አዲስ አበባ በመቶ ሚሊዮን ብር የመንገድ መብራቶቿን ልትቀይር ነው

0
715

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በ2010 በጀት ዓመት በነባር የከተማዋ መብራቶች ላይ ያሉትን የመንገድ ዳር መብራቶች ለእይታ ምቾት በሚሰጡ አዲስ ቴክኖሎጂ በሆኑት የኤል.ዲ መብራቶች 100 ሚሊየን ብር በጀት መድቦ ሊሠራ እንደሆነ ታወቀ።
በከተማዋ ነባር አካባቢዎች ላይ ያሉትን የመንገድ ዳር መብራቶች በኤል.ዲ ዘመናዊ መብራቶች መቀየሩ ከተማዋን በተሻለ መልኩ በመለወጥ አስተዋፅዎ እንዳለው እና ከአገልግሎት ጋር ተያይዞ ነባር መብራቶች በኤል.ዲ ሲተኩ 10 ዓመት አገልግሎት የሚሰጡና የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ 120 ዋት እንደሚወስዱ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ለአዲስ ማለዳ ገልፀዋል።
በከተማዋ አንዳንድ መንገዶች ላይ በምሽት የሚስተዋለው ደብዛዛ ብርሃን እንዲሁም ከአገልግሎት ዕድሜ ብዛት ከአግልግሎት ውጪ የሆኑ መብራቶችን ሙሉ በሙሉ በአዲስ ኃይል ቆጣቢ በሆኑና ረጅም ጊዜ አግልግሎት የሚሰጡ ተፈጥሮአዊ ብርሃን ባላቸው ኤል.ዲ መብራቶች የሚተኩ ሲሆን ሥራው የሚከናወንባቸው አካባቢዎች ከ21 በላይ ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል ከቤተ መንግሥት እስከ ሂልተን ሆቴል ፣ ከቴዎድሮስ አደባባይ እስከ አራዳ ሕንፃ ፤ ከመስቀል አደባባይ መብራት እስከ ፖስታ ቤት፣ ከአፍሪካ ኅብረት እስከ ገነት ሆቴል፣ ከአራዳ ሕንፃ እስከ ማዘጋጃ ቤት፣ ከአፍሪካ ኅብረት እስከ ሜክሲኮ አደባባይ፣ ከመስቀል አደባባይ እስከ ፖስታ ቤት ፤ ከሊፍ ሕንፃ የሚገኙት ሲሆኑ በመቀጠልም ከተክለሃይማኖት ሱማሌ ተራ እስከ አፍንጮ በር፣ ከራስ መኮነን ድልድይ እስከ አውቶቢስ ተራ መሳለሚያ እና ገዳመ ኢየሱስ አካባቢዎች ያሉ ጎዳናዎች ይካተቱበታል።
በከተማዋ ነባር መንገዶች ከ1983 በፊት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን አማካኝነት በእንጨት እና በብረት ምሶሶ ተተክለው አገልግሎት የሚሰጡት መብራቶች አብዛኛዎቹ የኢንካድሰንት እና ፍሎረስንት ምርቶች መሆናቸው ይታወቃል። በተመሳሳይም የሶድየም የመንገድ ላይ መብራቶች በከተማችን አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ። ሆኖም ግን አሁን ሙሉ በሙሉ አግልግሎት የሚሰጡት 40% ሲሆኑ አገልግሎታቸውም ቢያንስ ከ3 ዓመት የማይበልጥ እና ከኃይል አጠቃቀም ጋርም ተያይዞ የሚወስዱት 250 ዋት ነው።
ነባሮቹ መብራቶች ረጅም ዓመታት በማገልገላቸው የተነሳ አብዛኛዎቹ አገልግሎት ያለፈባቸው በመሆናቸው በመስመር መቆራረጥ እና የተለያዩ የመሠረተ ልማት በሚሠሩበት ወቅት በኬብል መቆራረጥ ምክንያት ብልሽት ያጋጥማቿዋል። በመሆኑም ባለሥልጣኑ በተደጋጋሚ የጥገና ወጪ እያደረጉ ያሉ የመንገድ ዳር መብራቶች ዘመኑ ባፈራው ኃይል ቆጣቢ ኤል.ዲ መብራቶች ሙሉ በሙሉ ሊቀየሩ እንደሆነ |የከተማው መንገዶች ባለሥልጣን አስታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here