ከነዳጅ እና ማዕድናት ማውጣት ጋር በተያያዘ ክልሎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ በሚንስትሮች ምክር ቤት ሊፀድቅ ነው። የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር እንደገለፀው ከዘርፉ የሚገኘውን ሀብት ኅብረተሰቡ ሕግን በተከተለ መንገድ ተጠቃሚ እንዲሆን እየሠራሁ ነው ብሏል። ከዚህም ጋር በተያያዘ በቅርቡ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲፀድቅ ረቂቅ አዋጅ እያዘጋጀሁ ነው ሲል አክሏል።
ሚንስቴር መስሪያ ቤቱ ጨምሮ እንደገለፀው ከዚህ በፊት ይሠራ ከነበረዉ ሥራ በተለየ የነዳጅ እና ማዕድናት አልኝታ ለሆኑ ክልሎች እንዲሁም ወረዳዎች በመቶኛ የሚታሰብ ድጋፍ እንደሚደረግ አሰታዉቋል።
ምንጮች እንደገለፁት በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ ክልሎች እስከ 40 በመቶ የሚደርስ ድጋፍ እንደሚደረግላቸዉ እና በተለይ ደግሞ የማዕድን አለኝታ ወረዳዎች 2 በመቶ የሚሆን ልዩ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል በታኅሣሥ 9/ 2011 በማዕድንና ነዳጅ ልማትና ቁጥጥር ዙሪያ ከሱማሌ ክልል ጋር ስምምነት ላይ የደረሰው የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር በክልሉ ላይ የሚታየውን የነዳጅ አቅርቦት ብክነትና ብክለትን በመቀነስ የአካባቢን ልማት በማረጋገጥ ክልሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዲያገኝ እንሰራለን ብሏል። ሚኒስትሩ ዶ/ር ሳሙኤል ኡርቃቶ እንዳሉት ዘርፉ በአግባቡ ከተመራ ለአገራችን ኢኮኖሚ እስከ 30 በመቶ ሊደርስ የሚችል አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚችል፣ሆኖም ከክልሎች እና ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራት ባለመቻሉ እና በሌሎች ምክንያቶች የሚጠበቅበትን ሚና እየተወጣ እንዳልሆነ ገልፀዋል።
ቀደም ባሉት ዓመታት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከማዕድናት ማውጣት ጋር በተያያዘ የታዩት ችግሮችን ለማስተካከል እና አካባቢን ከመጠበቅ አኳያ ጠንካራ ሥራ እንደሚሠራ አስታውቋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ ጉዳያቸው እየተጠና የሚገኙ የማዕድን አውጭ ድርጅቶች እንዳሉ መስሪያ ቤቱ ተናግሯል።
በተያያዘ ዜና በቅርቡ ከኦጋዴን -ጅቡቲ የሚዘረጋው 800 ኪሎ ሜትር የተፈጥሮ ጋዝ ማስተላለፊያ ቱቦ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እንደሚነካ ስለታወቀ ከወዲሁ ስለ ካሳ አከፋፈል ባለ ድርሻ አካላትን ባካተተ መልኩ እየተሠራ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል።
በቅርቡ ከሱማሌ ክልል ጋር በተደረሰዉ የጋራ መግባባት ላይ እንደተገለፀው የጋዝ ማስተላለፊያ ቱቦ ዝርጋታ ሲጀመር ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ እድልን በሰፈዉ የሚፈጥር እንደሚሆን ይገመታል። በመጨረሻም ምንጮች እንደገለፁት ክልሎችን እና ወረዳዎችን ተጠቃሚ የሚያደርገዉ ረቂቅ አዋጅ በቅርቡ ፀድቆ ተግባራዊ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011