“አማርኛ ‘ኢትዮጵያዊኛ’ ይባል የሚል ሐሳብ ቀርቦ ነበር”

0
1120

ጋዜጠኛ ተክሉ ታቦር ግለ ሕይወት ታሪካቸውን በመጽሐፍ ጠርዘው ለአንባብያን ሲያቀርቡ በዘመናቸው ስለነበረው ስርዓተ ማኅበር እና በሕይወታቸው ስላለፉ ሰዎች በርካታ ታሪኮችን አብረው ጽፈዋል። ብርሃኑ ሰሙ የመጽሐፉን ይዘት በአጭሩ ያስቃኙናል።

 

 

“ቀደም ሲል በተለያዩ ጊዜያት ሦስት የትርጉም መጻሕፍት ጽፌ ሳቀርብ፥ አእምሮዬ የወለደውን ወጥ የሆነ ድርሰት ጽፌ ለማበርከት አሳቡ ቢኖረኝም፣ የራሴን የሕይወት ታሪክ ለመጻፍ ግን ምኞት አልነበረኝም” የሚል መረጃ ያኖሩት ጋዜጠኛ ተክሉ ታቦር “የሕይወት ታሪክህን ጻፍልን” የሚለው የአንዱ ልጃቸው ጉትጎታ “ተክሉ ታቦር በተክሉ ታቦር” በሚል ርዕስ በ2010 ለአንባቢያን ያቀረቡትን መጽሐፍ እንዲያሰናዱ ምክንያት ሆኖኛል ይላሉ – በመጽሐፉ መግቢያ ባሰፈሩት ሐሳብ።
የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባልደረባ የነበሩት ጋዜጠኛ ተክሉ ታቦር በአዲስ አበባ ከተማ፣ “ፊት በር” በሚባለው መንደር ነሐሴ 30 ቀን በ1930 ነበር የተወለዱት። ከልጅነት አሁን እስከ ደረሱበት ያለውን የሕይወት፣ የትምህርትና የሥራ ታሪካቸውን በ585 ገጾች ባቀረቡበት ግለ ሕይወት ታሪክ መጽሐፍ፣ ስተወለዱበት መንደር የልጅነት ትዝታ፣ ወላጆቻቸው መኖሪያቸውን በመርካቶ አዲስ ከተማ ካደረጉ በኋላ በዘመኑ በአካባቢው የነበረው ማኅበራዊ ሕይወት ምን ይመስል እንደነበር፣ በ1940ዎቹ መርካቶ ውስጥ የነበረው የንግድ እንቅስቃሴና የዘርፉ ተዋንያን እነማን እንደነበሩ፣ ከአዲስ አበባ በመቀጠል ስለኖሩባት ጅማ ከተማ፣ በሥራና በተለያየ አጋጣሚ ስለጎበኟቸው የኢትዮጵያ ክፍላተ አገራትና ስለ ውጭ አገር የጉዞ ተሞክሯቸው ሰፊ ሊባል የሚችል መረዎችን አቅርበዋል።
ከነጋዴ ቤተሰብ በመወለዳቸው ምክንያት የመጀመሪያ ሥራቸውን ንግድ አድርገው የነበሩት ጋዜጠኛ ተክሉ ታቦር የመማር ዕድል ከማግኘታቸው ጋር በተያያዘ “የሕይወት ጥሪያቸውን” ሲፈልጉ ለጋዜጠኝነቱ አድልተው በሙያው ከመሠማራታቸው በፊት መምህር የመሆን ምኞት ነበራቸው። ወደ ጋዜጠኝነት ያመሩበት በብዙ የሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ አልፈው ነው። በግለ ሕይወት ታሪክ መጽሐፋቸው የበርካታ ሰዎችን ሥራና ታሪክ፣ የተለያዩ አገራዊና ዓለማቀፋዊ ክስተቶችን ያስቃኛሉ።
በ1940ዎቹ ኢትዮጵያዊያንን ለንግድ ሥራ በመቀስቀስ ታላቅ ሥራ ስላከናወኑት ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ፣ መርካቶ ውስጥ በኪስ አውላቂነቱ ምክንያት “ጥበበኛው” የሚል ሥም ወጥቶለት ስለነበረው “ጋሽ ታዬ”፣ “የቀጥቃጭ ልጅ” ተብሎ በመናቁ ምክንያት “ወደ ጅብነት እለወጣለሁ” እያለ ጓደኛቹን ያጠቃ ስለነበረ ልጅ ብልጠትና የተንኮል ሥራ፣ በየዓመቱ የጥምቀት በዓል ዕለት በአዶ ከበሬ ጨፋሪነቷ ትታወቅ ስለነበረቸው የአዲስ ከተማ (የመርካቶ) ነዋሪዋ ዘነቡ፣ መንግሥት “ወንጀለኞች” ናቸው ብሎ ስቅላት የተፈረደባቸው ሰዎች እንዲሞቱ ይደረግበት ስለነበረው የካሣ ገብሬ ሠፈር (7ኛ አደባባይ) ተነስቷል።
የመርካቶ ነዋሪዎች ውኃ ከጉድጓድ እየቀዱ፣ በመብራት ፈንታ ኩራዝ እና መሰል ተቀጣጣይ ነገር ይጠቀሙበት ስለነበረው ዘመን፣ በዳቦ ንግድ ታዋቂ በነበሩት የወለጋ ሰዎች ምክንያት “ወለጋ ሞፎ” የሚል ሥያሜ ወጥቶለት ስለነበረው የመርካቶ “ተራ”፣ የሱቅ በደረቴ ንግድ መርካቶ ውስጥ መቼና እንዴት እንደተጀመረ፣ አንድ ሳንቲም ያለው ዋጋ ከፍ ያለ ከመሆኑ የተነሳ ለእኔ ቢጤዎች ይቸር እንደነበር፣ ቅንስናሽ ሳንቲም አሳልፎ ላለመስጠት በሚደረግ ጭቅጭቅ ሽማግሌዎች ገብተውበት ሲያሸማግሉ በማስታረቂያነት የሚቀርበው “ግማሹን ሳንቲም ለባለ (ተከፋዩ) መተውን ነበር” እያሉ ያለፉበት፣ ያዩትናና የሰሙትን መረጃ አቅርበዋል።
በመጽሐፉ ሥም፣ ሥራና ታሪካቸው የተነሳው ሌላኛው ባለታሪክ ቀኛዝማች ተመስገን ደልኬሮ ናቸው። ወላጀቼ በአዲስ ከተማ መኖሪያ ቤታቸው ከብት እያረቡ ወተት ለገበያ ያቀርቡ ነበር የሚሉት ጋዜጠኛ ተክሉ ታቦር፥ በወተት ማከፋፈሉ ሥራ የነበራቸውን ተሳትፎ ሲገልጹ “ወተት ለሆቴላቸው ከምንሸጥላቸው አንዱ ቀኛዝማች ተመስገን ደልኬሮ ነበሩ። አንዱ ሊትር ይሸጥ የነበረው በስሙኒ ነው። ቀደም ሲል ኪኪያ ግንብ አጠገብ ውስጥ በነበረው ካፌያቸው፣ በኋላ ደግሞ ‘ነጸነት ጎሕ’ በተባለው ሆቴላቸው፣ በጠርሙስ ይዘን እንወስድ የነበርነው እኔና ወንድሜ ፈለቀ (በኋላ ኮሎኔል) በየተራ ነበር። ዘወትር በአውሮፓውያን አለባበስ ሽክ ይሉ የነበሩት ቀኛዝማች ተመስገን፣ ወተቱን ስናደርስ ፉርኖ (ዳቦ) ይሰጡን ነበር።”
በሥራዬ ስኬታማ ነኝ፣ በዚህ ምክንያት ካገኘሁት ተጨማሪ ገቢ ለመንግሥት የሚገባውን የግብር ሰብሳቢ መሥሪያ ቤት ሰዎች “እባካችሁን መጥታችሁ ተቀበሉኝ” የሚል ጥሪ በአደባባይ በማቅረባቸው ታዋቂ ሆነው የነበሩት ቀኛዝማች ተመስገን ደልኬሮ፣ ከ1967 ለውጥ በኋላ የደረሰባቸው ችግር ምን ይመስል እንደነበር ጋዜጠኛ ተክሉ ታቦር ያዩትና ከባለታሪኩ አንደበት የሰሙትን ምስክርነት በመጽሐፋቸው ከትበውታል።
የአዲስ አበባው ኑሮና ሕይወት ካበቃ በኋላ እናታቸውን ተከትለው ወደ ጅማ ከተማ የሔዱት ተክሉ ታቦር፥ እዚያም በተለመደው መልኩ የንግድ ሥራቸውን ነበር ለመቀጠል የሞከሩት። ሰልቫጅ አላባሳትን መነገድ በጅማ የመጀመሪያ ሥራቸው ሆነ። በመቀጠል የመጠጥ መሸጫ ግሮሰሪ ከፈቱ። ዕቁብ ገቡ፣ ገንዘቡን ለመውሰድ የሚዋሳቸው አጥተው ነበር። ቆይቶ የሚዋሳቸው ሲያገኙ “ብሩን ለእናቴ ስጧት እኔ አልፈልገውም” አሉ። ማታ ቤት ሲገቡ ለእናታቸው “ምን ሥራ ላይ መሠማራት እንደምፈልግ ቆይቼ አሳውቅሻለሁ” ብለው “የሕይወት ጥሪያቸውን ፍለጋ” መጻሕፍት ንባብ ላይ መሸጉ። በ1948 ዲንቁ ቢራቱ የሚባል አሮጌ መጻሕፍት ነጋዴ በጅማ ከተማ ስለተዋወቁ እሱ የሚያቀርብላቸውን መጻሕፍት ማንበብ ቀጠሉ።
በጂማ ከተማ የተዋወቁት ጃለታ ኡርጌሳ የሚባል ፀጉር አስተካካይ ቀን እየሠራ ማታ እንደሚማር ሲነግራቸው፣ አቋርጠውት የነበረው ትምህርታቸውን ለመቀጠል ልባቸው ተነሳሳ። በጅማ ሚያዝያ ሃያ ሰባት ትምህርት ቤት በማታው ክፍለ ጊዜ ትምህርታቸውን መከታተል የጀመሩት ከ3ኛ ክፍል ሲሆን በወቅቱ የ18 ዓመት ወጣት፣ ባለትዳርና የልጅ አባትም ነበሩ።
ጅማና አጎራባች መንደሮቿም በወቅቱ ምን ይመስሉ እንደነበር ለማስቃኘት በመጽሐፉ ብዙ ገጾች ተመድቧል። ፋሽስቱ ጣሊያን ለዋና ከተማነት አስቧት በነበረቸው ጅማ ላይ በዚያ ዘመን ስለተሠሩ የልማት ተግባራት፣ በኋለኛው ዘመን ቢቺሪሎ በሚባል ጣሊያናዊ በጅማ ከተማ በየዓመቱ ያዘጋጀው ስለነበረው የመኪና ውድድር፣ “ፈረንጅ አራዳ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘውና በአሜሪካ መንግሥት ተራድኦ ስለተቋቋመው የእርሻ ት/ቤት፣ ሰባተኛ ብርጌድ ይባል የነበረው የጦር ካምፕ ይገኝበት ስለነበረው ግቢ፣ የደርግ ሊቀመንበር የነበሩት መንግሥቱ ኃይለማርያም፣ በልጅነታቸው ዘመን የልጅ እስካውት ሆነው በሚያዝያ ሀያ ሰባት አንደኛ ደረጃ ት/ቤት እየተመላለሱ ይማሩ እንደነበር… በርካታ መረጃዎችን ከመቅረባቸውም ባሻገር፣ ተክሉ ታቦር ከኮሎኔል መንግሥቱ ጋር የአንድ ክፍል ተማሪዎችም ነበርን ይላሉ።
“‹ስሪ ቢ› ክፍላችን እያለን፣ በዚሁ ክፍል ይማሩ ከነበሩት የወታደር ቦይ እስካውት ተማሪዎች አንዱ፣ የኢትዮጵያ መሪ የነበሩት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም መሆናቸውን ዘግየት ብሎ ለመረዳት ችያለሁ” ይህንን ምስክርነት እንዲያግዝ በመጽሐፉ ገጽ 76 የ“ስሪ ቢ” ክፍል ተማሪዎች ፎቶ ግራፍ ቀርቧል።
ከቡና ምርቷ ጋር በተያያዘ፣ ብዙ ነጋዴዎች ይጎርፉባት በነበረቸው ጅማ ቀኛዝማች ተካ ኤገኖ የመሳሰሉት ባለሀብቶች የሥራ እንቅስቃሴ ምን ይመስል እንደነበር፤ የ1953ቱ መፈንቅለ መንግሥት ጅማ ከተማ ውስጥ እንዴት ባለ ሁኔታ እንደተሰማ፤ በ1967 አብዮት ዋዜማ የተቃውሞ እንቅስቃሴው “በላንድሮቨር ተራ” ምን ይመስል እንደነበር… በስፋት ይተረካል።
በትምህርትና ንባብ ውስጥ አልፈው የሕይወት ጥሪያቸውን ያገኙት ጋዜጠኛ ተክሉ ታቦር፥ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ባልደረባ ከሆኑ በኋላ ስላለፉበት የሥራና የሕይወት ገጠመኞቻቸውን ማዕከል አድርገው ያቀረቧቸው መረጃዎች “ብዙ ነው” የሚለው ቃል አይገልጸውም። ከሦስት ዓመት በኋላ ቢዘጋም ማስታወቂያ ሚኒስቴር በ1956 የሬዲዮ ጋዜጠኞች ማሠልጠኛ ማዕከል አቋቁሞ የነበር ስለመሆኑ፤ ሒልተን ሆቴልን ለመገንባት ሲታሰብ የተነሳው የባለቤትነት፣ የስያሜና የብድር ጉዳይ በምን ያህል ስፋት እንዳጨቃጨቀ፤ ጅቡቲ ነጻነቷን ከማግኘቷ በፊት ዕጣ ፈንታዋ ምን ሊሆን ይችላል በሚል ኢትዮጵያ ውስጥ ይነሳ ስለነበረው ጥያቄና ስጋት፤ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለውን መፈክር ከደርግ ቀድሞ የፈጠረው ማን እንደነበር፤ አማርኛ ቋንቋ “ኢትዮጵያዊኛ ይባል” ያሉ ቅን አሳቢዎች በአንድ ወቅት ስላደረጉት ትግል, “የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዳሚ በሺሕ ዘጠኝ መቶ ስድሳ ሰባት በመንግሥት ደረጃ በባሕል ሚኒስቴር” ሥር የተቋቋመውም በዚህ ምክንያት እንደነበር መረጃ ይሰጣሉ።
ጋዜጠኛ ብርሃኑ ዘሪሁን ለሥራ የተሰጠው መኪና በመንግሥት ሲቀማ፣ በማግስቱ ወንድሞቹ አዲስ ቮልስዋገን መኪና ገዝተው እንደሰጡት፣ ኤርትራ ከመገንጠሏ በፊት በሊቢያ አየር መንገድ ቢሮ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ተገንጥላ የሚያሳይ ካርታ ተሰቅሎ እንደነበር፣ ግብጾች ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞችን ጠርተው የጦር መሣሪያ ማምረቻ ፋብሪካዎቻቸውን ያስጎበኙበት ምክንያት ምን ይሆን? የሚል ጥያቄ በኢትዮጵያዊያን ስለመነሳቱ፣ የስድስት ኪሎው መታሰቢያ ሐውልት በዩጎዝላቪያዊያን ዕርዳታ እንዴት ሊሠራ እንደቻለ፣ ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር እንዲሆኑ ሲጠየቁ ፈቃደኛ ስላልሆኑበት ምክንያት… እና የመሳሰሉ በርካታ መረጃዎች የቀረቡበት “ተክሉ ታቦር በተክሉ ታቦር” መጽሐፍ፥ ደራሲው እንኳንም የልጃቸውን ጥያቄ አክብረው ጻፉት የሚያሰኝ ትልቅ የመረጃ ሰነድ ነው።

ብርሃኑ ሰሙ በተለያዩ የሕትመት ብዙኃን መገናኛዎች ለሁለት ዐሥርት ዓመታት የሠሩ ሲሆን፣ የመጽሐፍት ደራሲም ናቸው፡፡ በኢሜይል አድራሻቸው ethmolla2013@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here