በ1 ቢሊየን ብር የመንገድ ላይ ምልክቶችና ጠቋሚዎች ሊሠሩ ነው

0
386

በስድስት ከተሞች ላይ በአንድ ቢሊየን ብር ወጪ ለሚገነባው የአድራሻ ካርታ እና የአድራሻ ምልክት ጠቋሚዎች ስድስት አገር በቀልና የውጪ ድርጅቶች እየተወዳደሩ መሆኑ ታወቀ። በጀቱም ሙሉ በሙሉ በፌደራል መንግሥት ይሸፈናል። ምልክቶች የሚገነባባቸው ከተሞችም ድሬዳዋ፣ ሐረር፣ መቀሌ፣ አዳማ፣ ባሕር ዳር እና ሐዋሳ ሲሆኑ ግንባታውም አንድ ቢሊየን ብር እንደሚፈጅ ታውቋል።
በፌደራል የተቀናጀ የከተማ መሬት መረጃ ፕሮጅክት ጽሕፈት ቤት የመረጃ አያያዝ ዳሬክተር ያሬድ ተሾመ “ስድስቱ ከተሞቹ ባላቸው ስፋት እንዲሁም የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሁኔታ ሞዴል በመሆናቸው ተመርጠዋል” በማለት ከተሞቹን የማሰስፋፋት ሥራ ለመሥራት ጨረታ ጥቅምት 29/2011 መውጣቱን አስታውሰዋል። በጨረታውም 8 ድርጅቶች የተሳተፉ ሲሆኑ ከነዚህም መካከል ሁለቱ መስፈርቱን ባለሟሟላት ከውድድሩ እንዲወጡ ሲደረግ የተቀሩት ስድስት ተሳታፊዎች በውድድር ላይ ናቸው። “ጨረታውም ጥር 6 እንደሚጠናቀቅ ብናሳውቅም ተወዳዳሪዎቹ ይራዘምልን የሚል ጥያቄ በማቅረባቸው” ለትንሽ ቀናት ሊራዘም እንደሚችል ያሬድ ጨምረው ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የተቀናጀ የመሬት መረጃ ፕሮጀክት ቢሮ በስድስት የተለያዩ ከተሞች የቤት ቁጥር እንዲሁም አቅጣጫ ጠቋሚ ምልክቶችን ለመሥራት እንቅስቃሴ እንደሚጀምር እና ፕሮጀክቱንም በከተማ ልማት ቤቶች ሚኒስቴር እና የፌደራል ከተማ መሬትና መሬት ተያያዥ ነክ ኤጀንሲ ከክልል መሬት አስተዳደር ቢሮዎች ጋር በማቀናጀት ይተገበራል። ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ በ2020 ሀያ ሦስት ከተሞች ላይ የከተማ ምልክቶችን መገንባት የተያዘው ዕቅድ አካል ሲሆን ሥራውንም ለማስኬድ የሕግ ማዕቀፍ ወጥቷል። ከተሞቹ ላይ የሚሠራው የማስፋፋት ሥራ እሳት አደጋን ታሳቢ አድርጎ የሚሠራ ሲሆን ምልክቶቹ የከተሞችን ትራንስፖርትና መረጃ ያጠናክራሉ ተብሎም ይጠበቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here