የማያዳላ የተፈጥሮ ሥጦታ!?

0
771

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

«ልዩነት እንዳለንማ ማመን አለብሽ። በተፈጥሮ ለእናንተ የሚከብድ ለእኛ ግን ቀላል የሆነ ብዙ ነገር አለ» አለኝ። ከአብሮ አደግ ወዳጄ ጋር የሴቶችን ጉዳይ የተመለከተ ምንም ዓይነት ሐሳብ ሲነሳ ይህን ሳይጠቅስ አይቀርም። እኔም አስተያየቱን ተጋፍቼ አላውቅም። ለምን? ድንጋይ ፍለጪ ብባል አልፈልጥም፤ ወይም ኩንታል ጤፍ ተሸከሚ ብባል አልሸከምም።
ይህን የአቅም ጉዳይ በዚህ ሁኔታ ወደ ክርክራችን ሲያካትት ነገሩን እንደተቀበልኩት አምኖ ርዕሳችን ይቀየራል። አሁን ግን መልስ አገኘሁና «ልዩነት እንዳለን እመኚ! እናንተ ተፈጥሮንም ልትገዳደሩ ነው እንዴ?» ሲለኝ ተቀብዬ አላለፍኩትም፤ መልስ ነበረኝ። በቅድሚያ ግን መልሱን ከየት እንዳገኘሁ ልንግራችሁ።
በአንድ የቴሌቭዥን ጣቢያ በመድረክ ክዋኔ ላይ ነዋሪነቷን ባህር ማዶ ያደረገች ብርቱ ሴት ትታያለች። ብዙ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከመሥራቷ የተነሳ ሰውነቷ በብዛት ወንዶች ላይ የምናየውን የስፖርተኞች ቅርጽ ይዟል። ለዛች ሴት ድንጋይ መፍለጥም ሆነ ኩንታል መሸከም ቀልድ ነው። ሰውነቷን በዛ መልኩ መቅረጽ ስለፈለገችም አድርጋዋለች።
ንግግሮቿንና ለጠያቂዋ የሰጠቻቸው መልሶች ይቆዩን። የተመለከትኩት ነገር ብቻውን ግን ለራሴም የምቀበለውና ለወዳጄን የምነግረውን ሐሳብ ሰጥቶኛል። ያቺ ሴት ሰውነቷን ገርታ ለሴት ይከብዳል የሚባለውን ሁሉ ችላ አሳይታለች። በእርግጥ እንዲህ ያሉ ብዙ ሴቶች የኑሮ ቀዳዳቸውን በጊዜ በደፈኑ አገራት በብዛት ይገኛሉ።
እኛ ጋር «ሥጋ ሞኝ ነው» እንዲሉ፤ ሰውነታችንን እንደምርጫችን እኛ እንዳደረግነው የሚሆን ነው። በጤና መታወክ ምክንያት ካልሆነም በቀር ያሻንን እንዲችል አድርገን በእንቅስቃሴ ልንሠራው እንችላለን። ለዚህ ፍቅሩና ፍላጎቱ ካለ ብቻ በቂ ነው።
በእርግጥ ለማስተዋል መዘግየቴ እንጂ፤ ልጅ መውለዳቸው አቅም ሳይነሳቸው እኔ ነኝ ያለ ጎረምሳ በብዙ ጉልበት የሚያነሳውን የቅጠል ክምር ተሸክመው ዳገት ወጥተው ቁልቁለት የሚወርዱ የአገሬ እናቶችን አልረሳሁም። በተፈጥሮ የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎቻችንን የተለያዩ ቢሆኑም፤ እንዳንችል ሆነን የተፈጠርንበት ምንም ነገር የለም። ነገሩ የምርጫ ጉዳይ ነው። ይህ በውጫዊ አካል ብቻ አይደለም፤ በውስጥ አዕምሮና ልቦና አንጻርም ሊታይ የሚገባው ነው።
እናም! ለወዳጄ የሰጠሁት መልስ ይህ ነበር። «ልዩነት መበላለጥ ማለት አይደለም። አንተ ድንጋይ መፍለጥ ባትችል ሴት ልትባል ነው? እርሷስ ብረት ስለምትገፋ ወንድ ልንላት? በፍጹም። በሰውነታችን ልንሠራበትና ልንከውንበት እንደመረጥነው እንለያያለን። የሚያፈላልግ እንጂ የሚያበላልጥ የተፈጥሮ ስጦታ እንደሌለ ሳታውቅ ቀርተህ ነው?» አልኩት። በሐሳቡ ተስማምቶ ይሁን አላውቅም፤ ግን በአሁኑ መልስ ሳይሰጥ ያለፈው እርሱ ነበር

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here