የኃይል አጠቃቀምን የሚቆጣጠር አዋጅ ለማዘጋጀት ጥናት እየተደረገ ነው

0
468

የፀጥታ ኃይሉን የኃይል አጠቃቀምን በተመለከተ አዲስ አዋጅ ለማዘጋጀት ጥናት እየተደረገ መሆኑን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡
‹‹ተመጣጣኝ እርምጃ›› በሚል ስም በኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይል አባላት የሚሰነዝሩት እርምጃና የኃይል አጠቃቀም ለብዙዎች መከራከሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ‹መፈክር ይዞ ለወጣ ሠላማዊ ሰልፈኛ ጥይት መመለስ› ተመጣጣኝ ሊሆን አይችልም በሚልም ብዙ ትችት ሲስተናገድ እንደነበር ይታወቃል። ይህን ተከትሎም መንግሥት የኃይል አጠቃቀሜን እፈትሻለሁ ማለቱ ይታወሳል።
ጥናቱ በኢትዮጵያ የፀጥታ ኃይሉ የኃይል አጠቃቀም ምን ይመስል እንደነበረ ከመዳሰሱም ባሻገር የሌሎች አገራት ተሞክሮን ያካትታል ተብሏል።ከዚህ በፊት በአገሪቱ ባሉ ሕጎች ላይ የሚታየውን የማኅበረሰቡን የአኗኗር ሥርዓትና ወግ በጠበቀ መልኩ ያለመዘጋጀት ችግሮችን ለመቅረፍ ጥንቃቄ እንደሚያደርግም ዐቃቤ ሕግ ገልጿል፡፡
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ዝናቡ ቱኑ ለአዲሰ ማለዳ እንደተናገሩት የማኅበረሰብ እድገት በየጊዜው እየተለወጠ የሚመጣ በመሆኑ አዲስ የሚወጡትም ይሁኑ የሚሻሻሉት የሕጎች ማዕቀፎች እድገቱን ታሳቢ አድርገው ይዘጋጃሉ። ዝናቡ አክለውም ጥናቱን እስከ ታኅሣሥ 30/2011 ለማጠቃቀልና ረቂቅ አዋጅ እንዲዘጋጅ ለማድረግ እየተሠራ ነው ብለዋል’
‹‹ሕግ ብቻውን የሚፈታው ነገር የለም›› ያሉት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ተግባብተውና ተከባብረው እንዲኖሩ ያደረጉ የብዙ ባሕል መናኸርያ መሆኗን አስታውሰዋል፡፡ ይሁንና የማኅበረሰቡም ንቃተ ሕሊና ማደግ ይገባዋል የሚሉት ዝናቡ፣ በዐቃቤ ሕግ በኩል ከዚህ ቀደም ሕግን በማስከበር ዙሪያ ያሉ ክፍተቶችን በመሙላት የተሻለ የፍትሕ ስርዓትን ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን አክለዋል፡፡ በዚህም መሻሻል ያለባቸውን ሕጎች በማሻሻል፣ ሊለወጡ የሚገባቸውን በመለወጥ እንዲሁም አዲስ የሕግ ማዕቀፍ ለሚያስፈልጋቸው ጉዳዮችም አዳዲስ ሕጎችን በማዘጋጀት ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የመቶ ቀን ዕቅድ በማዘጋጀት ወደ ሥራ መገባቱን ዝናቡ አስታውቀዋል፡፡
በተያያዘ ዜና የጸረ የጥላቻ ንግግሮችን ሕግ በተመለከተ የአስፈላጊነት ጥናቱ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ለኢትዮጵያ ያለው ጠቀሜታ ስለታመነበት በጥናቱ ዙሪያ ውይይት ሊደረግበት ዝግጅት ላይ እንደሆኑም ተገልጿል፡፡ በኢትዮጵያ ነባራዊ እውነታ ሕጉ የግድ ያስፈልጋል የሚሉት ዳይሬክተሩ የጸረ ጥላቻ ንግግር ሕግን በመጠቀም መቆጣጠር ‹‹እጅግ አስፈላጊ ነው›› የሚል እምነት አላቸው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባለፈው ጥቅምት 2011 በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች የሚሰራጩ የሐሰት ወሬዎች ሠላምን እያሳጡ በመሆኑ ሊታሰብበት ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚንስትሩን አሳስበዋል፡፡ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስቴር በማኅበራዊ የመገናኛ ትስስር ገጽ ሐሰተኛ ወሬዎች ተማሪዎቼ ለችግር እየተጋበዙ ነው ሲል ቅሬታ ማሰማቱም ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የወንጀል ሥነ ስርዓት እና ማስረጃ ሕግ፣ የሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ሕግ፣ የመረጃ ነፃነትና መገናኛ ብዙኃን አዋጅ፣ የንግድ ሕግና የምርጫ ሕግን ጨምሮ ሌሎች ማሻሻያ ሊደረግባቸው ይገባል ያላቸውን ሕጎች በጥናት እንደለየ አሳውቋል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here