ይህ አባባል ከሰሞኑ በማኅበራዊ የመገናኛ ትስስር ገጾች ብዙዎች ሲቀባበሏቸው ከሰነበቱ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው፡፡ ‹‹ሁላችንም ዘር አለን›› ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሊቀ መንበሩ በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር) ናቸው፡፡
‹‹ሁላችንም ዘር አለን፡፡ ዘሩ ግን እኛ አይደለንም! እኛ ሰዎች ነን፡፡ ሰውነት ከመፈጠር እንጂ ከመወለድ አይጀምርምና ፈጣሪ ዘራችንን ኢትዮጵያ በምትባል ምድር ላይ ዘራው፡፡ ሲዘራው ኢትዮጵያ ማለት ሰዎች መሆኗን አወቅን›› ያሉት ሊቀመንበሩ አሁን ላይ ግን በሕንድ 2032 ብሔረሰብ፣ በቻይና 499 ብሔረሰብ በሠላም እየኖረ ምነው እኛ 80ዋን እንዴት መሸከም አቃተን ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
ሰው ገና ሲወለድ ስለ ዘርና ቋንቋ ምንነት የሚያውቀው ነገር እንደሌለ በማስታወስም ‹‹ቋንቋ የሚባልን ነገር ከመካከላችን አውጥተን ማሰብ ብንጀምር ዘረኝነት ሐሳብ ላይ እንጂ ደም ላይ እንደሌለ እንረዳለን›› ብለዋል፡፡
‹‹እየጨፈርን የናድነውን ቤት እያለቀስን አንሠራውም፡፡ ሁልጊዜ ጥፋት ካደረስን በኋላ እንዳጠፋን የምንረዳ ከሆነ ዞሮ መልሶ አለማወቅ ይሆንብናል፡፡ በመቻቻል ሳይሆን በፍቅር እንኑር መቻቻል አንድ ቀን ያሰለቸናል፡፡ ታገስኩህ ቻልኩህን ያመጣል፡፡ ፍቅር ግን እስከ ኦሜጋ ይሸከማል›› ማለታቸው ተጠቅሶም በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች ብዙዎች ሲያደንቋቸውና መልእክቱንም ሲቀባበሉት ሰንተዋል፡፡
ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011