የኦዴፓ እና ኦነግ ጫማ መለካካት! “የኦነግ ሠራዊት” ለዳውድ ኢብሳ ይታዘዛል ወይ?

0
1512

በኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ ተቀባይነት አለው የሚባለው ኦነግ እና የክልሉ ገዢ ፓርቲ ኦዴፓ ከፍተኛ የፖለቲካ እሰጣገባ ውስጥ ከገቡ ሰነባብተዋል። የሁለቱ ፓርቲዎች አለመግባባት መንስዔ እና እያስከተለ ያለውን ጦስ በሐተታ ዘ ማለዳ የሚዳስሰው የአዲሰ ማለዳው ስንታየሁ አባተ የኦነግ ሕዝባዊ ቅቡልነት በኦዴፓ መነጠቅ አለመነጠቁን ጨምሮ፣ በኦነግ ሠራዊት አዛዥ እና በድርጅቱ አመራሮች መካከል ያለውን የዕዝ ክፍተት ዳስሶታል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት እፈልጋለሁ ያለው የኢሕአዴግ መንግሥት በትጥቅ ትግልና በውጭ አገራት ሳይቀር ተሸሽገው ሊጥሉትና ሥልጣን ሊነጥቁት ይፈልጉ ከነበሩት የፖለቲካ ኃይሎች ጋር በሐሳብ ተፎካክረን እንሸናነፍ በሚል ሐሳብ አቅርቦ በርካታ የተቃዋሚ ጎራ ኃይሎች እስከ ዛሬም ወደ አገር ቤት መግባታቸውን ተያይዘውታል። ለሠላማዊ ትግል እንደመጡ ገልጸው ወደ ሕዝቡ ከተቀላቀሉት የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች መካከል የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አንዱ ነው።
ኦነግ በተለይም የበላይ አመራሩ ቡድን ወደ ኢትዮጵያ ከመግባቱ በፊት የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ መስተዳደሩ ለማ መገርሳና የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ወደ ኤርትራ ማቅናታቸውና ከኦነግ ሊቀመንበሩ ዳውድ ኢብሳ ጋር ተመካክረው “ሥምምነት ተፈራረምን” ማለታቸው ይታወሳል። ይሁንና እስካሁንም የኤርትራው ሥምምነት ምን ምን ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው የሚለው ግልጽ ያለ ምላሽ አልተሰጠውም። በተያያዘም በተወካዮች ምክር ቤት “አሸባሪ” በሚል በአገር ደረጃ እስከመፈረጅ ደርሶ ከነበረ የፖለቲካ ድርጅት ጋር ሥምምነት የሚፈርመው የክልል ርዕሰ መስተዳድር ወይስ የፌደራሉ መንግሥት ተወካይ የሚለውም በወቅቱ ጥያቄ ሆኖ ሲነሳ ነበር።
የሆነው ሆኖ በዳውድ የሚመራው የኦነግ ከፍተኛ ልዑክ መስከረም 5/2011 ኢትዮጵያ ሲገባ ሊቀመንበሩ በሠላማዊ መንገድ ለመታገል ስለመምጣታቸው ተናግረውም ነበር። ዳውድ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አየር ማረፊያ በደረሱበት ዕለት ሠላማዊ ትግልን ለመጀመር መምጣታቸውን ገልጸው “የሠላማዊ መንገድ ትግል አዲስ ዓይነት ሥነ ስርዓትና ዲስፕሊን ነው የሚፈልገው፤ ይኼንን በአጭር ጊዜ ውስጥ ሠላማዊ መንገድ ትግል ማለት ምን ማለት እንደሆነ ከሕዝባችንና ከወጣቱና እንደዚሁም ከአባሎቻችን ጋር፣ ከሠራዊቱ ጋር ይኼንን ሥልጠናና ውይይቶችና አስፈላጊ የሆኑትን እርምጃዎች እንወስዳለን” ነበር ያሉት። ከዚህ በተጨማሪም በሠላማዊ ትግል ውስጥ ሊኖር ስለሚገባው አካሔድ ከመንግሥት፣ ከኦሮሞ ድርጅቶችና ሕዝብ ጋር እየተወያዩ ሕዝብ እውነተኛው የሥልጣን ባለቤት የሚሆንበትን ዴሞክራሲያዊ ስኬት ለማምጣት እንደሚሠሩም ተናግረው ነበር። ለዚህም አምነውት ከመጡት የዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መንግሥት ጋር በቅርበትና በመመካከር እንደሚሠሩም መናገራቸው ይታወሳል።
ይሁንና ኦነግ በስፋት በሚንቀሳቀስበት ኦሮሚያ ክልል ዛሬም የተለያዩ ግጭቶችና የሰው ልጅ ሕልፈት እየተከተለ ነው። በዚህ መሐልም በአንድ በኩል ክልሉን የሚያስተዳድረው የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) በሌላ በኩል ኦነግ እየተወቃቀሱና የለየለት ውጥረት ውስጥ እየገቡ መጥተዋል። በቅርቡም በተለይም በምዕራብ ወለጋ የተለያዩ አካባቢዎች “ውጊያ” መግጠማቸውን በይፋዊ መግለጫ ሳይቀር ሲናገሩ ተደምጠዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ ሠራዊት?
ሕገ መንግሥቱ የታጠቀ ሠራዊትን የማደራጀትና የመምራት ኃላፊነት ሕጋዊ ሥልጣን ላለው የመንግሥት መዋቅር የተሰጠ ስለመሆኑ በግልጽ ጽፏል። ስለ ፌደራሉ መንግሥት ሥልጣንና ተግባር የሚያትተው አንቀጽ 51 (6) “የአገርና የሕዝብ የመከላከያና የደኅንነት እንዲሁም የፌደራል መንግሥት የፖሊስ ኃይል ያደራጃል፤ ይመራል” ሲል የክልል መንግሥታት ሥልጣን በተዘረዘረበት አንቀጽ 52 (2ሰ) “የክልሉን የፖሊስ ኃይል ያደራጃል፤ ይመራል፤ የክልሉን ሠላምና ፀጥታ ያስጠብቃል” የሚል ሕግ ተደንግጓል።
የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚገዙ ሕጎችም ይሁኑ ሌሎች ከሕገ መንግሥቱ ተቀድተው የወጡ የተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች በአንድ አገር ውስጥ የታጠቀ ኃይል ሊኖረው የሚችለው መንግሥታዊ ሥልጣን የያዘው አካል ብቻ እንደሚሆን ያትታሉ። ተፎካካሪም ይባሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ኃይሎች እንዲደራጁ የሚፈቀድላቸው በሐሳብ ለመታገል ብቻ ስለመሆኑም ግልጽ ነው። ታዲያ ኦነግ “ሠራዊቴ” የሚላቸው እነማንን ነው ሲባል ብዙ ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮች አሉ።
እርግጥ ነው ኦነግም ሆነ አርበኞች ግንቦት ሰባት “ተገደው” ወደ ትጥቅ ትግል አማራጭ ሲገቡ የራሳቸው የታጠቀ ኃይል ነበራቸው። በሠላማዊ መንገድ እንታገላለን ብለው ሲመጡ ደግሞ አንዱ እርምጃ የታጠቁ አባሎቻቸው ትጥቅ ፈተው ወደ ሥልጠና ስለመግባታቻውና በሒደት ወደ ማኅበረሰቡ እንዲቀላቀሉ እየተሠራ ስለመሆኑ ሲነገር ተከርሟል። ለአብነትም የአርበኞች ግንቦት ሰባት ጸሐፊ አንዳርጋቸው ጽጌ ከአዲስ ማለዳ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በንቅናቄው ሥር በኤርትራና አገር ውስጥ ሆነው በትጥቅ ሲታገሉ ስለነበሩት ትጥቅ ማስፈታትና መልሶ ማቋቋም ሲገልጹ ‘‘ከኤርትራ የመጡት ወደ 300 ገደማ ሲሆኑ አገር ውስጥ ሆነው አርበኞች ግንቦት 7 በተለያየ መንገድ ያስታጠቃቸውና ማዕከላዊነትን ባልጠበቀ መልኩ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ አምስት ሺሕ ናቸው። ከኤርትራ ከመጡት አሁን ከመቶ በላይ ካምፕ ውስጥ አሉ፤ ከካምፕ ወጥተው ወደ የቤታቸው የተመለሱት የፌደራል መንግሥቱ ዘጠኝ ሺሕ ብር እየሰጠ መልሶ ማቋቋም መርሓ ግብሩ ሲጀምር በያሉበት ሆነው የሚሳተፉበት ምርጫ ይሰጣቸዋል። የጀርመን መንግሥት ለ35 ሺሕ በትጥቅ ትግል ለተሳተፉ ሰዎች የገንዘብ ድጋፍ (ፈንድ) እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል። እሱን እየጠጠባቅን ነው ያለነው” ብለው ነበር።
35 ሺሕዎቹ የትጥቅ ትግል ተሳታፊዎች ደግሞ የአርበኞች ግንቦት ሰባት ብቻ ሳይሆኑ የኦነግና የሌሎችም በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ ድርጅት ታጣቂዎችን የሚመለከት ነው ተብሏል።
“የኦነግ ሠራዊት” እና ጥያቄው
እዚህ ላይ ግን ግልጽ ያልሆነው ነገር የኦነግ ሠራዊት የሚባለው ነው። ኦነግ ወደ አገር ቤት ሲገባ ትጥቅ ፈትቶ ነው ተብሎ ነበር። ይሁንና በኦነግ የመስቀል አደባባይ አቀባባል ላይ ከመድረክ መሪዎቹ በኩል “ዋናው ታጋይ አገር ውስጥ ነበር” የሚል ዓረፍተ ነገር በተደጋጋሚ ሲነገር ተሰምቶም ነበር። ኦነግ በይፋ አገር ቤት ከገባ ማግስት ጀምሮ በሚፈጠሩ ግጭቶች “የኦነግ ሠራዊት” የሚለው ሐረግ እጅግ አከራካሪ እየሆነ መጥቷል። በአንድ በኩል ኦነግ (በአመራሮቹ መግለጫዎች) የማያውቃቸውና በእሱ ሥም የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ጥቃት እያደረሱ ስለመሆኑና ኦነግ የሚለው ቃል የፖለቲካ ማጣፈጫ እየሆነ መምጣቱን በመጥቀስ ይቃወምና መለስ ብሎ ደግሞ “ትጥቅ አልፈታም፣ ፈቱም መባል አልፈልግም” ሲል ይደመጣል።
ዳውድ በሰሞነኛው መግለጫቸው በመንግሥትና በኦነግ መካከል በተደረገ ሥምምነት ጦርነት ማለቁን ግልጽ አድርገውና በጋራ መግለጫ ሰጥተው ወደ አገር ቤት መግባታቸውን አስታውሰዋል። በአንፃሩ አሁንም በትጥቅ ትግል ያሉ የኦነግ ታጣቂ ሠራዊት አባላት በብዙ አካባቢዎች እንዳሉም ግልጽ አድርገዋል።
ከዚህ በፊት ያለው የመንግሥት ሠራዊት ሳይሆን የኢሕአዴግ ሠራዊት ነው የሚል አቋም ያላቸው ዳውድ “በእኛ በኩል ያለው ደግሞ በመንግሥት የፀጥታ ኃይል ውስጥ እንዴት አድርጎ ‘ኢንተግሬትድ’ እንደሚያደርግ ተሞክሮ ያላቸው ዕርዳታ አድርገውልን፣ ሁለታችን ኦነግና መንግሥት ይኼ እንዴት እንደሚፈፀምና እንዴት እንደሚሆን መክረናል። አገር ቤት ስንገባ ኮሚቴ አቋቁመን ተፈፃሚ እንደምናደርገው ተስማምተን ነው የመጣነው” ይላሉ።
መንግሥትም ሆነ ኦዴፓ በአንድ አገር ሁለት መንግሥት ሊኖር ስለማይችል ኦነግ የታጠቀ ሠራዊት ሊኖረው አይገባም፣ በአስመራው ሥምምነት ስለ ትጥቅ መፍታት አልተወራም፤ ምክንያቱ ደግሞ ትጥቅ መፍታት ግዴታና ለድርድር የማይቀርብ ቀይ መሥመር ስለሆነ ነው የሚል መግለጫን መስጠታቸው አይዘነጋም።
እዚህ ላይ ግን ሊታይ የሚገባው አሁን ያለው የፀጥታ ኃይል የፓርቲ እንጂ የመንግሥት አይደለም፤ የአገር ሠራዊቱ ከፓርቲ አስፈፃሚነት መላቀቅ አለበት ብሎ የሚያምነው ኦነግ፥ የእኔ ሠራዊት ይካተትልኝ ማለቱ ምን ያክል ተገቢ ነው የሚለው ነው። ምክንያ ቱም የኦነግ ሠራዊት የሚቆመው ለኦነግ ነውና። ታኅሣሥ 11 የፀደቀው የመከላከያ ሠራዊት ማሻሻያ አዋጅ የሠራዊት ምልመላ፣ ቅጥርና አደረጃጀት ግልጽነት ያለውና የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ሚዛናዊ ተዋፅዖ ያካተተ እና ከፖለቲካ ወገናዊነት ነጻ ሆኖ እንዲደራጅ የሚያሳስብ መሆኑ ይታወቃል።
በሁለቱ ፓርቲዎች መካከል የነበረውን ሥምምነት ማየት ያስፈልጋል የሚሉት የሕግ ባለሙያው ሰለሞን ጎሹ ሁለት ፓርቲዎች ስለ መንግሥት መዋቅር ሊወስኑ እንደማይችሉ ይናገራሉ። በአገር የፀጥታ ኃይል መዋጮ ላይ ሁለት ፓርቲዎች ሥምምነት ይፈራረማሉ ብለው እንደማያምኑ የሚገልጹት ሰለሞን ‘‘ቢፈራረሙ እንኳን ተቀዶ ከመጣል ያለፈ ዕጣ ፈንታ አይኖረውም’’ ይላሉ።
በሌላ በኩል ታጥቆ የገባ ፖለቲካ ፓርቲ ሠራዊት የለም የሚለውን የጠቅላይ ሚንስትሩ መግለጫ ማመኑ እንደሚሻል ይመክራሉ። ይሁንና ኦነግ በይፋ አገር ውስጥም የኖሩ ታጣቂዎች እንዳሉትና ሰሞነኛው ግጭትም ኦነግ ነጻ አውጥቸዋለሁ በሚለው አካባቢና የግንባሩ ታጣቂዎች በሚገኙበት ሥፍራ የመከላከያ ሠራዊት በመሥፈሩ የተነሳ ነው ስለሚለው የዳውድ መግለጫ ሰለሞን “የፖለቲካ ፓርቲ ወታደርና ነጻ የሚያወጣው መሬት ሊኖረው አይችልም” ይላሉ። ይህ መግለጫ በራሱ “ወንጀለኛ ነኝ” ማለት እንደሆነም ያነሳሉ። ይህንንም ወንጀል የሚያደርጉ በርካታ ሕጎች ስለመኖራቸው ያክላሉ።
ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ በባሌ፣ ሰላሌ፣ ጉጂና ምሥራቅ ወለጋ ግጭቶች እንደነበሩ መግለጫ የሰጡት ዳውድ “ዋነኛው ውጊያ ግን በሥፋት ያለው ምዕራብ ወለጋ ነው” ማለታቸው ይታወሳል። ውጊያውም በኦነግ ሠራዊትና የመንግሥት ኃይል (መከላከያ ሠራዊት) መካከል ስለመሆኑ ተጠቅሷል። ዳውድ “ለውጊያው” ምክንያት ካሏቸው መካከል የመከላከያ ሠራዊት የኦነግ ታጣቂዎች ባሉበት አካባቢ በተለይም በምዕራብ ወለጋ መሥፈሩን ነው። ከጥቂት ሳምንት በፊት በቤንሻንጉልና ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች የሰው ሕይወትን እየቀጠፉ የመጡ ተደጋጋሚ ግጭቶች መከሰታቸውን ተከትሎ ሁለቱ ክልሎች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት የፌደራል ፀጥታ ኃይል ጣልቃ እንዲገባና በአካባቢዎቹ ሰፍሮ እንዲያረጋ መወሰኑ ይታወሳል። በኦነግ የመከላከያ ኃይል አካባቢው ላይ መሥፈሩን ተከትሎ ግጭት ሊነሳ ችሏል የሚለው ምክንያት ግን በሕግ በሚተዳደር አገር ውስጥ ይቻላል ወይ የሚለው በራሱ ጥያቄ ነው፣ “ኦነግ ተኩስ አቁም ካወጀበት ቀን ጀምሮ የኦነግ ሠራዊት አንድም ቀን በራሱ ተነሳሽነት ተኩስ ከፍቶ እንደማያውቅ” የገለጹት ዳውድ፣ ሌሎች ተኩስ ሲከፍቱበት ግን ራሱን እየተከላከለ ስለመሆኑ ነው ያነሱት፤ “የኦነግ ሠራዊት የሚሰነዘርበትን ጥቃት” እንዲከላከል መመሪያ እንደወረደለትም በዳውድ መግለጫ ላይ ተነስቷል።
ኦነግ በታኅሣሥ 12/2011 መግለጫው በመጪው ዓመት ምርጫ እንደሚሳተፍም ተናግሯል። ለመሆኑ ኦነግ እንዴት ‘ተፎካካሪ ነኝ፤ በምርጫም እሳተፋለሁ’ እያለ፥ በሌላ ጎኑ ደግሞ የታጠቀ ሠራዊት እንዲኖረው ይፈቀድለታል የሚለውን ግን በወጉ መመለስ ይፈልጋል። እዚህ ላይ በፌደራሉ መንግሥትም ይሁን በኦሮሚያ ክልል በኩል “ትጥቅ አንግቦ ሠላማዊ ትግል” የሚባል ነገር የለም ከሚል በዘለለ በግልጽ ወጥቶ መፍትሔ የተሰጠው ጉዳይ አይደለም። ይህም የፌደራሉን መንግሥት እያስተቸው ነው፤ “ሌላው ፓርቲ ትጥቅ ፈትቶ እንዲገባ ሲደረግ፣ ኦነግ እንዴት ነው ከእነትጥቁ እንዲገባ የሚፈቀድለት” የሚሉ የተቃውሞ ጥያቄዎች በየማኅበራዊ መገናኛ አውታሮችም ሲንሸራሸሩ ይስተዋላል። በኦሮሚያ ክልልና በኦዴፓ በኩል በተደጋሚ ሲሰጡ ከነበሩት ምለሾች መካካል አንዱ ከውጭ የገቡት ትጥቅ በፊቱም አገር ውስጥ የነበሩት ስላልፈቱ ነው፣ እነዚህም ቢሆኑ ትጥቃቸውን በአስቸኳይ ይፈታሉ የሚሉ መግለጫዎች ይገኙበታል።
ለአብነትም ጠቅላይ ሚንስትሩ የመከላከያ ሠራዊት አባላት አግባብ ባልሆነ መንገድ ወደ ቤተመንግሥት ገብተው በነበረበት ዕለት መግለጫ ሲሰጡ ከጋዜጠኞች በኩል ተያይዞ ለተነሳላቸው የኦነግ “ትጥቅ አልፈታም” ውዝግብ “ኦነግ ትጥቅ አልፈታም ይላል ብዬ አላስብም፤ ምናልባት የአፍ ወለምታ እንዳይሆን መልሶ ‹ቼክ› ማድረግ ያስፈፈልጋል። ትጥቅ ለማንኛውም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አያስፈልገውም፤ የሚስፈፈልገው ትጥቅ የሐሳብ ትጥቅ ነው።… እኛ እኮ ጥሪ ያደረግነው ፋሽኑ አለፈበት አንገዳደል ብለን ነው፤ ትጥቅ ያልፈታና ይዞ የገባ ተፎካካሪ ፓርቲም የለም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ሕገ ወጥ ትጥቅ በጣም ብዙ ነው።… በምናወጣው ሕግ ትጥቅ መፍታት ያስፈልጋል” ብለው ነበር።
ታኅሣሥ 11 የኦዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሠላማዊ መንገድ ትልግ ለማድረግ የተገባው ቃል እየፈረሰ መሆኑን አሳውቆ “ኦዴፓ ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት እያሳየ ያለውን ትዕግስት እንደ ፍራቻ በመመልከት ሲዘርፉና ሲያሰቃዩ የነበሩ እንዲሁም ከሥልጣን የተባረሩ ወገኖች ተላላኪዎችን በመግዛት ኦሮሚያን እና ኦሮሞን የጦርነት አውድማ ለማድረግ እየሠሩ ነው” ሲል መውቀሱ ይታወሳል።
ሕዝቡ በሠላም ወጥቶ እንዳይገባ እየተደረገ ስለመሆኑ አንስቶም ለሕዝብ የሚጠቅሙ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እንዲቆሙ፣ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ ገበያም እንዲቆም ስለመደረጉ አንስቷል።
የደቦ ፍርድ እየነገሰና ዜጎች እየተገደሉ መምጣታቸውን ያመለከተው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጥፋቱ ከዚህ በላይ ከቀጠለ የሕዝብ እልቂትና የአገር መበተን ስለሚከተል የወንጀል ተሳታዎችን በማደን ለሕግ የማቅረቡ ሥራ በአስቸኳይ እንዲፈፀም አቅጣጫ ማስቀመጡን ማሳወቁም አይዘነጋም። ይሁንና በማግሥቱ መግለጫ የሰጡት ዳውድ የኦዴፓ መግለጫ “የጦርነት አዋጅ” ይመስላል ካሉ በኋላ መንግሥት ቸኩሎ እርምጃ በመውሰዱ ግጭቶቹ መቀስቀሳቸውን ተናግረው ነበር። ዳውድ መንግሥት ለእርምጃ ቸኩሏል ይበሉ እንጂ ኦዴፓ በአንፃሩ “የትዕግስቴ ብዛት እንደፍራቻ ተቆጥሮብኛል” ሲል ነው የገለጸው።
ሰኞ ታኅሣሥ 15 መግለጫ የሰጡት የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ዓለማየሁ እጅጉ ላለፉት ስድስት ወራት ችግሮችን በመነጋርና ሠላማዊ መንገድ ለመፍታት ጥረት ቢደረግም የበለጠ ዋጋ አስከፍሏል ብለዋል። በምዕራብ ኦሮሚያ ባጋጠሙ ግጭቶች ባለፉት አራት ወራት ብቻ የዞን መምሪያ ኃላፊዎችንና ፖሊሶችንና ጨምሮ 41 (12 ፖለሲሶች ናቸው) ንፁኃን መገደላቸውን በመጥቀስም ተጠያቂዎቹ የኦነግ ሠራዊቶች ናቸው ሲሉ ከሰዋል። የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ግን ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ ባለፈው ኅዳር 18 በቄለም ወለጋ በተፈጠረ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ተገድለዋል፤ ሲል ኦሮሚያ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ባወጣው መግለጫ ደግሞ በርካቶች ሞተዋል በሚል ቁጥሩን በቅርቡ አሳውቃለሁ ሲል ነበር ያለፈው። ኮሚሽነሩ የኦነግ ታጣቂዎች የመንግሥትን ሁለት ሺሕ 72 ጠመንጃዎችና ከሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብን ከመንግሥት ካዝና ዘርፈዋልም ብለዋል። ከባንኮች የተዘረፈውም በርካታ መሆኑን አሳውቀዋል። ዳውድ ባለፈው ሳምንት የክልሉ መንግሥት ለውይይት ክፍት ከሆነ በሠላም ለመነጋገር ዝግጁ እንደሆኑ መናገራቸው ይታወሳል። ኮሚሽነሩ እንደሚሉት ከሆነ ደግሞ ኦነግ ከኦዴፓ አመራሮች ጋር በሚያደርገው ውይይት በሠላም ለመታገል ቢስማማም በተግባር ግን ታጣቂዎቹ ችግር እየፈጠሩ ነው።
ኮሚሽነሩ በኦሮምኛ “አባ ቶርቤ” የተባለ እና ወደ አማርኛ ሲመለስ “ባለሳምንት” የሚል ትርጉም የሚሰጥ ሥያሜ ያለው፣ በየጊዜው የሰው ሕይወት ሲያጠፋ የነበረ ነፍሰ ገዳይ ቡድን አለ ያሉ ሲሆን የቡድኑ አባላት በቁጥጥር ሥር እየዋሉ እንደሆነም አንስተዋል። ይህ ቡድን በዳውድ ከሚመራው ከኦነግ ጋር ግንኙነት የነበረውና ትዕዛዝ እየተቀበለ ይፈፅም የነበረ ነውም ተብሏል።
የኦነግ ሠራዊት ለዳውድ ይታዘዛል?
በምዕራብ ኦሮሚያ እየከረረ የመጣውን የኦነግና ኦዴፓ ተቃርኖ የተመለከቱ አካላት የኦነግ ሠራዊት የሚባለው ራሱ ለኦነግ መሪው ዳውድ እንደማይታዘዝ ይገልጻሉ። ዳውድ የኦነግ ሠራዊት የሚሉት ስላልታዘዘላቸው የትጥቅ ማስፈታትንም ሆነ የተኩስ አቁም ሥምምነትን ተግባራዊ ለማድረግ እንደተቸገሩ መላ ምታቸውን የሚያስቀምጡ አሉ። የዚህ መላ ምት መነሻ ደግሞ የምዕራብ ኦሮሚያ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ሠራዊት አዛዥ ነው የሚባለው ኩምሳ ድሪባ ነው።
ኩምሳ በ1996 የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የማኔጅመነት ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ በነበረበት ወቅት ያጋጠመው ሁነት (በተማሪዎች ዲን ጽሕፈት ቤት ፊት ለፊት የተነሳ ተቃውሞ) ዛሬ በምዕራብ ኦሮሚያ ላለው ነገር መሠረት መሆኑ ይጠቀሳል። በቅርቡ “medium” በተሰኘ የበይነመረብ ጡመራ መድረክ ላይ “Who is Kumsa Diriba?” በሚል የወጣ ጽሑፍ እንደሚያትተው፥ ኩምሳ የመጀመሪያ ዓመት ተማሪ በነበረበት ወቅት በ6 ኪሎ ግቢ በተነሳ ግጭት ለአንድ ቀን ታስረው ከተፈቱ ስምንት ተማሪዎች መካከል አንዱ ነበር። ኢሰመጉ በ6 ኪሎ ተፈጥሮ ስለነበረው አለመግባባት ሪፖርት ባወጣበት የአውሮፓዊያኑ የካቲት 10/2004 (74ኛ ልዩ ሪፖርት) አሁን ላይ ኩምሳ ድሪባ ወይም በትግል ሥሙ ጃል መሮ (ጓድ መሮ) የሚባለው በወቅቱ ከታሰሩት መካከል አንዱ እንደነበር ያሳያል። የወቅቱ የትምህርት ቤት ሥሙም ሚሊዮን ድሪባ እንደነበር ነው የተገለጸው።
በ1998 በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙ የኦሮሞ ተወላጅ ተማሪዎች “Fincilaa Diddaa Gabrumma-FDG” (‘ጭቆና የመመከት ትግል’) የሚል ዘመቻ መጀመራቸውን ተከትሎ ሚሊዮን ድሪባ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አማካኝነት በቦረና ዞን ሥልጠና እንዲወስዱ ከተደረጉት መካከል መሆኑንም ጽሑፉ ያትታል። ከሥልጠናው በኋላ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ “Qeerroo Bilisummaa Oromia” (‘የወጣቶች ኅብረት ለኦሮሚያ ነጻነት’) የተሰኘውን ድብቅ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ቡድን የተቀላቀለው ኩምሳ በመንግሥት በኩል በነበረ ጫና ወደ ቦረና ተመልሶ በይፋ የኦሮሞ ነጻነት ጦር ሠራዊት አባል መሆኑን መረጃው ያመለክታል።
ይሁንና የመንግሥት ፀጥታ ኃይል በአካባቢው እያየለ መምጣቱን ተከትሎ ኩምሳ ወደ ኡጋንዳ እንደተሰደደ የሚያትትው ጽሑፉ፣ በዚያም የኢትዮጵያ መንግሥት ተላልፎ እንዲሰጠው ቢጠይቅም ኡጋንዳ ጥያቄውን አለመቀበሏንና ይልቁንም ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ብቻ እንዲታሰር ማድረጓም ተጠቅሷል። ኋላም የኦነግ የበላዮች ወደ ነበሩባት ኤርትራ ማቅናቱን የሚያትተው ጦማር በእስር ላይ እያለ የኦነግ ሠራዊት የምዕራቡ ግንባር ኮማንደር ጃል ለገሰ ወጊ በመገደሉ “በመበተን ላይ ያለውን የግንባሩን ሠራዊት ማደራጀት አለብኝ” በሚል በአውሮፓዊያኑ 2010 ወደ ኢትዮጵያ መመለሱን ይገልጻል። ለዓመታት ግንባሩን ሲያደራጅ እንደነበር የሚነገርለት ኩምሳ የቢሾፍቱውን የኢሬቻ አደጋ ተከትሎ ብዛት ያላቸው የቄለም ወለጋ ወጣቶች ግንባሩን እንዲቀላቀሉት ምክንያት እንደሆነለትም ያትታል።
ይሁንና በዚህ አግባብ የተጠናከረው ግንባር አዛዥ ነው የሚባለው ኩምሳ በኦነግና ኦዴፓ መካከል ኤርትራ ላይ የተደረሰውን ሥምምነት እንደሚቃወመው ተነግሯል። ይህን አብነት የሚያ ደርጉ ተንታኞችም በምዕራብ ወለጋ ያለው የኦነግ ሠራዊት ለዳውድ ኢብሳ እንደማይታዘዝ ይገልጻሉ።
በተያያዘም ዳውድ የክልሉ መንግሥት ዝግጁ ከሆነ በሠላም ለመታገልና ለመወያየት ዝግጁ እንደሆኑ ይግለጹ እንጂ ኩምሳ (ጃል መሮ) ባለፈው ሳምንት ባወጣው የ48 ደቂቃ በኦሮምኛ ቋንቋ የተደረገ ንግግር ሠላማዊ ትግል ብሎ ነገርን በፍፁም መስማት እንደማይፈልጉ ገልጿል። በንግግሩ ‘ሕዝቡ ራሱ ነጻ ወጥቻለሁ፤ መሣሪያ አልፈልግም ቢል እንኳን የጫካ አራዊትን ነጻ ለማውጣት እስከመታገል’ እንደሚደርስ ግልጽ አቋሙን ያንፀባረቀው መሮ ትጥቅ ፍቱ የሚባለውን እንደማይቀበሉም አሳውቋል። በንግግሩ ‘የኦነግ የበላዮች ከፈለጉ ራሳቸው በሠላማዊ መንገድ መታገል’ እንደሚችሉ አክሎ ከዚህ በኋላ ለእነሱ እንደማይታዘዝና በእርሱ ላይ ማንም የበላይ እንደማይሆንም ዝቷል።
የኦዴፓና ኦነግ ኮሚቴ ምንድነው?
ኦዴፓና ኦነግ ቀድመው ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የመጠላላፍና መወነጃጀል ልምድ እንዲቀር የሚለው አንዱ ነው። ሌላው ኦነግ ሠራዊት አለኝ ማለቱን ተከትሎ ሠራዊቱን መንግሥት ሊረከብና በአቅማቸው፣ ፍላጎታቸውና ችሎታቸው የሥራ ድልድል አድርጎ ወደ ሥራ ሊያሰማራቸው፣ ኦነግም በሠላማዊ መንገድ እንዲታገል መሆኑ ተገልጧል። ይህንን የሚያስፈፅም ኮሚቴም ከሁለቱ ፓርቲዎች ሦስት፣ ሦስት አባላት ተመርጠው ኅዳር 16 ወደ ሥራ መግባታቸው ተጠቅሷል። በኮሚቴው የኦዴፓ ተወካይ ሞገስ ኤደኦ እንደሚሉት ኦነግ ሠራዊቱን ከኅዳር 20 እስከ ታኅሣሥ 5 አወያይቶ እንዲያሳምን ዕቅድ ቢወጣም አልፈፀመውም። ኦዴፓ ትጥቅ ፈትተው ከገቡት መካከል ሥልጠና ወስዶ በፖሊስ አባልነት መቀጠል የሚፈልጉትን ጨምሮ በሌሎች የመንግሥትና የግል ሥራ መሠማራት ለሚፈልጉት ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አሳውቋል። በተቃራኒው ኦነግ በምዕራብ ኦሮሚያ ተጨማሪ አዳዲስ ታጣቂዎችን የመመልመልና የማሠልጠን ሥራን ሲሠራ ነበር ሲሉም ሞገስ ይወቅሳሉ። ኦነግ በበኩሉ ከሥምምነቱ በፊት ወደ ሥልጠና የገቡ እንጂ አዳዲስ ምልምሎች አይደሉም የሚል ምላሽ መስጠቱን የሚያክሉት ሞገስ ኦዴፓ (መንግሥት) ግን ኦነግ አንደኛ ዙር ሥልጠና ገብተው የወጡ እና አሁን ሁለተኛ ዙር ሥልጠና ላይ ያሉ አባላት እንዳሉት መረጃ እንዳላቸው ይገልጻሉ።
በኮሚቴው ዕቅድ መሠረት የጋራ መግለጫ መሰጠት በነበረበት ታኅሣሥ 16 የኦነግ ተወካይ ባለመገኙቱም ኦዴፓ ብቻ በመድረኩ ተገኝቶ ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫን ሰጥቷል።
ይሁንና በዚሁ ዕለት የጽሑፍ መግለጫን በይፋዊ ገጹ ያሰፈረው ኦነግ “አግባብነት የሌለው መንገድ ወደ መፍትሔ አያመራንም” ሲል ይጀምራል።
በኦነግ፣ በኢትዮጵያ መንግሥትና በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት መካከል ከተደረሱ ሥምምነቶች ውስጥ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ተግባራዊ በማድረጉ ሒደት ላይ የሚሠራ የጋራ ኮሚቴ መዋቀሩን በመግለጽ ለማ መገርሳና ዳውድ ኢብሳ የኮሚቴውን ሥራ በበላይነት የሚከታተሉት መሆኑንም መግለጫው ያትታል። ኮሚቴው ሥራውን ሲያጠናቅቅ ለሁለቱ አመራሮች አቅርቦ በጋራ ውሳኔ እንደሚሠጡበት በመጥቀስም “የዚህን ኮሚቴ የሥራ አፈፃፀምና ውጤት በተመለከተ ለሕዝቡ መረጃም ሆነ ማብራሪያ መስጠት ትክክለኛ፣ ተገቢና ውጤታማም የሚሆነው ከላይ የተገለጹትን የአሠራር ሒደትና ቅደም ተከተሉን ጠብቆ ሥራው ሲጠናቀቅ ብቻ ነው” ይላል። በመሆኑም ሥራው እልባት ላይ ሳይደርስ በአንድ ወገን መግለጫ ብቻ ዘገባ መሥራትንም ይኮንናል። ይሁንና አዲስ ማለዳ ይህን ሐተታ ጽሑፍ በማዘጋጀት ሒደት ከሰኞ ታኅሣሥ 15 ጀምሮ የኦነግ አመራሮችን ለማግኘት ያደረገችው ጥረት አልተሳካም።
ዳውድ እና ከማል
ኦነግ ከሥምምነቱ ውጭ በክልሉ የመንግሥት መዋቅር ‹እከሌን ለምን ሾማችሁ? የሾማችሁት ሰው እንዲህ ተናግሯል› በሚል ክርክር እየገጠመ እንደሆነ የሚነሱት ሞገስ ትጥቅ አስፈትቶ ወደ ካምፕ ለማስገባት ‹የኦነግ አመራር ቤትና መኪና አልተሰጠውም፣ ቢሮው ዘግይቶ ነው የተፈቀደለት› የሚሉ ምክንያቶችን እየደረደረ ነው ሲሉም ወቅሰዋል። የዳውድ ኢብሳ ቅሬታ ከማል ገልቹ የኦሮሚያ ክልል የፀጥታ አማካሪ ሆነው መሾም በስርዓቱ መለወጥ ላይ አጠራጣሪ ስለሆነባቸው እንደሆነ ገልጸዋል።
ከማል ገልቹ ከዚህ ቀደም 150 ያክል ወታደሮችን ይዘው የኮበለሉ ጄኔራል ሲሆኑ፣ ኤርትራ የነበረውን የኦነግ ሠራዊት ከተቀላቀሉ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ በእስር እና በቁም እስር እንዲቆዩ ከዚያም ከኤርትራ ምድር እንዲወጡ የተደረጉ መሆናቸው ይታወሳል። በዚህም በሁለቱ የጦር መሪዎች መካከል የከረመ ቁርሾ የነበረ ሲሆን፣ አሁን የከማል ገልቹ የክልሉ የፀጥታ ጉዳዮች አማካሪ ሆኖ መሾም ዳውድ ኢብሳ ላይ የሥነ ልቦና ጫና ያሳደረባቸው ይመስላል።
ኦነግ ቅቡልነቱ እንዳለ ነውን?
በኦሮሚያ በተለይም ምዕራቡ ክፍል እያጋጠመ ካለው ግጭት ጋር ተያይዞ ችግሩ ያለው በማን በኩል ነው የሚለውን ሐሳብ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን አውታር በተለይም የፌስቡክ ተጠቃሚዎች ሐሳባቸውን እንዲያጋሩ የሚጠይቅ የበይነ መረብ ድምጽ መሰብሰቢያ ሰሞኑን በተለያዩ ሰዎች አማካይነት ሲንሸራሸር ተስተውሏል።
ቅዳሜ ታኅሣሥ 13 የጀመረውን ድምፅ መሰብሰቢያ በገጻቸው ከስቀመጡ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች መካከል በፍቃዱ ዘ. ኃይሉ አንዱ ሲሆን “ባልዎት መረጃ ወይም አስተያየት፣ ኦሮሚያ ውስጥ ያለውን ግጭት በተመለከተ ኃላፊነት የጎደለው ሥራ እየሠራ ያለው ከእነዚህ ሁለቱ የትኛው ድርጅት ነው?” ሲል ኦዴፓንና ኦነግን ለምርጫ አቅርቧል። እስከ ረቡዕ ድረስ ከተሰጠው ከአራት ሺሕ አንድ መቶ ድምፅ ሰጪዎች ውስጥ “ኦነግን” ተጠያቂ ያደረጉት 83 በመቶዎቹ ናቸው። ፈርሃን አብዱልሠላም የተባሉ ግለሰብም በኦሮምኛ ላቀረቡት ተመሳሳይ ጥያቄ ከሦስት ሺሕ አንድ መቶ በላይ ድምፅ ሰጪዎች ተሳትፈው 75 በመቶዎቹ ኦነግን ወቅሰዋል። በተመሳሳይ፣ ግርማ ጉተማ የተባሉ ግለሰብም ዳወድ ኢብሳ በኦኤምኤን ላይ ቀርበው የፖለቲካ ድርጅታቸው ተወዳጅ ስለሆነ ብቻ ከመንግሥት በኩል ከፍተኛ ጫና እንደሚደርስበት መናገራቸውን በመጥቀስ በእርግጥ ዳውድ እንደሚሉት የችግሩና ግጭቱ መነሻ ይኼ ይሆን የሚል ጥያቄን አስፍሯል። ለዚህም በ16 ሰዓታት ውስጥ ያገኙት ምላሽ ከአንድ ሺሕ 400 በላይ ሰዎች ድምፅ መካከል የ72 በመቶዎቹ “አይደለም” የሚል ነው።
ሦስቱም ሰዎች የሚሰበስቡት ድምፅ የመስጠቱ ሒደት እንደቀጠለ ቢሆንም ውጤቱ በመቶኛ ሲሰላ ከዕለት ዕለት ተመሳሳይ ሁኖ ቀጥሏል። ይሁንና እንዚህን ማሳያዎች መሠረት አድርገው ትንታኔ የሚጽፉ ሰዎች ለግጭቶቹ ኦነግን ጥፋተኛ የሚሉት እየበዙ ስለመምጣታቸው እና “ኦነግ በፊት የነበረውን ቅቡልነትና ተደማጭነት እያጣ የመምጣቱ ምልክት ይሆን?” ሲሉ ይጠይቃሉ።
መፍትሔው ምን ይሁን?
ከዚህ ቀደም ባለው ጊዜ አንዳንድ የፖለቲካ ፖርቲዎች ከሊቀ መንበራቸው ወይም ፕሬዘዳንታቸው ውጭ የሚታወቅ ነገር እንዳልንበራቸውና ምርጫ ቦርድ የሚያወጣቸውን ሕጎችና የየራሳቸውን መመሪያዎች አክብረው በመንቀሳቀስ በኩል ብዙ ክፍተት እንዳለ ይነሳባቸዋል። ስለዚህ ጉዳይ ሰለሞን ሲያብራሩ አሁን ያለው መንግሥት የተለያዩ የሕግ ማሻሻሻያዎችን እያደረገ እንደሚገኝ በመጥቀስ በቀጣይ በሚወጡ ሕጎች ያሉት ችግሮች እየተፈቱ እንደሚሔዱ ያምናሉ። ይሁንና ከዚህ ቀደም ሕጎችና ስርዓቶች እንደነበሩ መዘንጋት የለበትምም ይላሉ።
የፌደራሉ መንግሥት “ብዙ ትዕግስት ማብዛት አያስፈልገውም” የሚሉት የሕግ ባለሙያው ሰለሞን የወንጀልና የፀጥታ ጉዳይ የፌደራል መንግሥቱ ስለሆነ ሕጎችን ማስፈፀም እንዳለበት ይመክራሉ። ጎን ለጎንም እየተግባቡና ይቅር የሚባለውንም እያሉ መሔድ አስፈላጊ እንደሆነ ይመክራሉ። ፀጥታና ሠላምን አረጋጋቶ የተጀመሩ ማሻሻያዎችን ሁሉን አሳታፊና አካታች በሆነ መንገድ ማስኬድም መዘንጋት እንደሌለበት ያነሳሉ። ሁሉን ነገር ክፍት አድርጎ ግን ሁሉም በመሰለው እንዲሔድና የፈለገውን እንዲወስን መፍቀድ ተገቢ አለመሆኑን ያክላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here