የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ሰኞ፣ ታኅሣሥ 29 ለሚከበረው የገና በዓል እስከ 3500 የዳልጋ ከብት፣ የግና ፍየል እርድ አገልግሎትን ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታወቀ። ከዚህ ቀደም የበግ ሥጋን ለተጠቃሚዎች ያቀርብ የነበረው ድርጅቱ ይህን አገልግሎት ማቋረጡንም ገልጿል።
ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት በአማካይ በቀን አንድ ሺሕ 600 የዳልጋ ከብቶችን እና አንድ ሺሕ 500 መቶ በግና ፍየል የማረድ አቅም ያለው ቢሆን ከበዓላት ውጭ ባሉ ቀናት እየሠራ ያለው ከአቅሙ በታች መሆኑን የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አታክልቲ ገብረሚካኤል ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ይሁንና በፆም መግቢያና መውጫ ወይም የበዓል ቀናት የእርድ አገልግሎት ፍላጎቱ ከፍተኛ እንደሚሆን ያነሱት ኃላፊው ለዘንድሮው የገና በዓል እስከ 3500 የእርድ አገልግሎትን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አመልክተዋል። ለአገልግሎቱም በአንድ በሬ 500 ብር የሚያስከፍል ሲሆን ለበግና ለፍየል ደግሞ 85 ብር ያስከፍላል ተብሏል።
ድርጅቱ ከዚህ ቀደም ከሚሰጠው የእርድ አገልግሎት ባለፈ በተለይም ለበዓል ቀናት በጎችን በራሱ አርዶ ሥጋን ለገበያ ያቀርብ የነበረ ቢሆን ይህን አገልግሎት ከ2010 ወዲህ ማቋረጡን የሕዝብ ግንኑነት ኃላፊው አስታውቀዋል። አሁን ላይ ድርጅቱ ለገበያ ያቀርብበት የነበረውን ሱቅ ለግለሰብ ማከራየቱን አክለዋል።
የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ጤንታቸው በመርምራ የሚረጋጡ የሥጋ ከብቶችን የእርድ አገልግሎት ለመስጠት በ1949 መቋቋሙ ይታወቃል።
በተያያዘ ዜና በበዓላት ወቅት ጎልቶ የሚታየውን የሕገ ወጥ እርድ ለመከላከል ዝግጅት ማድረጋቸውን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ እና የደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽሕፈት ቤት አስታውቀዋል።
ሕገ ወጥ እርድን ለመከላከልና ተገቢውን የሕግ እርምጃ ለመውሰድ በ2010 አዲስ ደንብ ተዘጋጅቶ በዚህ ዓመት ወደ ተግባር መግባቱን ያመለከቱት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አሰግደው ኃይለ ጊዮርጊስ እንደተናገሩት ሕገ ወጥ እርድ ሲያካሂዱ በተገኙ 54 ነጋዴዎች ላይ እርምጃ ተወስዷል።
በተለይ የሥጋ ንግድ በስፋት ከሚከወንባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው ፒያሳ በተደረገ ፍተሻ በስፍራው ካሉት ሥጋ ቤቶች ሦስቱ በቄራ ያልታረደ ሥጋን ሲያቀርቡ በመገኘታቸው ሥጋው ተወርሶ እንዲወገድ መደረጉንም አክለዋ። ይሁንና ቢሮው ሕገ ወጥ እርድን በመከላከል ረገድ እጥረት እንዳለበት የሚያነሱ ወገኖች ቢሮው በሚገኝበት ፒያሳ አካባቢ የተገደበ ሥራ እንደሚሠራም ይተቻሉ።
የአዲስ አበባ ደንብ ማስከበር አገልግሎት ጽሕፈት ቤት የቁጥጥር ባለሙያዋ አበባ መስተያየት እንደሚሉት ደግሞ አዲሱ ደንብ ባልነበረበት 2010 አንድ መቶ 67 ሕገ ወጥ እርድ ሲፈጸም ተይዟል።
በሕገ ወጥ እርድ የተሠማሩ አካላት የተያዙት በኅብረተሰቡ ጥቆማ መሆኑን የተናገሩት የቁጥጥር ባለሙያዋ በዓሉን ምክንያት በማድረግ ሕገ ወጥ እርድ ሊሰፋ ስለሚችል ኅብረተሰቡ የሚጠቀመው ሥጋ ላይ ጥንቃቄ እንዲያደርግና በጥቆማ በኩልም የተለመደ ድጋፉን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
ደንብ ማስከበር በተቋቋመበት አዋጅ ሕገ ወጥ እርድ ከሚያስፈጽሙ ነጋዴዎች ይልቅ ለሚያርድበት ሙያዊ አገልግሎት ተከፍሎት ሲያርድ የተገኘን ግለሰብ የበለጠ የሚቀጣ መሆኑ ሲያስተቸው እንደነበር ታወሳል።
ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011