት አውቆ ይተዋወቃል ብለው እነዚህንም ሥራቸውን ሳያደንቁ እነርሱንም ሳይከለክሉ ዝም ቢሏቸው ባንዲራቸውን ይዘው ጥሩምባ እያስነፉ ከተማውን ሲዞሩ የሚጣላቸው የሚያደንቃቸው ቢያጡ እልካቸው ሲበርድ በየቤታቸው ይገባሉ። ሁለተኛም አይመለሱ፣ ብሎ ባልደረባችን ሚስተር ዳርመር መለሰላቸው። ይህም ከሴት እልከኝነትና ግብዝነት አይጠፋምና ጥፋታቸውን ሳይመለከቱ ንቆ ዝም ቢሏቸው አውቀው እንዲተውት ያስረዳል።”
ዛሬ ከመቶ ዓመት በኋላ ዳርመር ከተባለው ሰው ሐሳብ የባሰ ኋላ ቀር ድምፅ በምድረ ኢትዮጵያ ይሰማል። በአገረ ኢትዮጵያ ዛሬም ቢሆን ሰፊ የሴቶች አርነት እንቅስቃሴ የለም። ዛሬም ከመቶ ዓመት በኋላ የሴቶች ጥያቄ በኢትዮጵያ ተነስቷል ማለት አይቻልም። ዛሬም የሴቶች ጥያቄ የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ ማኅበር ያስደነብረዋል። ኢትዮጵያ ዛሬም የወንዶች አገር ናት።
በአገሪቱ ብዙ ጊዜ ብልጭ ድርግም የሚለው የሴቶች እንቅስቃሴ እና ስለሴቶች መብት የሚነሳው ጥያቄ እና ክርክር አንዲት ሴት ዘግናኝ ጥቃት ሰለባ በሆነችበት ወቅት ነው። ይህም ቢሆን በአንድ በኩል ተጎጂዋን ሴት የራሷ ጥቃት ደራሲ የሚያደርግ ትርክት በሌላ በኩል ሕግ ላይ ብቻ በሚሽከረከር ዲስኩር የተዋጠ ክርክር ነው። ድርጊቱ ማኅበረሰቡ ቆም ብሎ ራሱን እንዲፈትሽ የሚያደርግ፣ ኩራቱን የሚተችና አካሔዱን እና አወቃቀሩን የሚጠይቅ መሆን ሲገባው ሁሌም በተጎጂ እና በጥቃት አድራሹ ግለሰባዊ ታሪክ ዙሪያ ተወስኖ በጉንጭ አልፋ ክርክር የሚደመደም አጭር ልብወለድ ሆኖ ያልፋል። የምትቀጥለውን የጥቃት ሰለባ ከሌላ አሰልች ክርክር ጋር ታጅባ እስክትመጣ ድረስ። እሷም በቅፅበት ከማኅበረሰብ ትውስታም ትጠፋለች። ይህም የፖለቲካ ማኅበረሰቡ የተሸመነበት ዋነኛ አባታዊ ስርዓት (patriarchal) ድር እንዳይፈተሽ የአገሪቱ የነጻነት አድማስ እንዳይሰፋ አድርጓል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ በተካሔደውም መሬት አንቀጥቅጥ ሕዝባዊ እምቢተኝነት የሴቶች የትግል ሚና ገና አልተወሳም። በቄሮ በፋኖና በሌሎች የወጣቶች ትግል የሴቶች ምስል ጎልቶ መነገር አልተጀመረም። በሰፊው ሕዝባዊ ጥያቄዎች ውስጥ የሴቶች ጥያቄ ምንድነው ብለን አልጠየቅንም።
የሴቶች ጥያቄ በቅጡ ሳይነሳ መንግሥት ብዙ ሴቶችን በፖለቲካ የሥልጣን መንበር ላይ በማስቀመጥ ለመመለስ ሞክሯል። 50% የአገሪቱ ካቢኔ የመከላከያ ሚኒስቴርነት ቦታ ጭምር ለሴቶች አድሏል። የአገሪቱ ሴት ርዕሰ ብሔር
ሠይሟል። በብሔራዊ ተቋማት ሴቶች በስፋት ሥልጣን ይዘዋል። በአዲስ አበባ በክፍለ ከተሞች አስተዳደር እና በተለያዩ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ሴቶች ቁንጮውን ወንበር ይዘዋል። በዚሁ ሳምንትም ብዙ ሴቶች በአምባሳደርነት ተሹመዋል። ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ ሴቶች ጥያቄ ዙሪያ የመንግሥት መልስ የአደባባይና የማጀት የውይይት ርዕስ ሆኖ ቆይቷል። የፖለቲካ ሕይወት በተከፈተለት መሥመር መሔድን ግን ቀጥሏል። በዚህ የፖለቲካ ዐውድ ውስጥ ሌላ ሴት ላይ ጥቃት ላለመከሰቱ ምን ዋስትና አለ? የሴቶች ጥያቄ ሩቅ ተወርውራ እንደተሰወረች ኳስ ከትውስታችን እየደበዘዘ ሔዷል። እንደውም ክርክራችን መልስ ላይ ብቻ አትኩሯል። የኢትዮጵያ ሴቶች ጥያቄ ምንድን ነው? ይህን ጥያቄ በንድፈ ሐሳብ አዳብራ ከአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ እየቀዳች የምትጠይቅ ሞጋች እስክትመጣ ሌላ መቶ ዓመት እንጠብቅ ይሆን? ዛሬም አብዮቱ ግቡን ሲመታ፣ ልማቱ ሲሳካ የሴቶች ጥያቄ አብሮ ይመለሳል የሚል መንግሥት ላለመፈጠሩ ምን ዋስትና አለ? ‘ነገሮች በተለወጡ ቁጥር ባሉበት ይቀጥላሉ’ ያለ/ች/ው ማን ነበረ/ች?

የቢልለኔ ጥያቄ
የሴቶች ሹመት ክርክር እየቀዘቀዘ በሔደበት ወቅት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ሴክሬታሪ ቢልለኔ ሥዩም “ወይዘሮ ወይም ወይዘሪት” የሚል ማዕረግ አላስፈላጊነት መግለጻቸው እንደሞገድ በሚሔድ የሚመጣው ክርክር እንደገና እንዲመጣ ምክንያት ሆኗል። ሐሳቡ የአባታዊ ስርዓት አርበኞችን ‘ነርቭ’ የነካ ይመስላል። የዲሞክራሲያዊ አራማጆችን የነጻነት ግንዛቤ ከትዝብ የሚያስገባ ክርክርን ከፍቷል። የአደባባይም ሆነ የማጀቱ ክርክር በአገሪቱ የነጻነት መንገዶችን ምን ያህል ሩቅ እንደሆነ አሳይቶናል። የሴቶች ጥያቄን ከመንግሥት ሹመት እና ቢልለኔ ሥዩም ያነሱት ሐሳብ እሱንም ተከትሎ የተደረገው ክርክር ከግራ ዘመም ኅልዮት ጋር አያይዘን በአጭሩ እንመልከት።
የሴቶች ጥያቄ በግራ ዘመም ኅልዮት
የግራ ዘመም ኅልዮት (Theory) የሴቶች ጥያቄን በሦስት ይከፍለዋል። “ባንድ ወገን ጠጋኞቹ እንስታዊነት፣ በሌላ ወገን ሥር ነቀሎቹ አብዮተኞችና ላብአደሮች፣ በመሐል ደግሞ የሚሙለጨለጩ የንዑስ ከበርቴ ወይዘሮዎችና ቆንጆዎች ይፋተጋሉ” ትላለች ዓለሚቱ ረታ ‘የሴቶች ጥያቄ’ በሚለው የትርጉም ሥራዋ መግቢያ ላይ። ግራ ዘመሙ ርዕዮተ ዓለም እንስታዊነት (feminism) ዋና የትችት ዓላማው ነው። እንስታዊነት የቡርዧ እና የንዑስ ከበርቴ ሴት ላይ ስለሚያተኩር በወዛደሩ መደብ ትግል ውስጥ ቦታ የለውም፤ እንዲያውም “እንስታዊነትን ሴቶችን እውነተኛ የነጻነት መንገድ ፆታና ብሔር ወዘተ. ሊያግደው የማይችለውን የወዛደሮች የመደብ ትግል የሚቃረን አደገኛ ዝንባሌ” ይለዋል። የሴቶች ጥያቄ በተለይ “ስለወዛደር አፈር ገፊ ሴት እንጂ በሌሎች መደቦች ውስጥ ስለሚገኙ ሴቶች አይደለም” ይላል። የወዛደሩ አብዮት የሚቆመው ለብዙ ጓዝ ሳይሆን ለወይዘሪቱ፣ ለድሀዋ ገበሬ ነውና። በዚህም መሠረት የሴቶች ጥያቄ ከመደብ ጥያቄ ነጥሎ አይመለከተውም። ጥያቄዎችንም በመደብ ከፋፍሎ ጠጋኝ፣ ሥር ነቀል፣ መሐል ሰፋሪና በራዥ በማለት ይከፋፍላል።
በሌላ በኩል ይህ ክርክር እየሰፋ ሔዶ የሴቶችን ጥያቄ የስርዓተ ፆታ ብቻ ሳይሆን ድርብ ድርብርብ በመሆን ይህንን ባሕርዩን አንድም በተለያየ ገጽ፣ አንድም ደግሞ አንዱን ከሌላው ማለትም ከመደብ፣ ከብሔር እና ከፆታ ጭቆና ጋር አገናዝቦ መንገድ ማስያዝ ያስፈልጋል በማለት ይመክራል። ይህን ተከትሎ በእንስታዊነት ንቅናቄዎች ዙሪያ ሰፊ ክርክር ከአውሮፓ እስከ አፍሪካ እና እሲያ ተካሔዷል። የሴቶች ጥያቄ ከተለያዩ ዐውዶች የሚቀዳ በልዩነት የተዋሐደ የኣርነት እንቅስቃሴ ሆኗል። በዛም የግራ ዘመሙ ርዕዮተ ዓለም ምናልባትም ከፍሬድሪክ ኤንግልስ ‘የቤተሰብ፣ የግል ንብረትና የመንግሥት ጥንተ ነገር’ ከሚል መጽሐፍ ጀምሮ ወሳኙን ሚና ተጫውቷል። ነገር ግን አንዳንድ ወሳኝ ጥያቄዎች በመደብ በፖለቲካ በአብዮት ሥም የማፈን ሁኔታዎች ይታይበታል። ለምሳሌ አኔሳ አርማን የምትባል ኮሚኒስት “ነጻ ፍቅር በኮሚኒስት ዓለም” በሚል ያነሳችውን ሐሳብ ጥያቄውን የቡርዣ ጥያቄ በሚል ብዙ ትችቶች ተነስቶበታል። በተለይም የቁስ አካል እና ገንዘብ ጉዳይ ከነጻ ፍቅር ጋር ምን ይወሰናል በማለት የተለያዩ መደቦች ስለፍቅር የተለያየ ግንዛቤ ይኖራቸዋል በማለት ቁሳካላዊ ግን ሌሎች ምክንያቶችን ያገለለ ትንታኔ ያቀርባል። ይህም ንዑሳን ጥያቄዎች ንዑሳን መልሶችና ትግሎች ከአብዮት ጥላ ሥር ስለሚታዩ አብዮቱን የማራቅ ሁኔታ ይፈጥራሉ ተብሎ ይታሰባል።
እነዚህ ንዑሳን የተባሉ ጥያቄዎች በራሳቸው የታሪክ ዐውድ ውስጥ አይተነተኑም። የሴቶች ጥያቄ ማለትም በሕግም፤ በኑሮም፣ በቤተሰብ ውስጥ፣ በመንግሥት አስተዳደርና በኅብረተሰብ ውስጥ ከወንዱ ጋር ሙሉ እኩልነት ማግኘት ማለት ነው፤ ይህም የቡርዧዎች ሥልጣን ማክተም ማለት ነው ይላል። ከዚ ውጭ የሚነሱ ጥያቄዎች ጠጋኝና ስርዓቱን እሽሩሩ የሚሉ ናቸው በማለት ይተቹታል። ሕግ ተኮር መልሶችን ሕጎች ብቻ በቂ አይደሉም፤ በዚህ ብቻ ልንረካ አንችልም በማለት ሥር ነቀል ለውጥን ያራምዳል።
ሴቶች ወደ ሥልጣን አምጡ
የግራው ኅልዮት ሴቶችን ወደ ሥልጣን መምጣት እንዳለባቸው ያትታል። በተለይም ከአብዮት በኋላ በፍጥነት ሴቶች ሠራተኞች ለከፍተኛ ደረጃ በሕዝባዊ ተቋሞችና በመንግሥቱ አስተዳደር ውስጥ እንዳይሳተፉ ይመክራል። ይህም ግብ ብቻ ሳይሆን ወደ ግብ የሚወስድ መንገድም ነው። ሴቶች በስፋት ሲሳተፉ ፈጥነው እንዲማሩና ከወንዶችም እኩል እንዲሆኑ ያስችላቸዋል። የምትሾመው ሴት የፓርቲ አባል አለመሆኗ ብዙም ለውጥም አያመጣም ይላል። የኮሚኒስት ፓርቲው ግብ ወደ ግቡ ለሚያደርሰን መንገድም ሴቶች ወደ ሥልጣን አምጡ ይላል። ‘ሴቶች ሙሉ ነጻነት እስካልተጎናፀፉ ድረስ ላብአደሩ ሙሉ ነጻነት አያገኝም’ የሚለው የሌኒን መፈክር የፖለቲካው መርሖው ነው። ዛሬ በኢትዮጵያ መንግሥት የተወሰደውን ሴቶችን ወደ ሥልጣን የማምጣት እርምጃ በጎ ጎን ወደ ግብ እንደሚወስድ መንገድ አንዲት እርምጃ መውሰድ እንችላለን። ከአብዮት በፊት ባለ መንግሥታዊ አስተዳደር ሴቶች ሥልጣን መያዝ አዎንታዊ ተምሳሌት እና የፖለቲካ ይዘት ፋይዳ ቢኖርም ትልቁ ስጋት ‘የአስተዳደራዊ እንስታዊነት’ ነው ትላለች፤ በተለይ በዓለም ዐቀፍ ተቋሞች ላይ ሴቶችን የመሾም ኹነት ያጠናችው ጄኔት ሀሌ።
የኢትዮጵያ መንግሥት መልስ እና ‘አስተዳደራዊ እንስታዊነት’ እንደ ስጋት
የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው ሴቶችን ወደ ሥልጣን የማምጣት ውሳኔ ከድኅረ አብዮት የግራ ዘመም ትንታኔ ስንመለከተው ተራማጅ ውሳኔ ነው ልንል እንችላለን። በተለይ ይህ እርምጃ በራሱ ግብ ሳይሆን ወደ ግብ የሚወስድ ተምሳሌታዊ እና የፖለቲካ ይዞታዊ ፋይዳ ያለው ፍኖት ነው። ኅልዮቱን ተመርኩዘን እርምጃው ሴቶች ፈጥነው እንዲማሩ ልምድ እንዲቀስሙ ወደ ነጻነት የሚደረገውን የፖለቲካ ይዞታ ያፋጥነዋል ልንልም እንችላለን።
ሆኖም የዚህ ተራማጅ ውሳኔ ትልቅ ስጋት ‘አስተዳደራዊ እንስታዊነት’ ነው። ይህም ጃኔት ሀሌ እንዳብራራችው እንስታዊ እና የእንስታዊነት ሐሳቦችን ቀስ በቀስ በአገዛዝ ተቋማዊ ኃይል ውስጥ በማሳለጥ አስተዳደሩ እንስታዊነት ባሕሪይ ያላብሰዋል። ይህም እንስታዊነትን ከፖለቲካ አርነታዊ (emancipatory) እና ሊቃውንታዊ (intellectual) እንቅስቃሴ ወደ አገዛዝ መሣሪያ ያሸጋግረዋል ትላላች። ዋና ዋናዎቹ እና ቁልፍ ጥያቄዎች የሚያደበዝዝ ተፅዕኖ ይኖረዋል ትላለች። ይህንንም ‘አስተዳደራዊ እንስታዊነት’ ብለዋለች። በኛ አገር ዐውድ ውስጥ ‘መንግሥታዊ እንስታዊነት’ (State feminism) ልንለው እንችላለን።
ይህ አሉታዊ ገጽ ግን የሴቶች ሥልጣን መያዝ፣ የሴቶች ጥያቄ እንደተመለሰ ተደርጎ ከተወሰደ ብቻ የሚፈጠር ፖለቲካዊ ኹነት ነው። የብዙ ተራማጅ ድምፆች እና ጥርጣሬዎች በኢትዮጵያ መንግሥት ውሳኔ ላይ የተሰሙት ይህ ውሳኔ በግራ ዘመሙ ቋንቋ ጠጋኝ ውሳኔ የመሆኑ ስጋት ነው። ነገር ግን ከትችቱ ባሻገር ሹመቱ የሴቶች ጥያቄ መመለስ የሚያሳይ ሳይሆን ጥያቄውን ለማንሳት ፖለቲካዊ መልሶች እና ማኅበረሰቡን የማሸጋገር ሒደት ንዑስ ጅማሮ ነው ብሎ መወሰድ ያስፈልጋል። የሴቶች መንበሩን ለተራማጅ ፖለቲካ እንዲጠቀሙበት መወትወት ዋነኛ ታክቲክ መሆን አለበት። የቢልለኔ ሥዩም ሐሳብ ምን ያህል ክርክር እንዳስነሳ እና ሴቶች የያዙት ሥልጣን ለተመሳሳይ ንዑስም ሆነ ዐብይ ተራማጅ ፖለቲካ ሊጠቅሙበት እንደሚችሉ ፍንጭ ሰጥቷል። የሴቶችን ጥያቄ ሌላው መመልከቻ መነፅር የአገር ባሕል ከምዕራባዊ ወረራ የመጠበቅ ትርክት ነው።
የምዕራባውያን ተፅዕኖ እንደምክንያት
የሴቶች ጥያቄ ተከትለው የሚነሱ ትችቶች እና ዝም ማሰኛ አመክንዮች አንዱ ጥያቄውን ‘የነጭ ምዕራባዊ ሴቶች ጥያቄ ነው’ የሚለው አንዱ ነው። ይህ በብዙ አፍሪካ አገሮች፣ በዐረቡ ዓለም እና በእስያ የሴቶች የነጻነት እና የእኩልነት ጥያቄ ከአውሮፓ የመጣ ባህል በራዥ፣ ሃይማኖት ቀያሪና ትውፊት አፍራሽ ጥያቄ ነው የሚል ወቀሳ ይደረስበታል። በእርግጥ የምዕራብ ሞደርኒቲ ራሱን አግዝፎ ዓለም ዐቀፋዊነት በሱ ዛቢያ አሀዳዊ አድርጎ ያቀርባል። ከዚህ ውስጥ የምዕራብ እንስታዊነት ይህንኑ ከምዕራብ ኹነት የተሸመነ አሀዳዊ ዓለማቀፋዊነት በሌሎች ላይ ለመጫን ይሞክራል። የዚህም ዋና ትርክቱ አባታዊ ስርዓት (patriarchy) ብቻ የሴቶች ጎስቋላ ሕይወት ደራሲ አድርጎ ማየቱ ነው። ይህም የግራዘመሙ አብዮት የቡርዧ ሴቶች ጥያቄ ይለዋል።
ሌሎች በአፍሪካ እና በእሲያ ያሉ ተራማጅ ድምፆች ደግሞ መደባዊ ጭቆናን ብቻ ሳይሆን ቄሳራዊ (colonial) የዘር (race) የብሔር እና የካፒታሊዝም ጭቆና ማየት የማይችል ነው ይሉታል። ከነዚህ ጥያቄው ከሀብታም ሴቶች የሕይወት ሙዳይ የሚታይ ሆኖ ግን ዓለማቀፍ የሴቶች ጥያቄን ከአባታዊ ጭቆና ብቻ የሚተነትን በእኔነት ድር የተሸመነ ጥያቄ ይሉታል። በኛም አገር ከተነሱት ውስጥ የሴቶች ጥያቄዎች ከምዕራብ ብቻ የተቀዳ አድርጎ የማቅረብ እና የመተቸት ሁኔታ እንጂ ጥያቄውን በተሻለ ሁኔታ የመተንተን ለመልሱ የሚታገል ተራማጅ እንቅስቃሴ ጎልቶ አልወጣም። ለመሆኑ የሴቶች እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ መቼ ይጀምራል? ከንግሥት ዮዲት ፖለቲካ ወይስ ከ‘ብርሃንና ሰላም’ ጋዜጣ ውይይቶች? ከተማሪዎች እንቅስቃሴና የ፲፱፻፷፮ቱ አብዮት? የሴቶች ንቅናቄንስ በምን ሥም እንጥራ? ‘እንስታዊነት’፣ ‘ሴታዊነት’፣ ‘እናታዊነት’ ወይስ ሌላ? የሴቶች ጥያቄ በሕዝባዊ እንቅስቃሴዎችና በሕዝባዊ ዲሞክራሲ ያለው ቦታ ምን ዓይነት ነው?
በቅርቡ ቢልለኔ ያቀረቡት ሐሳብ ላይ የተነሱት ትችቶች በአብዛኛው ከዚሁ መንፈስ ተቀድተው ለአጭር ግብ የዋሉ ናቸው። በአንድ በኩል ተራማጅ ድምፆችን የሐሳቡን ንዑስነት እና ጠጋኝነት ከግራ ዘመሙ ኅልዮት እየቀዱ ተችተዋል።
በጣም አስገራሚው የሊብራል ዴሞክራሲ አራማጆች እና የድኅረ ርዕዮተ ዓለም አርበኞች ጭምር የግራውን መንፈስ ተላብሰው የአርሶ አደሯን ጥያቄ ለትችታቸው መነሻ ማቅረባችው ነው። በሌላ በኩል የባሕል፣ የወግ እና የፕሮቶኮል ጠበቆች ምዕራባዊነትንና ወረራውን ሐሳቡን ለማጣጣል ተጠቅመውበታል። አንዳንዶች ሐሳቡ የፕሮቶኮል ድንበርን የሚጥስ ሲያደርጉት፥ ሌሎች ደግሞ የቋንቋ ሕግን የሚያነውር አድርገው ቋንቋና ፕሮቶኮል ምንም እንኳ ጨቋኝ ቢሆኑም የማይሻሩና የማይደፈሩ አደርገው ትችቶች ሰንዝረዋል። ሕግ እና ፕሮቶኮል የታሪክ እና የፖለቲካ ውጤቶች መሆናቸውን ቀርቶ ዘላለማዊ የተፈጥሮ ሕግ እንደሆኑ በማስመሰል ሐሳቡን በድፍረት እና ባለማወቅ የቀረበ አድርገውታል። ከዚህ የበለጠ አባታዊ እና ተባዕታዊ ጨቋኝ ድምፅ ከየት ይገኛል?
የማይደመደመውን መደምደምያ
አሁንም በኢትዮጵያ የሴቶች ጥያቄ መልስ እንጅ ጥያቄው በቅጡ አልተነሳም። ጥያቄዎች ሲነሱ ከግራ ዘመሙ ኅልዮት ወይም ከባሕልና ወግ አርበኝነት በሚነሱ ትችቶች ዝምታ እንዲውጣቸ ይደረጋል። በሴቶች ላይ ጥቃት ሲደርስ የግራውም የአርበኛውም ድምፅ ዝም ይላል። ክርክሩ ሕግ እና በግል ሕይወት ዙሪያ ይዳፈናል። ንዑስም ይሁን ዐብይ የሴቶች ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄ ነው። የሴቶች ጥያቄ ሕዝባዊ ተራማጅ ጥያቄ ነው።
የሴቶች ጥያቄ ማኅበረሰቡን የሚያሸጋግር የለውጥ ድምፅ ነው። የሴቶች ጥያቄ ብሔራዊ እና ዓለማቀፋዊ ጥያቄ ነው። ጥያቄው ከግል የሕይወት ልምድ ሙዳይ፣ ከማጀት፣ ከአደባባይ፣ ከከተማ ከገጠር ከተለያዩ መደቦች ሊቀዳ ይችላል። ጥያቄው እኔን እና አንቺን ከማትመስል ሴት ሕይወት ተሞክሮ ሊመነጭ ይላል።
የሴቶች ጥያቄ የብሔር፣ የመደብ፣ የፆታ ጉዳይ ከማጀት እስከ አደባባይ ተደራርቦ የተጨቆነ ማንነት ሲያምፅ የሚፈጠር የኣርነት ድምፅ ነው። ጥያቄው ንዑስም ይሁን ዐብይ ዋናው ጉዳይ እኛ እና የኛ ትችት የጭቆና ግድግዳ ማገር ወይስ የነጻነት እና የእኩልነት ድምፅ ይሆናል የሚል ነው። ምርጫው የኛ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here