በኮቪድ-19 መከሰት ለግማሽ ዓመት ተቋርጦ የቆየው የመማር ማስተማር ስራ ትምህርት ቤቶቹ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው በ3 ሳምንታት ውስጥ ትምህርት እንዲጀምሩ ተወሰኗል፡፡
የዓለም የጤና ድርጅትና የጤና ሚኒስቴር ወረርሽኙን ለመከላከል ባስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ መሰረት ትምህርት ቤቶች ከመከፈታቸው በፊት በመድሃኒት ማፅዳት፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብልና የእጅ ማፅጃ ማሟላት እንዲሁም አካላዊ ርቀትን ማስተግበር ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
እንደየ ትምህርት ቤቶቹ ነባራዊ ሁኔታ ትምህርት በፈረቃ እና አንድ ቀን በመዝለል ተራ ሊያስተምሩም ይችላሉ፡፡ ትምህርት ሚኒስቴር ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት በአንድ ክፍል ውስጥ ከ20 እስከ 25 ተማሪ ማስተማር የሚችሉ መሆንም ይጠበቅባቸዋል ተብሏል፡፡
ከተቀመጡት መስፈርቶች በተጨማሪ በገጠር ወረዳና ቀበሌ ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመጀመሪያው ዙር ጥቅምት 9/2013፣ በሁሉም የዞንና የክልል ከተሞች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በ2ኛ ዙር ጥቅምት 16/2013፣ በአዲስ አበባና አዲስ አበባ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ደግሞ በ3ኛ ዙር ጥቅምት 30/2013 ትምህርት እንዲጀምሩ ምክረ ሀሳብ ቀርቧል፡፡
ቅጽ 2 ቁጥር 99 መስከረም 16 2013



