በአዲስ አበባ የመታወቂያ የአሰጣጥ ስርዓት ኦዲት ሊደረግ ነው

0
1041

በአዲስ አበባ በሚገኙ 121 ወረዳዎች ላይ መታወቂያን ጨምሮ የልደት እና የጋብቻ ሰርተፍኬት አሰጣጥ ስርዓት በቅርቡ ኦዲት ሊደረግ እንደሆነ የከተማ አስተዳደሩ የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ኃላፊ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በኤጀንሲው የነዋሪዎች አገልግሎት ዘርፍ ኃላፊ ዮሀንስ አምባቸው እንደገለፁት በ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር በሚገኙ በሁሉም ወረዳዎች የኦዲት ስራ ሊስራ እንደሆነ አረጋግጠዋል።

የመታወቂያ የልደትና የጋብቻ ሰርተፍኬቶች በብርሀንና ሰላም እንደሚታተም ጠቅሰዉ የሚታተሙት ካርዶችም አመሳስሎ መስራት እንደማይቻል ሁሉም ሰርተፍኬትና መታወቂያዎች መለያ ቁጥር እንዳላቸው ያስረዱት ዩሐንስ ነገር ግን በህገወጥ መልኩ የተለያዩ ወረዳዎች ላይ ብር በማስከፈል ለከተማዋ ነዋሪ ላልሆኑ ሰዎች መታወቂያ የልደት፣የጋብቻ ሰርተፍኬት ሲሰሩ የነበሩ ሰዎችም እንዳሉ ጠቁመዋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ በቅርቡ ወደ ስራ የሚገባው የኦዲት የማድረግ ሒደት ምን ያህል በሕገ ወጥ መንገድ ተሰርተው ለሰዎች ተላለፉ መታወቂያዎች እና ሌሎች ሰነዶች መኖራቸውን ለማረጋገጥ እንደሚቻል አዲስ ማለዳ ከኤጀንሲው ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

አመሳስሎ አለመሰራታቸው ደግሞ ሕገወጥነትን ከማስቀረት አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅኦ አልው በተለይ አሁን ለፓስፖርት የልደት ሰርተፍኬት ስለሚያስፈልግና በዚህም ብዙ ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ሰዎች ኢትዮጵያዊ ነን እያሉ እንዳሉና እሱን ከማስቀረት አንፃር ከፍተኛ ጥቅም እንዳለው ዩሐንስ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

ይህንንም ለማስቀረት ወሳኝ ኩነት የክትትል ስራ በመስራት ላይ እንዳለና እነሱም ላይ ከአመራር ቦታ ማንሳትንና በቁጥጥር ስር ማዋልን ጨምሮ እርምጃ እየወሰዱ እንደሆነ ነግረውናል።

መታወቂያ ማለት አንድ ሰው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የሚያስፈፅምባቸው ናቸው ያሉት ኃላፊው ይህ የመታወቂያ ኦዲት ስራ ከፖለቲካም ሆነ ከምርጫዉ ጋር ምንም የሚያያይዘው ነገር እንደሌለ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

መታወቂያ ስለሰጣችሁ ነው ቤት የተሰጠው መሬት የተሰጠው የሚሉት አካሎች የተሳሳቱ እንደሆኑና ማስረጃ አለኝ የሚል አካል ካለ ግን ቢሮአቸው ክፍት እንደሆነ አስታውቀዋል።

የኦዲት ማድረጉ ጥቅም ለሀብት ቁጥጥርና ካሳተምነው ምን ያክል ጥቅም ላይ ዋለ፣ምን ያክል በትክክል ስራ ላይ ዋለ የተበላሸስ አለ ማከማቻ ውስጥ ስንት አለ የሚለውን ለማጣራት እንደሆነ ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ ገልጿል።

ለትርፍ ያልተቋቋመ ተቋም መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው ለመታወቂያና ለሰርተፍኬቶች ወሳኝ ኩነቱ የሚያወጣው ገንዘብ ከፍተኛ እንደሆነ ከተገልጋዩ የሚቀበለው ክፍያ ግን አናሳ እንደሆነ ለዚህም አሁን መንግስት እየደጎመው እንዳለ አስታውሰዋል።

የወሳኝ ኩነት ኦዲት ክፍል የሰው ኃይል አነስተኛ በመሆኑና በአዲስ አበባ የሚገኙ ወረዳዎች 121 በመሆናቸው የከተማው ኦዲት የሚመለከተው አካል እገዛ ስለሚያስፈልግ ትብብር እንደጠየቁና በትብብር እንደሚሰሩ ጠቅሰዋል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የዲጂታል መታወቂያ ህዳር 2012 መስጠት የጀመሩ ሲሆን በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ እንደተጀመረም ያስታወሱት ዮሐንስ በአሁኑ ሰአት ደግሞ በጉለሌ ክፍለ ከተማ ፣ ቦሌ በወረዳ3 እና በየካ ክፍለ ከተማ ሁሉም ወረዳ ላይ ሙሉ በሙሉ የዲጂታል መታወቂያ እንደሚሰጥ ኃላፊው ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

በዘጠና አንድ ወረዳዎች የሚገኙ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መታወቂያ ለመቀየር ወይም ለማውጣት ሲሄዱ የሚያገኙት አዲሱን ዲጂታል መታወቂያ ወይም የሲስተም ችግር ከኖረ መለያ ቁጥር ያላቸው እና በዕጅ የተጻፉ መታወቂያዎች እንደሚሰጥና በአንዳንድ ወረዳዎች ደግሞ ከኢንተርኔት ውጪ የምዝገባ ስርአት ተዘርግቶ ማንኛውም መታወቂያ ለመቀየር የሄደ ሰው አሻራ ሰጥቶ የተመዘገበበትን ቁጥር ይዞ እንደሚሄድ ተናግረዋል።

በአሁኑ ሰአትም 150ሺ ለሚሆኑ ሰዎች ዲጂታል መታወቂያውን እንዳዳረሱ ለማወቅ ተችሏል። ቀልጣፋ አሰራርን እንዲኖር ለማድረግ እንዲያስችል ከኹለት ወር በፊት 880 የሚሆኑ አዳዲስ ሰራተኞች ከእነዚህም ውስጥ 571 የሚሆኑ አዲስ ተመራቂዎች እንደቀጠሩና በእያንዳንዱ ክፍለ ከተማ ኹለት የአይሲቲ ባለሙያዎች እንዳሉም አሳውቀዋል።

ለዲጂታል መታወቂያው ማመላለሻ እንዲሆን 47 ሞተር ሳይክል አሰራጭተናል ያሉት ኃላፊው፤ የመብራት ችግርን ከመቅረፍ አንፃር 56 ለሚሆኑ ወረዳዎች ጀኔሬተር እንደተገዛም ለማወቅ ተችሏል።

በከተማችን ላይ የሚገኙ 18 ወረዶች ግን ጭራሽ የዲጂታል መታወቂያ መስጠት እንዳልጀመሩና ይህም የሆነው የመሰረተልማት ችግር በዋናነት መብራት ተደራሽነት ስለሌላቸው መሆኑን ኤጀንሲው አስታውቋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 103 ጥቅምት 14 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here