“አዲስ ተቀጣሪ የመንግስት ሰራተኛ ስራ ከመጀመሩ በፊት ሀብት የማስመዝገብ ግዴታ አለበት”

0
727

የፌደራል የስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን

በ2013 በጀት ዓመት ማንኛውም አዲስ የመንግስት መስሪያ ቤት ተቀጣሪ ስራ ከመጀመሩ በፊት ሀብት የማስመዝገብ ግደታ አንዳለበት የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው ከዚህ በፊት የነበረው የመንግስት ተመራጭና ተሿሚ በሚል ተገድቦ የነበረው የሀብት ማስመዝገብ ግዴታ በ2013 በጀት ዓመት አንደማይሰራ ገልጿል።በመሆኑም ሁሉም የመንግስት ሰራተኛ ተመራጭ፣ ተሿሚና አዲስ ተቀጣሪ ያለውን ሀብት ሳያሳውቅ ስራ መጀመር አይችልም ብሏል።
የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሀብት ምዝገባና ማሳወቅ ዳይሬክተር መስፍን በላይነህ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ በሀብት ምዝገባ ስርዓት ለማስቀረት የታሰበውን የሙስና ምዝበራ ወንጀል በመንግሰት ተሿሚዎች ብቻ ከተገደበ ውጤታማ ሊሆን እንደማይችል ጠቁመዋል።ዳይሬክተሩ አክለውም ከመንግስት መስሪያ ቤት አሰራር ስርዓት ውስጥ ስራዎች የሚከወኑት መጀመሪያ በባለሙያና ከተሿሚ ስር ባሉ ሰራተኞች ስለሆነ ቁጥጥሩ ከስር መሰረቱ መሆን ይገባዋል ሲሉ ገልጸዋል።

ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት አዲስ ተቀጣሪ የመንግስት ሰራተኛ የመጀመሪያ ደምወዙን ከመውሰዱ በፊት የሀብትና የገቢ ምንጩን ሳያሳውቅ ስራ መጀመር አንደማይችል ተናግረዋል።ይሄን ለማስፈጸም መመሪያ መዘጋጀቱንም ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።

ሀብትን ከማስመዝገብ ግዴታ ጋር ተያይዞ ፈቃደኛ ሆኖ ያልተገኘ ሀብት የማስመዝገብ ግዴታ ያለበት አካል በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠባቂነት ሙስናን እና ብልሹ አስራርን ለመከላከል በወጣው የሀብት ማሳወቅና ማስመዝገብ አዋጅ ቁጥር 668/2002 መሰረት በህግ ተጠያቂ እንደሚደርግ ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም በአዋጁ መሰረት ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተው የተሰጣቸው ጊዜ ገደብ በመጠናቀቁ አስፈላጊው እርምጃ ተወስዶ አንድ ሺህ(1000) ብር ተቀጥተው ሀብታቸውን እንዲያስመዘግቡ የሚደረግበት የህግ አግባብ መኖሩን አመላክተዋል።

በሌላ በኩል ኮሚሽኑ በ2013 በጀት አመት የጥቅም ግጭትን ለመከላከል በከፍተኛ ትኩረት እየሰራ እንደሆነ መስፍን ጠቁመዋል።በዚህም የመንግስት ሰራተኛ የሆነ ሰው በግል የሚሰራው ሰራ ከሚስራው ጋር በቀጥታንም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚገናኝ ከሆነ አንዱን መምረጥ አንዳለበት መስፍን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
መስፍን እንደሚሉት ለምሳሌ በንግድና ኢንዱስትሪ መሰሪያ ቤት ውስጥ የሚሰራ የመንግስት ሰራተኛ በንግድ ዘርፍ ከተሰማራ ወይ የመንግስት ሰራውን ወይ ደግሞ የግል ስራውን መምረጥ ይኖርበታል ብለዋል።

ይህ የሆነትን ምክንያት መስፍን ሲያስረዱ የሀብት ምዝገባ አዋጅ ላይ የተቀመጠው ህግ በንግድ ስራ ላይ ተሰማራ የመንግስት ሰራተኛ አሰራሩን ለራሱ ንግድ ስራ በሚመች መልኩ ሊመራው ይችላል የሚል እሳቤ እንደተቀመጠ ጠቁመዋል።“ህጉ ማንኛውም የመንግስት ሰራተኛ ከሚሰራው ስራ ጋር የጥቅም ግጭት የሚፈጥር ስራ መስራት የለበትም” ሲሉ መስፍን አስረድተዋል።

ኮሚሽኑ ይሄን ስራ በ2013 በትኩረት የሚሰራው የጥቅም ግጭትን ለማስቀረት ሲባል መሆኑን የኮሚሽኑ የሀብት ምዝገባ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የፌደራል ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሀብታቸውን ለማስመዝገብ ፈቃደኛ ያልሆኑ 184 የፌደራል እና የአዲስ አበባ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለሰልጣናትን ለጠቅላይ አቃቢ ህግና ለፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጉዳያቸውን እንዲጣራና ክስ እንዲመሰረትባቸው ማስተላለፉ የሚታወስ ነው።በዚሁ መሰረት የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ በተላለፈለት ዝርዝር ላይ ምርመራ አካሂዶ ክስ እንደሚመሰርት አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 98 መስከረም 9 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here