በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የመምህራን የትርፍ ጊዜ ክፍያ ወጥ ሊሆን ነዉ

0
800

በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን የትርፍ ጊዜ ክፍያ በመላ አገሪቱ ተመሳሳይ እንዲሆን ዉሳኔ ላይ ተደረሰ። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ሰበሳቢነት እና በዋና ኦዲተር አቅራቢነት ታኅሣሥ 16/2011 የመንግሥት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዘዳንቶች በተገኙበት በተደረገ ዉይይት ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን የሚከፈለዉ የትርፍ ጊዜ ክፍያ ሕጋዊ አካሄድን ያልተከተለ እና የአሰራር ክፍተት የሚስተዋልበት እንደሆነ ተጠቁሟል፤ ሁሉም ተቋማት የራሳችዉ የሆነ የክፍያ መጠን እንዳላቸውም ተነግሯል።
በውይይቱ ላይ ተመሳሳይነት የሌለዉ የአከፋፈል ሥርዓት ለተለያዩ አስተዳደራዊ ችግሮች እንደሚያጋልጥ እንዲሁም በተግባርም እያጋለጠ እንደሆነ ተጠቁሟል። ዋና ኦዲተር ገመቹ ዱቢሳ እንደተናገሩት ‹‹ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አሰራራቸዉ ብዙ የኦዲት ክፍተት የሚታይበትና በየዓመቱ መሻሻል ያልታየበት ነዉ ብለዋል። በዋናነት ደግሞ ዋና ኦዲተሩ ያነሱት ነጥብ የትምህርት ተቋማቱ የዉስጥ ገቢያቸዉን ከመንግሥት ዕዉቅና ዉጪ ጥቅም ላይ እንደሚያዉሉት እና ይህም አግባብነት የሌለዉ አካሄድ እንደሆነና ከፍተኛ የሆነ የኦዲት ችግር እንዲያጋጥም ምክንያት ሆኗል›› ብለዋል።
ዋና ኦዲተሩ ገመቹ ስለ ትርፍ ጊዜ ክፍያም ሲናገሩ ‹‹በመላ ኢትዮጵያ ያሉ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በዉስጥ ቦርድ በሚወሰን ተመን ክፍያ እንደሚፈጽሙ ገልፀዉ፥ ይህም ተቀባይነት እንደሌለዉ እና በሁሉም ተቋማት አንድ ዓይነት አሠራር እንዲኖር የሚያስችል ጥናት ተጠናቋል፤ በቅርቡ ይፀድቃል›› ሲሉ አክለዋል። በዚህ ጉዳይ ላይ ባለ ድርሻ አካላትን አካቶ ሲካሔድ የነበረዉ ጥናት ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት እና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሲተካ ሥራዉ ቆሞ ነበር። አሁን ሥራዉ ተጠናቆ እንዲፀድቅ እንቅስቃሴ እየተደረገ ነዉ ተብሏል።
በሌላ በኩል ደግሞ ተቋማቱ የራሳቸዉ ገቢ እንዲኖራቸዉ በማሰብ የተለያዩ ኢንተርፕራይዞች እንዲኖሯቸዉ ቢደረግም ሕጋዊ የሆነ አሰራር ስለማይከተሉ እና አላግባብ የተቋማቱን ሀብት ስለሚጠቀሙ የተፈለገዉን ጠቀሜታ እያስገኙ እንዳልሆነ በስብሰባው ላይ ተነግሯል። ከኢንተርፕራይዞቹ ጋር በተያያዘ እንደ ትልቅ ችግር የተነሳው ጉዳይ ኢንተርፕራይዞቹ በአዋጅ የተቋቋሙ ስላለሆኑ የሚተዳደሩበት መንገድም ሕግን የተከተለ እንዳይሆን አድርጓቸዋል ተብሏል። በተጨማሪም ተቋማቱ በተጓዳኝም ሥልጠና በመስጠት እና ከተለያዩ ሽያጮች የሚገኘዉን ገቢ ከአሰራር ውጪ አገልግሎት ላይ እንደሚያውሉና ግዢም እንደሚፈፅሙ ተጠቁሟል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ዋና ኦዲተሩ ‹‹የትኛዉም የከፍተኛ ትምህርት ተቋም አስፈላጊዉን ግዢ በሚመለከት በግዢ ኤጀንሲ በኩል ማከናወን እንደሚችል [ይሁንና] በቦርድ በተላለፈ ውሳኔ ግዢ መፈፀም አይችልም›› ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል።
በዋና ኦዲተሩ ከቀረቡት ሐሳቦች መረዳት እንደተቻለዉ ተቋማቱ እንደ ውስጣዊ ገቢያቸዉ ብዛት ክፍያ እንደሚያካሂዱና ከሚመለከተዉ አካል ዕዉቅና ውጪ ግዢ እንደሚፈፅሙ የታወቀ ሲሆን አዳዲስ የትምህርት ተቋማትም ከቀደምት ተቋማት በመማር ሕጋዊ ያልሆነ አሠራር እየተከተሉ እንደሆነ እና ከፍተኛ የኦዲት ክፍተት እንደሚታይባቸዉ ለማወቅ ተችሏል። ተቋማቱ በበኩላቸው ችግሩ በእርግጥም መኖሩን አምነዉ፤ ነገር ግን አንዳንድ አስቸኳይ እና ጊዜ የማይሰጡ ነገሮች እንደ ተማሪዎች ምግብ የመሰለ ጉዳይ ሲያጋጥም በውስጥ ቦርድ አስወስነዉ ግዢ እንደሚፈፅሙ ገልፀዋል። ተቋማቱ ጨምረዉ እንደገለፁት በግዢ ኤጀንሲ በኩል የሚደረጉት ግዢዎች በሰዓቱ ስለማይደርሱ እና ችግሩም ጊዜ ስለማይሰጠን በቦርድ አስወስነን ግዢ ለመፈፀም እንገደዳለን ብለዋል። ግዢ ኤጀንሲም በበኩሉ ተቋማቱ በጊዜ የግዢ ጥያቄ አያቀርቡልንም የሚል ወቀሳ ሰንዝሯል።
በመጨረሻም ዋና ኦዲተሩ ገመቹ እንደዚህ ዓይነት መድረኮች ዘግይተዋል። ቀደም ቢሉ ኖሮ ብዙ የሕዝብ እና የመንግሥት ንብረትን ከብክነት መታደግ ይቻል እንደነበር አስታውሰው፤ ነገር ግን ጊዜው ስለረፈደ በ2011 ማስተካከል እንደማይቻል አስታውቀዋል. አያይዘዉም እስካሁን ድረስ ባሉት ተከታታይ ዓመታት ምንም በኦዲት በኩል ለዉጥ የለም ብለዋል። በውይይቱም እንደመፍትሄ ከተቀመጡ ነጥቦች መካከል ምሁራን በአስተዳደራዊ ሥራዎች እንዳይገቡ የሚለዉ ሲሆን ይህም በጥናትና ምርምር ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የታሰበ ነዉ. ሌላዉ ደግሞ ተቋማቱ የዉስጥ ገቢያቸዉን ለመንግሥት አሳዉቀዉ በገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር በኩል መጠቀም እንዳለባቸዉ ተጠቁማል. በዚህ አካሄድ ከዚህ በፊት የታዩትን የኦዲት ክፍተቶች በተወሰነ ደረጃ ይቀንሳል የተባለ ሲሆን በግዢም በኩል ለተነሱት ክፍተቶች ሁሉም ተቋማት ሕጋዊ አካሄድን የተከተለ ግዢ እንዲፈፅሙና ሁሉም ግዢዎች በግዢ ኤጀንሲ በኩል ማለፍ እንዳለባቸው መግባባት ላይ ተደርሷል፡፡
ዋና ኦዲተር ከዚህ ቀደም በ2007 የበጀት አመት በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የ64 ሚሊዮን ብር የኦዲት ክፍተት እንዳለ ያሳወቀ ሲሆን በዚሁ ዩኒቨርስቲ ለአንድ የህንድ ዜግነት ላላቸዉ መምህር በወር 86,755 ብር ድረስ ደሞዝ እንደሚከፈል ያነሳበት ሁኔታ የሚታወስ ነዉ። በተጠቀሰዉ በጀት አመት በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በጅማ፣ በወላይታ፣ በደብረ ብርሃን እና በደብረ ታቦር ዩኒቨርስቲዎች ዉስጥ ለመምህራን ከተከፈሉ ጥቅማ ጥቅሞች፣ የዉሎ አበሎች፣ ከመደበኛዉ ዉጭ ፈተና ወረቀቶችን ለማረም እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ 56.38 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ሲልም ዋና ኦዲተር አሳዉቋል። አያይዘዉም ጅማ ዩኒቨርስቲ ተገቢዉ ሰነድ ባልተሟላበት ሁኔታ የ47 ሚሊዮን ብር ግዢ መፈፀሙም ተጨምሮ ተገልጿል።
ለመንግሥት የከፍትኛ ትምህርት ተቋማት መምህራን የትርፍ ጊዜ ክፍያ ተመሳሳይነት እንዲኖው የሚያስችል ሕጋዊ የአሰራር ሥርዓት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ እንዲጸድቅ ጥረት እየተደረገ መሆኑም ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here