በፌደራል መንግሥት፣ በትግራይና በአማራ ክልል መካከል ያለውን አለመግባባት ለመፍታት የተደረገው ሙከራ ሳይሳካ ቀረ

0
426

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ጎልማሶች ማኀበራት ኅብረት በመስከረም 4 /2013 ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽኅፈት ቤት፤ለትግራይ ክልል እና ለአማራ ክልል ኅብረቱ በጻፈው ደብዳቤ በሦስቱ አካላት መካከል ያለውን አለመግባባትና ልዩነት በውይይት ለመፍታት ያስችላቸው ዘንድ የሽምግልና ጥያቄ ቢያቀርቡም ጥያቄው ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱን አስታውቋል ።

በመሆኑም ከፌደራልም ይሁን ከኹለቱ ክልሎች ምንም ዓይነት ምላሽ ሳያገኝ መቅረቱ የተገለጸ ቢሆንም አሁንም ቢሆን ችግሩ መቋጫ ስላልተገኘለት የሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት ከሠላም ጥሪ ጎን እንዲሆኑና መፍትሔ እንዲያበጁ ኅብረቱ ጠይቋል፡፡

በተጨማሪም በዓለም ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፤ ‹‹የተለያዩ የእምነት ተቋማት ምንም እንኳን በእምነታችን ዶግማ የምንለያይ ብንሆንም በኢትዮያዊነታችን አንድ ነን›› ያለው ኅበረቱ፤የእምነት ተቋማቱ የቀረበውን የሠላም ጥሪ እንዲደግፉ ብሎም ከሠላም ጥሪው ጎን በአንድነት እንቁም ሲል ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ግጭትን ለመቀስቀስ ወጣቱ ወደ ጦርነት እንዲገባ የቅስቀሳ ሥራ የሚሰሩ መገናኛ ብዙሃንና ጦማሪያንን ደግሞ እንደሚቃወም የገለጸ ሲሆን ባህላዊም ሆነ ሃይማኖታዊ የአብሮነት እሴቶችን ለማጠልሸት ከየትኛውም ወገን ይሁን የሚሰሩ ሥራዎችን እንቃወማለን ብሏል።

አሁንም ቢሆን መገናኛ ብዙኃን፣የሃይማኖት አባቶች እና የአገረ ሽማግሌዎች ከሠላም ጥሪው ጎን እንዲቆሙ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ጎልማሶች ማኀበራት ኅብረት ጥሪውን አቅርቧል።

ቅጽ 2 ቁጥር 103 ጥቅምት 14 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here