ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካን በ3 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የገዛዉ ድርጅት ክፍያ አልፈጸመም

0
1153

የብሔራዊ አልኮል እና አረቄ ፋብሪካ በጨረታ ወደ ግል ይዞታ የተዛወረ ቢሆንም እስካሁን ገዢዉ አካል የሚጠበቅበትን 35 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ እንዳልከፈለ ተገለፀ። ፋብሪካዉን በ3 ነጥበ 6 ቢሊዩን ብር በመግዛት ወደ ግል ይዞታ ያዘዋወረዉ ሎሚናት የመጠጥ ፋብሪካ ሲሆን በቅድሚያ መክፈል ያለበትን 35 በመቶ ክፍያ በጊዜዉ ሳይከፍል ቀርቶ ተጨማሪ የጊዜ ገደብ ጠይቋል። የቀረበለትን ጥያቄ በመቀበል የሕዝብ የልማት ድርጅቶች ፕራይቬታይዜሽን አጀንሲ ተጨማሪ ጊዜያት የፈቀደ ሲሆን ገደቡም ሊጠናቀቅ ወደ አንድ ወር ገደማ እንደቀረዉ አስታዉቋል።
የፕራይቬታይዜሽን ኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወንዳፍራሽ አሰፋ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ሎሚናት የመጠጥ ፋብሪካ ክፍያዉን በጊዜ የማይከፍል ከሆነ ከጨረታዉ ሰነድ ጋር ያስያዘዉ የጠቅላላዉ ዋጋ 2 በመቶ ለመንግሥት ገቢ እንደሚሆን እና መንግሥትም ጨረታዉን የመሰረዝ መብት እንዳለዉ ገልፀዋል። ሎሚናት የመጠጥ ማምረቻ ፋብሪካ በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ2006 በሁለት ኢትዮጵያዊያን ባለሀብቶች ቢኒያም ብርሃኔ እና ብሩክ ወርቁ የተቋቋመ ድርጅት ነዉ።
ቢኒያም ብርሃኔ ከሰላሳ ዓመት በፊት የተቋቋመዉ የካንትሪ ትሬዲንግ ባለቤት ናቸዉ። የድርጅቱን የንግድ እንቅስቃሴ ለማስፋት በማሰብ ካንትሪ ትሬዲንግን ከሀያ ዓመታት በፊት ወደ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ በመቀየር እህት ኩባንዎችንም አቋቁሟል። ካንትሪ ትሬዲንግ በአሁኑ ሰዓት ከ2200 እስከ 2400 ሠራተኞችን በጊዜያዊ እና በቋሚነት ያስተዳድራል።
ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ የአራት ፋብሪካዎች ጥምረት ሲሆን ሁለቱ በአዲስ አበባ ከተማ ሲገኙ አንዱ ፋብሪካ ደግሞ ከአዲስ አባባ በስተምዕራብ አቅጣጫ 25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘዉ ሰበታ ከተማ ላይ ይገኛል ሌላዉ ደግሞ በትግራይ ክልል ማይጨዉ ከተማ ይገኛል። ብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ መንግስት ሙሉ በሙሉ ወደ ግል ይዞታ ካቀዳቸዉ ድርጅቶች ዉስጥ አንዱ ሲሆን ከፍተኛ ሽያጭ እና ትርፍ በማስመዝገብ ስኬታማ እንደሆነም የሚታወቅ ነዉ። ፋብሪካዉ 42 ከመቶ የሚሆነዉን የኢትዮጵያን የአረቄ ገበያ ተቆጣጥሯል። ፋብሪካዉ በ2008 አንድ ዓመት ዉስጥ 475 ሚሊዮን ብር ሽያጭ ያስመዘገበ ሲሆን ትርፉም ከታክስ በፊት 132 ሚሊዮን ነበር። ነገር ግን ፋብሪካዉ ስትራቴጅካዊ ጥቅም ስለሌለዉ ወደ ግል ይዞታ እንዲዘዋወር በመወሰኑ በግንቦት 2010 በጨረታ ሊወጣ ችሏል። ኤጀንሲዉ በቀድሞ ስያሜዉ በመንግስት የልማት ድርጅቶች ሚኒስቴር ከተቋቋመበት 1987 ጀምሮ 370 የልማት ድርጅቶችን ወደ ግል ይዞታ አዛዉሯል። ቀደም ሲልም የትንባሆ ሞኖፖልን በ22 ቢሊዮን ብር ለጃፓን ባለሀብቶች ያዘዋወረ ሲሆን ይህም ኤጀንሲዉ ከሸጣቸዉ ድርጅቶች ከፍተኛ ዋጋ የተመዘገበበት ነዉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በብሔራዊ አልኮል እና አረቄ ፋብሪካ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ተነስቶ ጉዳዩ በፍርድ ቤት እልባት እንደተሰጠዉ ለማወቅ ተችሏል። ብርሃኔ ገብረመድህን የተባሉ ግለሰብ በርካታ ዓመታትን በባለቤትነት ይገባኛል ክርክር ጉዳያቸዉ በፍርድ ቤት ሲታይ የቆየ ሲሆን በመጨረሻም ካሳ እንዲከፈላቸዉ በፍርድ ቤት ተወስኗል። በደርግ የሥልጣን ዘመን ያላግባብ ተወርሶብኝ ነዉ እንጂ ባለቤትነቱ የእኔ ነዉ በሚል መንግሥትን የሚሞግቱት ብርሃኔ ጉዳያቸዉ እልባት አግኝቶ መንግሥት ካሳ እንዲከፍል ተወስኗል። በትዉልድ ኤርትራዊ እና በዜግነት አሜሪካዊ የሆኑት ብርሃኔ ገብረመድህን የይገባኛል ጥያቄ ያነሱበት የብሔራዊ አልኮልና አረቄ ፋብሪካ ጨረታ በወጣ ጊዜ ከባድ ዉዝግብ አስነስቶ ነበር።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዳና ሮህራባቼር ፋብሪካዉ ለብርሃኔ እንዲመለስላቸዉ የሚጠይቅ ደብዳቤ ወደ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ(ዶ/ር) ልከዉ ነበር። ወንዳፍራሽ እንደሚሉት ከሆነ “የብርሃኔ ድርሻ እርሳቸዉ እንደሚሉት ትልቅ አይደለም፤ እንዲዉም ከጊዜ ብዛት ድርሻቸዉ ወደ ፍርስራሽነት እንደተቀየረ” ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here