የማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር ለማዕድን አሰሳ እና በቅርቡ ለሚጀምረው የኢቲዮ-ጅቡቲ የተፈጥሮ ጋዝ ቱቦ ዝርጋታ ድሮን መጠቀም እንደሚጀምር አስታወቀ።
ሚንስቴሩ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ የሚታየው አስቸጋሪ መልክዓ ምድር የማዕድን አለኝታ ቦታዎችን ለመለየት ስላስቸገረኝ የድሮን ቴክኖሊጂን ልጠቀም ነው ብሏል።
በቅርቡ ለሚጀምረው የተፈጥሮ ጋዝ ቱቦ ዝርጋታም ድሮኖችን ለመጠቀም ከኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ጋር ተስማቷል።
ከኦጋዴን ተነስቶ ጅቡቲ ድረስ የሚዘልቀው እና ስምንት መቶ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የቱቦ ዝርጋታው ደኅንነቱም እንዲጠበቅ በማሰብ ድሮን መጠቀሙ አስፈልጓል ተብሏል።
ድሮኖቹ በቱቦው ውስጥ የሚተልላለፈውን የጋዝ መጠን የሚለኩ፣ በተፈጥሮ ሊኖር የሚችልን ፍሰት መጠቆም የሚችሉ ሲሆን ከውጭ ደግሞ ቱቦው ጥቃት እንዳይፈፀምበት ቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ ይሠጣሉ። ቱቦው በድሮን እንዲጠበቅ ሦስት ጣቢያዎች ይሰሩለታልም ተብሏል።
እያንዳንዱ ድሮን ከ150 እስከ 300 ኪሎ ሜትር ሲሸፍኑ አንዱ ድሮን እስከ 60 ኪሎ ግራም ክብድት የመሸከም አቅም አለው። ለተከታታይ አምስት ሰዓት አየር ላይ መቆየት እና ስድስት ሺሕ ኪሎ ሜትር መጓዝ የሚችሉ ናቸውም ተብሏል።
ቅጽ 1 ቁጥር 7 ታኅሣሥ 20 ቀን 2011