ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር መዝጋቷን ተከትሎ በኤርትራ የሸቀጦች ዋጋ እየናረ ነው

0
539

ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስናትን ድንበር መዘጋቷን ተከትሎ በኤርትራ የምግብና የግንባታ ዕቃዎች ጭማሪ ማሳየታቸውን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
ከአራት ወራት በፊት በዛላምበሳ እና ራማ በኩል የሚገኘውን የሁለቱ አገራትን ድንበር መከፈትን ተከትሎ የጤፍ፣ የበርበሬና ሌሎች ቅመማ ቅመሞች የዋጋ ቅናሽ ማሳየታቸው ይታወሳል።
ሥማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ በአስመራ የሚኖሩ ግለሰብ እንደገለጹት በኤርትራ መንግሥት የተወሰደውን እርምጃ ተከትሎ በአስመራ በሚገኙ ዋና ገበያዎች የተጋነነ ባይሆንም የዋጋ ጭማሪ በአንዳንድ ሸቀጦች ላይ ታይቷል።
እንደ አብነትም ጤፍ ከ1700 ናቅፋ ወደ 2000 ናቅፋ የጨመረ ሲሆን በርበሬ ደግሞ በኪሎ በ20 ናቅፋ አካባቢ ጨምሮ በ80 ናቅፋ እንደሚሸጥ ገልጸዋል።
ከድንብሩ መዘጋት በፊት፤ የኤርትራ መንግሥት ዜጎቹን ግንባታ እንዳያደርጉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አሸዋና ብሎኬት ግዢ ካገደበት ቀን አንስቶ ጭማሪ ማሳያት የጀመረው ሲሚንቶ ከ 250 ናቅፋ ወደ 400 ናቅፋ መጨመሩ ከምንጮች መረዳት ተችሏል። አንዳንድ ነጋዴዎችም ምርቱ ዋጋ ሊጨምር ይችላል በሚል ስጋት በመጋዘን ውስጥ ማከማቸት መጀመራቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ለድንበሩ መዘጋት በኤርትራ በኩል ይህ ጋዜጣ ለኅትመት እስከተላከበት ትላንት ምሽት ድረስ ለሕዝብ ይፋ የሆነ መግለጫ የለም።
በቅርቡ በኬኒያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ መለስ ዓለም በበኩላቸው የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ዳግም መዘጋቱን በተመለከተ ሚንስቴሩ መረጃ የለውም ብለዋል።
በተጨማሪ ከሰሞኑ የኢትዮ ኤርትራ ድንበር ዳግም መዘጋቱንና ኤርትራም ወታደሮቿን ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ማስጠጋቷን በተመለከተ የሚናፈሰው ወሬ ምን ያህል ትክክለኛ ነው ተብለው ለተጠየቁት መለስ ስለጉዳዩ ውጪ ጉዳይ መረጃ እንደሌለው ተናግረዋል።
እሳቸው ይህንን ቢሉም፤ ከወትሮ በተለየ መልኩ የኤርትራ ወታደሮች በብዛት ሁለቱን አገራት የሚያዋስነው ድንበር ላይ እንደታዩ አብረሃ ተስፋይ የሚባሉ በአካባቢው ተጉዘው የነበሩ የአይን እማኝ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በተጨማሪም ከባለፈው ሐሙስ አንስቶ ወደ ኤርትራ ሊያቋርጡ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ከፌዴራል መንግሥት ልዩ ፈቃድ ሊኖራቸው እንደሚገባ ተነግሯቸው እንደሚመለሱ መደረጋቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ነገር ግን፤ ኤርትራ ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ድንበሩን ያለምንም ፈቃድ ወረቀት በማቋረጥ ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚችሉ ታውቋል።
ስለ ተዘጋው ድንበር ምንም ይፋዊ መግለጫ ያልሰጠው የኤርትራ መንግሥትም ሆነ ስለ ጉዳዩ የማውቀው ነገር የለም ያለው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ፈቃዱ የሚገኝበትን መንገድ ለሕዝቦቻቸው ይፋ አላደረጉም። በዚህም የተነሳ፤ በሁለቱም አገር የሚገኙ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች መቸገራቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል፤ የኤርትራ ፕሬዘደንት ከሆኑት ኢሳያስ አፈወርቂ ቀጥሎ ተሰሚ ናቸው ተብሎ በሚታመኑት የቀድሞው የኤርትራ መከላከያ ሚኒስትር የነበሩት ኤፍሬም ስብሃቱ (ጄኔራል) ከተደረገ የግድያ ሙከራ በኋላ ድንበሩ መዘጋቱ ደኅንነት ከማስጠበቅ ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል ሲሉ የጂኦ-ፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ።
የቀድሞ የቢቢሲ አፍሪካ አዘጋጅ የነበረውና በአፍሪካ ቀንድ ትንተናዎቹ የሚታወቀው ማርቲን ፕላውት ኤርትራ ሃብ በተባለ ድረ ገፅ ባሳረፈው ጽሑፉ የጄኔራሉ የግድያ ሙከራ በአገሪቷ ባሉ የመንግሥት ግልበጣ ለማድረግ ባሰቡ የጦር መሪዎች የተቀነባበረ ነው ሲል አትቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here