የሰላም ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለቀቁ

0
523

በኢፌዲሪ የሰላም ሚንስቴር ሚንስትር ዲኤታ በመሆን ሲያገለግሉ ቆዩት አልማዝ መኮንን በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው ታወቀ።
አዲስ ማለዳ ከሚንስቴሩ ያገኘችው መረጃ እንደሚያመለክተው አልማዝ መኮንን በገዛ ፈቃዳቸው ነገር ግን ለጊዜው ይፋ ባልሆነ መንገድ ሥልጣናቸውን መልቀቃቸው ታውቋል። ከኃላፊነት ሥፍራቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ በሚኒስቴሩ የክብር አሸኛኘት የደረገላቸው ሲሆን በተቀመጡበት ኃላፊነት ሥፍራ ላይ ለሕዝባቸው ላበረከቱት ኃላፊነትም ምስጋና ተችሯቸዋል።

አልማዝ መኮንን ነባር የሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ አባል እንደነበሩ እና ከዚህ ቀደም ለረጅም ዓመታት በአዲስ አበባ ጽዱ እና አረንጓዴ፤ ዘላቂ ማረፊያ ስፍራዎች ዋና ኃላፊ በመሆን ሲያገለግሉ እንደነበርም የሥራ ታሪካቸው ያስረዳል።

አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት አሁንም ደረስ የአልማዝ ከኃላፊነታቸው መልቀቅ ግልጽ የሆነ ምክንያት ማግኘት እንዳልተቻለ እና ምናልባትም ግን በቅርቡ በሕወሓት በኩል በፌደራል የስልጣን ስፍራዎች ላይ ተቀምጠው የሚገኙ አባላት በአስቸኳይ ከኃላፊነታቸው ለቀው ወደ ትግራይ በመሔድ ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚል መልእክት ከመተላለፉ ጋር የተያያዘ እንደሚሆንም ተገምቷል። ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት አልማዝ መኮንን በአዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።

የኢፌዲሪ ሰላም ሚንስቴር በፈቃዳቸው ከኃላፊነታቸው ለቀቁትን አልማዝ መኮነንን ተክተው የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሆነው ሲያገለግሉ ነበሩትን ኃይላይ ብርሐኔን በምትካቸው መቀበሉን አዲስ ማለዳ ከሰላም ሚኒስቴር ምንጮቿ አረጋግጣለች።
ኃይላይ ብርሐኔ በመጀመሪያዎቹ በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ከተሾሙት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አንዱ ሲሆኑ ለኹለት ዓመታት ገደማም በጠቅላይ ሚንስትር ቢሮ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ በመሆንም አገልግለዋል። በመሆኑም በቅርቡ የአልማዝ መኮንን መልቀቅን ተከትሎ ኃይላይ በርሐኔ ወደ ሰላም ሚንስቴር ድኤታነት በመዘዋወር ሥራ መጀመራቸውም ለማወቅ ተችሏል።

የለውጡ ኃይል ወደ ሥልጣን ከመጣበት ከኹለት ዓመት ተኩል ወዲህ በከፍተኛ ሁኔታ የካቢኔዎች ሽግሽግ መደረጉ የሚታወቅ ነው። በገዛ ፈቃዳቸው ከተመደቡበት የኃላፊነት ሥፍራ የለቀቁ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም ከአልማዝ መኮንን ጋር አዲስ ማለዳ ባደረገችው ማጣራት ስድስት ደርሰዋል። በኢፌዲሪ ሰላም ሚኒስትር ውስጥም በሚንስትር ዲኤታ ማዕረግ ላይ የነበሩ እና በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን ለቀቁ አልማዝ መኮንን ከዘይኑ ጀማል ቀጥለው ኹለተኛዋ ናቸው። የዘይኑን መልቀቂያ ማስገባት ተከትሎም በትምህርት ቤት ምገባ መርሃ ግብር ላይ ስማቸው ከፍ ብሎ የሚሰማው ፍሬዓለም ሽባባው ወደ ሰላም ሚኒስቴር ሚንስትር ዲኤታነት መግባታቸውም ይታወሳል። ከዚህ ጋር በተገናኘም በርካታ ግለሰቦች እና የተፎካካሪ ፓርቲ አባላትም ከዚህ ቀደም ምንም አይነት የመንግስት መዋቅር ውስጥ ሰርተው የማያውቁን ሰው መንግሥት መሾሙ አንደምታው ምንድነው የሚል ትችቶችን አሰምተው ነበር።

በአራት የሚንስቴር ዲኤታ የተዋቀረው ሰላም ሚኒስቴር ከለውጡ መንግሥት ጋር በአዋጅ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገባ እና በርካታ የደኅንነት እና የጸጥታ አካላትን በስሩ አቅፎ የያዘ መስሪያ ቤት ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 103 ጥቅምት 14 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here