ከቅርንጫፉ ይልቅ ዛፉ ብዙ ፍሬ›››››››

0
529

ሁሌም ቢሆን በዝሆኖች ጸብ የሚጎዳው ሳሩ ነው ፤ይባላል ያም የሆነበት ምክንያት የሳሩ አቅምና የዝሆኖቹ ክብደት በራሱ ከባድ ሆኖ እየለ ትግሉ ሲታከልበት ደግሞ ሳሩ የሚያስተናግደው ጉዳት ሳይሆነ መጥፋት ሊባል ይቻላል።ዛሬም በአገራችን እይሆ ነ የመጣው ነገር ከዚህ የተለየ አይመስልም።በአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ የፊተኞቹ ባልተግባቡና ወደ ትግል እንግባ ባሉ ቁጥር የንጹሃን ዜጎች ሕይወት የለአንዳች ቅድመ ሁኔታ አጣብቂኝ ውስጥ ይወድቃል።

በጉልበት እና በመሳሪያ የመጣ ሥልጣን ጥቂቶችን ባለጊዜ ያደርግ ቢሆን እንጂ ብዙኃኑን ሲጠቅም አይታይም።በሕዝብ ስም ለሕዝብ እንታገላለን ብለው ምለው ተገዝተው እርካቡን ከጨበጡ በኃላ ሕዝባቸውን ያከበሩ እና ሕዝባቸውን የለወጡ መሪዎችን ማግኘት በአፍሪካ ምድር ከቅንጦት የሚቆጠር ጉዳይ ነው።

የደርግ ሥርዓትን ለመጣልገና ከጅምሩ የከፍትኛ ትምህርታቸውን አቋርጠው ሕወሃትን ሲቀላቀሉ የትግራይን ሕዝብ ከዘመናት ጭቆና ለማላቀቅ በሚል የትግራይ ሕዝብ የከፈለው ዋጋ ቀላል የሚባል አልነበረም።ለኹለት ዓስርት ዓመታት በፈጀው የእርስ በእርስ ጦርነት መላው ኢትዮጵያውያን ብዙ መከራን ገፍተዋል።

ጦርነቱ ካደረሰው የሰው ሕይወት መቀጠፍ እና አካል ማጉደል በላይ ኢትዮጵያን የምታክል ገናና ታሪክ ያላትን አገር ወደብ አልባ አድርጓታል።ከምንም በላይ ግን ለሕዝብ የተገባውን ቃል ወደ ጎን ትቶ የቤተሰብን እና የቅርብ ግንኙነት ላይ ብቻ ያተኮረ በመሆኑየሕዝብን አደራና ጥቅም የካደ መሆኑ ሳያንሰው እራሱን አበልጽጎ አገርን ዘርፎ ሲያበቃ እና በፖለቲካ ቁማር ተበልቶ ሲባረር እንዲሁም የሥልጣን ዕርካቡ ሲናድበት አይኑን በጨው አጥቦ ሕዝብን መሸሸጊያ አድርጓል።

በለውጥ ኃይሉ በኩልም የሰቆቃ ሕይወት ማክተም ያበሰረው እና ቁማሩን የበላው ቡድንም ውሎ አድሮ የዜጎችን መጻኢ ዕጣ ፈንታ ወደ አልታሰበ የቁልቁለት መንገድ ይዞ እየተንደረደረ ነው። በአጭር ጊዜ ውስጥ ብቻ የበርካታ ዜጎች ሕይወትን ቀጥፏል፣ በሚሊዮኖች የለሚቆጠሩ ዜጎችን ከቀያቸው አፈናቅሏል ።

ምን እንኳን በቀላሉ የሚመጣ ለውጥ ባይኖርም የንጹሃንን ክቡር ሕይወት አስይዞ የፖለቲካ ቁማር መጫወቻ ማድረግ ከልክ ያለፈ የሥልጣን ጥማት እንጂ ሕዝባዊነትን አያመለክትም።በሕወሐትና በለውጥ ኃይሉ መሀከል በተፈጠረው እሰጥ አገባ በጥቂቱ ለማየት ስንሞክር ፤ማንነታቸው ባልጣወቁ ሰዎች የሚሞቱ ዜጎች በዝተዋል፤በማንነታቸው ሳቢያ ከተወለዱበት ቀየ ተፈናቅለዋል፤ዩንቨርሲቲዎች ከትምህርት ገበታነት ወደ ብሔር ሽኩቻ መድረክነት ተለውጠዋል የተማሪዎች ታፍነው የደረሱበት ሳይታወቅ ወራት ተቆትረዋል።

ከ እስከ ብለን በንጹሃን ዜጎች ላይ የተፈጸመውን በደል እንቁጠር ካልን ብዙ ሊባል ያስችላል። ነገር ግን ችግሩም ውጤቱም ከእኛው ቤት አይርቅም።እኛው ገድለን እኛው እናወግዛለን። በሟች እና በገዳይ መሀከል ካለው ልዩነት ይልቅ አብረው የኖሩበት ዘመን ይልቃል።ብዙ የደስታ እና የችግር ጊዜያት አሳለፈዋል፤ለአንደኛቸው ጉድለት ሌላኛቸው ተሞልተዋል።

ለውጡ አስገኛቸው ከሚባለት ትሩፋቶች ይልቅ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች የብሔር ማናነትን ምክንያት በማድረግ የተፈናቀሉ እና የሞቱ እንዲሁም ዛሬም ድረስ በስጋት ያሉ በርካት ዜጎች መኖራቸውን ላሰበ የቁማሩ ትሩፋት ነውጥ እንጂ ለውጥ አለመሆኑ አስረጅ ነው።

ከአመታት በፊት በሊቢያ በረሃ ላይ በዜጎች ላይ በደረሰው ኢሰብዓዊ ጥቃት አብረን አልቅሰን አብረን የተጽናናንበት የሞራል ልዕልና ዛሬም ልባችን ውስጥ አለ ፤ላለማየት ወስነን ካልሆነ በቀር።አሁን ላይ ቆመን ይህ ለምን ሆነ? ይህ ለምን አልሆነም? እያልን ከቀጠልን ወደ ማያባራ ውዝግብ ውስጥ ገብተን በንጹሃን ደም አፋሳሽ ተግባር እንጠመዳለን።ለትውልድ ካሰብን አይቀር ቆም ብለን ለማሰብ እንሞክር።

ኢትዮጵያውያን ከተናጠል ችግራችን ይልቅ በጋራ ልንፈታው የሚያስገድደን የአገርን ሁለንተናዊ አቃም የሚፈታተኑ እና የሚገዳደሩ ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ተደቅነውበናል።ለዘመናት ጠፍሮ የያዘን የደህነት እና ኋላቀርነትን ቀንበር በጸብ ውስጥ አይደለም በፍቅርም ልናሸንፈው ተስኖናል።የበረሀ አንበጣ ፣ኮቪድ 19፣ድርቅ እና ሌሎችም ችግሮች ዛሬም በአንድነት ተጋምደን እንድንቆም የሚያስገድዱን ችግሮቻችን ናቸው።

ለኢትዮጵያውድ ልጆች የሚበጀው የቱ ነው?
ውድ በለሥልጣናት እና ሹማምንት ይህ ሕዝብ ሐሳቤን የሚሞላ ትልሜን የሚያሳካ ለወገኔ የሚበጅ ፤የአገርን ኢኮኖሚ ሚገነባ ፤በሥልጣኔ በሰላምና በአንድነት ወደፊት ያራምድልኛል ብሎና ተማምኖ ውድ ሕይወቱን ለገበረላችሁ ዜጋ የምትመች አገር ፍጠሩለት እንጂ ለማያበቃ ጣር እና ፍዳ አትዳርጉት።

አመናችሁም አላመናችሁም አሁን ያላቸሁበት ቦታ ላይ ለመድረስ ትከሻው አውሷችሁ እርሱን እረግጣችሁ ከፍ ማለታችሁን ላፍታም ልትዘነጉት አይገባም፤እናንተን ከፊት ለማቆም እርሱ ከኋላ የሆነበትን የሕዝብ አደራ አትብሉ፤የሰጣችሁን ሀላፊነት ለመወጣት ዛሬ ነገ አትበሉ፤እንደ ኢተዮጵያዊ እሰባችሁ ኑሩ በብሔርተኝነት አትያዙ ፤ለሥልጣን ቆይታችሁ ስትሉ የንጸሃንን ደም አታስገብሩ፤ ይልቅ ለእናንተ ብሎ ለሚሰዋው ሕይወቱ በሀቅ ታገሉ።

እናነት የአገሬ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ቅኝታችሁን መልሳችሁ ቃኙ፤ከጽንፈኝነት ወጥታቸሁ ወደ ማስተዋል ጓዳ ግቡና ሰፊውን ሁዳድ ተመልከቱ፡የትግላችሁ መንገድ ፍቅር እና ማሰተዋል የተሞላ ይሁን እንጂ ብሔርን ከብሔር ጎሳን ከጎሳ የሚያወደድር ጠባብ እይታ አይኑራችሁ፤አንደበታችሁ ከውሸት ልባችሁ ከክህደት ይመለስ፤ከመሄዳችሁ በፊት ቁሙ የትግላችሁን መስመር ፈትሹ ፤ ታላቋን ኢትዮጵያ እሹ እንጂ ወደ ጎጥ አትውረዱ።

ከቅርንጫፉ ይልቅ ዛፉ ብዙ ፍሬ አለውና ዛፉን ተንከባከቡ ፤ቅርንጫፉን ከግንዱ ብንገነጥለው ከተፈጥሯዊ ህልውናው እንለዋለንና ምርታማነቱን እናሳጣዋለን ዕድሜውንም እናሳጥረዋለን እንጂ አናተርፍበትም፤የተጠለልንበት ዛፍ ሁላችንን በአንድ ጊዜ ሊያስጠልለን ይችላል፤ ዛፉን ገነጣትለን መጠለያ ከማጣት ውጪ አንዳች እንደማናተርፍ ልናውቅ ይገባልና ፤ነጣጣይ ሀሳባችንን ወዲያ አሽቀንጥረን ጥለን በአንድነት እንቁም ልዩነታችን እንደ ውበት ፈርጥ እንጂ መተፋፈሪያ እና የግጭት መንስኤ አናድርገው።

እናንተ የሕዝብ እንደራሴዎች ከምንጣላበት ይልቅ የምንፋቀርበትን አልሙ፤ ምሁራን የዘር ጥላቻን ሰባኪ አትሁኑ፤ታሪክን ለትምህርት እንጂ ለጦርነት አታጣቅሱ፤እናንተ የአገሬ ሕዝቦች በተራ ወሬ አትጠመዱ፤ቆማችሁ አስተተውሉ እንጂ እየሔዳችሁ አታስቡ። ብዝሃነት አቅም ነው። በመንደር ከተወሰነ ሐሳብ ይልቅ በሁለንተናዊ አመለካከት አንሞላ፤ ከወንድማማቾች ጸብ በሚመጣ ጥቅም አንደለል፤ እናንተ የእምነት አባቶች ትውልድን በማስተዋልና በፈሪሃ እግዚአብሔር ልታንጹ በቆማችኁበጽ መንገድ ትውልድ ሲቸገር ጥሩውን ከመጥፎ መለየት ሲያቅተው በዝምታ የምልፉበት ዘመን አየደለምና ነቅታችሁ ቁሙ፤ ቸል አትበሉ፤ ምከሩ፤ ገስጹ ነብር ዥንጉርጉርነቱን ላይተው ኢትዮጵያዊም ኢትዮጵያዊነቱ ላይለወጥ በሚያስተዛዝብ መነገድ ላይ ቆመን አንገኝ።
ይሄ አዲስ ማለዳ ነው። በሰለጠነ እና በተራማጅ አስተሳሰብ ማለዳችንን እንጅረው።

ቅጽ 2 ቁጥር 105 ጥቅምት 28 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here