በኢትዮጵያ እየታየ ባለው የፖለቲካ ለውጥ ተፅዕኖ ያሳደረው በፖለቲካ ምኅዳሩ ላይ ብቻ ሳይሆን በምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴውም ጭምር ነው። መንግሥት በገበያ ተሳትፎው እና መዋዕለ ንዋይ ማፍሰስ ረገድ የሚኖረው ተሳትፎ እንደሚቀየር የተነገረ ከመሆኑም በላይ በፖለተካዊ ኹነቶች ምክንያት እና በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት መርካቶ ተቀዛቅዛለች የሚለው ሳምሶን ብርሃኔ፣ ነጋዴዎችን እና ባለሙያዎችን በማናገር የመርካቶ መቀዛቀዝ በጥቅሉ ምጣኔ ሀብት (‘ማክሮ ኢኮኖሚ’ው) ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎ አቅርቦታል።
ለ25 ዓመታት በመርካቶ ገበያ ነጋዴነት ያሳለፉት ሚሊዮን ያሲን በምዕራብ ሆቴል አካባቢ የሚገኝ መጋዘን ባለቤት ናቸው። የእርሳቸውና በአካባቢው የሚገኙ መጋዘኖች እንቅስቃሴ በገበያው ያለው ሁኔታ ነፀብራቅ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም።
ገበያው ሞቅ ሲል፣ መጋዘኑን የሚጠቀሙት ሰዎች ይበዛሉ፤ ሲቀዘቅዝ ደግሞ ተጠቃሚዎች ይቀንሳሉ። ይህ ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በነበረው የገበያ ሁኔታ የተለመደ ቢሆንም፥ አሁን ግን ያጋጠመው ከወትሮው ለየት ያለ ነው።
የንግድ መቀዛቀዝና ሞቅ ማለት የተለመደ ነገር ቢሆንም፥ አሁን ያጋጠመው ችግር ግን ከዚህ ቀደም ከነበረው ለየት ማለቱን የሚናገሩት ሚሊዮን “ከዚህ በፊት በነበረው የሥራ እንቅስቃሴ ሥራ በሌለበት ወቅት እንኳን መጋዘኑ ለሳምንት እንኳን ባዶ ሆኖ” እንደማያውቅ ይናገራሉ።
“አሁን ባለው የንግድ እንቅስቃሴ በደህናው ጊዜ እንኳን ይህንን ማሳካት ይቸግራል። ቢያንስ መጋዘናችንን ለማከራየት ከሁለት እስከ ሦስት ወራት ይወስድብናል” ሲሉ የሥራ መቀዛቀዙን ተከትሎ ገቢያቸው በከፍተኛ መጠን እንደቀነሰ በመግለጽ ሚሊዮን ያማርራሉ።
የገቢ መቀነስ እና የንግድ መቀዛቀዝ ችግር ያጋጠማቸው ሚሊዮን ብቻ አይደሉም። ከ30 ሺህ በላይ ሱቆች በሚገኙበት እና በአፍሪካ ግዙፉ ክፍት ገበያ መርካቶ፥ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ነጋዴዎች የሚሊዮንን ሐሳብ ይጋራሉ። በእርግጥ፣ በቅርብ ቀናት ውስጥ ወደ መርካቶ ብቅ ያለ ማንኛውም ሰው የመርካቶን መቀዛቀዝ ለመረዳት ጊዜ አይወስድበትም።
የመሰላቸት ስሜት የሚነበባቸው እና የተከዙ ነጋዴዎችን፣ ገበያተኛ የሌለባቸው ሱቆችን እንዲሁም ቁጭ ብለው አላፊ አግዳሚውን ‘የሥራ ያለህ’ የሚሉ ወዝ አደሮችን በመርካቶ ማግኘት የተለመደ ነገር እየሆነ መጥቷል። በአመዴ ገበያ ያለው ሁኔታም እንደ ተጨማሪ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።
እንኳንስ እንዳሁኑ ኦና ሊሆን ቀርቶ፥ ነጋዴዎች ሰላምታ ለመለዋወጥ የሚሆን ደቂቃ ከዛሬ አምስት ወይም ስድስት ዓመታት በፊት ማግኘት ይቸገሩበት እንደነበረ የሚናገሩለት የአመዴ ገበያ ንግድ ልውውጥ መቀዛቀዝ ከጀመረ ሰንበትበት ብሏል። አሁን ያጋጠማቸው ችግር ግን ከወትሮውም ለየት ያለ ነው ሲሉ ነጋዴዎቹ ይናገራሉ።
ሥራ ቢጠፋ ዓመት በዓል ቀረብ ሲል ቢያንስ በቀን እስከ 30 ጥንድ ጫማ ይሸጥ ነበር ያሉት በአመዴ ገበያ፣ በጫማ ንግድ ላለፉት 15 ዓመታት የሠሩት መንግሥቱ ማረኝ፣ “አሁን ላይ ከሦስት ጫማ በላይ” እንደማይሸጡ ይናገራሉ።
እንደ ሚሊዮን ያሉ በውጭ ንግድ ላይ ኑሯቸውን መሠረት ያደረጉ ነጋዴዎች የውጭ ምንዛሬ እጥረት የተነሳ የተከሰተውን የዕቃዎችና የሸቀጣ ሸቀጦች እጥረት ለንግዳቸው መቀነስ እንደ ዋነኛ ምክንያት ሲገልጹ፣ ሌሎች እንደ መንግሥቱ ያሉ ቸርቻሪዎች ደግሞ የመንገድ ላይ ንግድ መስፋፋትን እንደ ዋነኛ ምክንያት ያነሳሉ።
ይሁን እንጂ ሁሉም የሚሥማሙበትና ከምንም በላይ እንቅፋት የሆነባቸው ነገር ቢኖር፥ በአገሪቷ ያለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ነው።
ሰላም ማጣት
የፖለቲካ አለመረጋጋት በኢትዮጵያ የተለመደ ነገር ከሆነ አምስት ዓመታት አልፎታል። በ2006 የፀደቀው አዲስ አበባን እና በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ የኦሮሚያ ከተሞችን ያጣመረ ማስተር ፕላን መውጣትን ተከትሎ በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ዘመን የጀመረው አለመረጋጋት፣ ከሥልጣናቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ በመጡት ዐብይ አሕመድ (ዶ/ር) ጊዜ መጀመሪያ በረድ ቢልም የአመፅ እንቅስቃሴ እና ውጥረቱ ግን ዳግም በከፋ ሁኔታ ሊቀጥል ችሏል።
ምንአልባትም፣ ከሌሎች ከተሞች አንፃር ሰላም በሆነችው አዲስ አበባ ላይ የሚገኘው መርካቶ ገበያ ላይ ይህ ምን ተፅዕኖ አለው የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል። ለዚህ መልስ ማግኘት ከባድ አይደለም። ከዛሬ ዐሥር ወይም 15 ዓመታት በፊት የመርካቶ ነጋዴዎች ዋነኛ ደንበኞች በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ካሉ ከተሞች የሚመጡ ነጋዴዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ፣ ይህ ለዓመታት የቆየ ልማድ ተቀይሮ መርካቶ ቁርኝቱን ከሰሜን እስከ ደቡብ እና ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ከሚገኙ የክፍለ ሀገር ነጋዴዎች ጋር አድረጓል።
ይህም ማለት፣ በማንኛውም ክልልም ሆነ ከተማ የሚኖር አለመረጋጋት ተፅዕኖ መርካቶ ገበያ ላይ ለመታየት ጊዜ እንደማይወስድበት ያሳያል። የብርድ ልብስ እና የተለያዩ ጨርቃ ጨርቅ ውጤቶች የጅምላ ነጋዴ የሆነው ዮናታን ደጉ ገጠመኝ ለዚህ ማሳያ መሆን ይችላል። በያዝነው ወር መጀመሪያ ነበር ዮናታን አክሱም ለሚገኘው የችርቻሮ ነጋዴ ለሆነው ደንበኛው ዕቃ የጫነው።
በወቅቱ ምንም ገንዘብ ያልተቀበለው ዮናስ ዕቃውን ሲጭን ምንም ዓይነት እክል ይገጥመኛል ብሎ አላሰበም ነበር። ነገር ግን፣ የእሱንና የሌሎች ነጋዴዎች ዕቃ ይዞ ወደ አክሱም በመጓዝ ላይ የነበረው የጭነት መኪና አፋር ላይ ቆሞ ጭነቱን እንዲያራግፍ ይነገረዋል።
ከዚያም ለዐሥር ቀናት ያለምንም ምክንያት እዚያ በሚገኙ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት ተቆጣጣሪዎች እንዲቆም ይደረጋል። “በዚህ መሐል፣ ዕቃዬ ጠፋ ብዬ ደምድሜ ነበር፤ ከዚያ በኋላ ችግሩ ቢፈታም፣ የምልከው ዕቃ ሊዘረፍ ወይም ሊጠፋ ይችላል በሚል ዕሳቤ፣ ያለኝ የመተማመን ስሜት ወረደ” ሲል ዮናስ ያገጠመውን ችግር ይገልጻል።
ዮናስም ሆነ እንዲህ ዓይነቱ ችግር የገጠማቸው ወይም ከገጠማቸው የተማሩት ነጋዴዎች፣ ከደንበኞቻቸው ጋር ያላቸውን የሥራ ሁኔታ ለመቀየር ተገደዋል። “በእንዲህ ዓይነቱን ችግር እና ፍራቻ፣ ብዙ የመርካቶ ነጋዴዎች በተለያዩ ክፍለ ሀገራት ላሉ ነጋዴዎች የዱቤ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን” ዮናስ ይገልጻል።
ይህንንም ተከትሎ፤ ብዙ የክልልና የሌሎች ከተሞች ነጋዴዎች ወደ መርካቶ መምጣት መቀነሳቸውን፣ እንዲሁም ጥቂቶች ማቆማቸውን ዮናስ የራሱን አጋጣሚ በመጥቀስ ያስረዳል። “ወደ እኔ የሚመጡት የክልሎችና ከተሞች ነጋዴዎች የዛሬ ዓመት ከነበረው በ70 በመቶ ቀንሰዋል ብል ማጋነን አይሆንም” ይላል ዮናስ።
ይህ ዓይነቱ ችግር፤ ለኢትዮጵያ አዲስ አይደለም። በአማራ እና በትግራይ ክልል አመራሮች መቃረን ሳቢያ፣ ከአማራ እና ከሌሎች ክልሎች የሚገቡ ሸቀጣ ሸቀጦች እንደ ወትሮው መተላለፍ አልቻሉም። በተጨማሪም በሁለቱ መካከል ያለው የትራንስፖርት አገልግሎት በመቋረጡ መተላለፊያ መንገድ ለመቀየር ተገደዋል።
በዚህ ይተዳደሩም የነበሩ የክልሎቹ ነዋሪዎች፣ የሥራቸውን ዘርፍ ለመቀየር እንዲሁም ሥራ አጥ እስከመሆን ለመድረስ ተገደዋል። ተመሳሳይ ችግር ሌሎች ክልሎችን በሚያገናኙ ከተሞች ላይ ከተከስተ ሰንበትበት ብሏል። ከፍተኛውን የመርካቶ ክፍል፣ ማለትም ከአውቶብስ ተራ መስጊድ እስከ ጣና ገበያ ድረስ የሚሸፍነው የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 8 ንግድ ቢሮ ምዝገባና ፈቃድ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ጉግሣ ኡርጌሣ ገለጻ የፀጥታው ችግር እስካልተፈታ ድረስ፣ መርካቶ ውስጥ ያለው መቀዛቀዝ ሊቀጥል እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ፤ የመርካቶ የንግድ ሁኔታ የሚወሰነው የሌሎች ከተሞችና ክልሎች ሰላም ላይ ነው በማለት አክለዋል።
የውጭ ምንዛሬ እጥረት
መርካቶ ውስጥ ከውጭ ምንዛሬ እጥረት ተፅዕኖ ነጻ የሆነ ነጋዴ እንደ ማግኘት ከባድ የሆነ ነገር የለም ቢባል ማጋነን አይሆንም። እንደ ሚሊዮን ያሉ ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎች እጥረትን ተከትሎ መጋዘኖቻቸው የተራቆቱባቸው ነጋዴዎች አንስቶ እስከ ችርቻሮ መደብር ባለቤቶች ድረስ በውጭ ምንዛሬ እጥረት የተነሳ ችግር ካጋጠማቸው ዓመታት ተቆጥረዋል። ችግሩ የፀናባቸው ጥቂት የማይባሉ ነጋዴዎች ደግሞ ሥራቸውን ለማቋረጥ ወይም ዘርፍ ለመቀየር ተገደዋል። ሌሎች በበኩላቸው አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት ይፍጨረጨራሉ።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው አንድ ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ በመርካቶ የሚገኙ የጨርቃ ጨርቅ ወጤቶችን አስመጪ ከዚህ ጎራ ውስጥ ይካተታሉ። “ከዛሬ ዓመት ወይም ሁለት ዓመታት በፊት፣ በሕጋዊው መንገድ ማለትም ከባንኮች ዶላር ለማስፈቀድ ዕድለኛ ለሆኑት ቢያንስ ስድስት ወራት ይወስድ ነበር” ያሉት አስመጪው፥ “አሁን ግን በዓመትም ለማስፈቀድ ከባድ” መሆኑን ያወሳሉ። “በዚህም የተነሳ የሚፈለገውን ያህል ዕቃ ማምጣት” አለመቻሉን ይገልጻሉ።
ከዚህ ቀደም ለእንዲህ ዓይነቱ ችግር አዲስ ያልሆኑት ነጋዴው “በባንክ ማግኘት ያልቻሉትን የውጭ ምንዛሬ በተለምዶ “ብላክ ማርኬት” ከሚባለው “ትይዩ ገበያ” ይወስዱ እንደነበር ያወሳሉ። ነገር ግን ትይዩ ገበያውን ለማዳከም፣ ከባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ወዲህ በብሔራዊ ባንክ የወጣውን መመሪያ ተከትሎ፥ የውጭ ምንዛሬው የሚፈቀደው አስመጪው በሚያመጣው ዕቃ የዓለም ዓቀፍ ዋጋ ስለሆነ፣ ሰው ይህንን አማራጭ መጠቀም ማቆሙን ይገልጻሉ።
ይሁን እንጂ ችግር መፍትሔ ይወልዳል እንዲሉ ነጋዴዎች ሌሎች ክፍተቶችን በመጠቀም የውጭ ምንዛሬ ፍላጎታቸውን ማሳካት እንደቀጠሉ መረጃዎች ያሳያሉ።
የውጭ ዜጎችና ድርጅቶች፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ከአንድ ዓመት በላይ የኖሩ እና በሥራ ላይ ለቆዩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚፈቀደው የውጭ ምንዛሬ አንዱ ምንጭ ሲሆን፣ የተለያዩ ዕቃዎችን ወደ ውጭ በመላክ ከሚያገኙት የውጭ ምንዛሬ 30 በመቶ ዕቃዎችን በመላክ ገቢ የሚያገኙት ሌላ ሟሟያ ናቸው።
እንደ ምንጮቻችን ገለጻ፣ አንዳንድ ላኪዎች በዶላር እና ሌሎችም ምንዛሬ ከብሔራዊ ባንክ ከሚወጣው የውጭ ምንዛሬ ተመን ላይ እስከ 10 ብር ያተርፋሉ። የአንዳንድ ባንኮች ቅርንጫፍ ኃላፊዎችም እንዲህ ዓይነቱ የሕገ ወጥ የውጭ ምንዛሬ ግብይት ውስጥ እንዳሉበት መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህ ዓይነቱ ክፍተት የውጭ ምንዛሬ ገበያው ላይ ያለው ቁጥጥር ፍትሓዊ ክፍፍልን ከማረጋገጥ አንፃር ደካማ መሆኑን ያሳያል ያሉት ሚሊዮን፣ አሁን መርካቶ ላይ ላጋጠመው የዕቃ እጥረት ምክንያት ነው ብለዋል። በርግጥ የውጭ ምንዛሬ እጥረት መርካቶን ብቻ አይደለም ያዳከመው። ከመርካቶ ውጪ ያሉ ሌሎች ነጋዴዎችም የተመሳሳይ ችግር ተጠቂዎች ናቸው።
በኢትዮጵያ ያለው የውጭ ንግድ ገቢ አለማደግ ዋነኛው የውጭ ምንዛሬ እጥረት መንስዔ ነው ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ። በርግጥ፣ የአገሪቷ ዓመታዊ የውጭ ንግድ ገቢ ከሦስት ቢሊዮን ዶላር ከፍ ሊል ባለመቻሉ ከገቢ ንግድ ወጪ መጨመር ጋር ተዳምሮ እጥረቱን አባብሶታል።
በተጨማሪም አሁን መርካቶ ላለው የገበያ መቀዝቀዝ፥ ከወራት በፊት የነበረው የውጭ ምንዛሬ ክምችት አነስተኛ መሆን እንደ ምክንያት ይገለጻል። የዛሬ ስድስት ወር ገደማ የውጭ ምንዛሬ ክምችቱ የኢትዮጵያን የአንድ ወር የገቢ ንግድ የማይሸፍን እንደነበር በወቅቱ ከመንግሥት አፈትልከው የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ። ይህ ቁጥር አሁን ከፍ ብሎ፣ ክምችቱ የአንድ ወር ከ18 ቀናት ገቢውን መሸፈን ቢችልም እጥረቱ ሊፈታ አልቻለም።
በምጣኔ ሀብቱ መዳከም የመንግሥት ሚና
በኢትዮጵያ ትልቁ ቀጣሪ የሆነው መንግሥት የአገሪቷ ኢኮኖሚ ላይ ከማንም በላይ ትልቁ ባለድርሻ ነው። በተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት የተደነቀውን በአማካይ ከዘጠኝ በመቶ በላይ ዕድገት ባለፉት ዐሥር ዓመታት ለማስመዝገብም የተቻለው መንግሥት አንዱ አልሚና መዋዕለ ንዋይ አፍሳሽ በመሆኑ እንደነበር በመንግሥትም ሆነ እንደ ‘ኢንተርናሽናል ሞንታሪ ፈንድ’ ያሉ ድርጅቶች መረጃዎች ያሳያሉ።
አመቺ ባልሆኑ ሕጎች፣ ያልተሟሉ እና ደካማ አገልግሎቶች እንዲሁም አሰልቺ/አድካሚ ሂደቶች ምክንያት ማደግ ያልቻለው የግሉ ዘርፍ ሚናው አነስተኛ ሆኖ ሲቀጥል፣ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ተከታዩ ኢሕአዴግ መር መንግሥት በኢኮኖሚው ያለው ተፅዕኖ ጠንክሮ ቆይቷል።
ይሁን እንጂ፣ በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የሚመራው መንግሥት በዚህ መቀጠል የፈለገ አይመስልም። ገና ወደ መንበረ ሥልጣኑ ከመጡ ሦስት ወራት ሳይሞላቸው መንግሥት በምጣኔ ሀብቱ ላይ ያለውን ተፅዕኖ እንደሚቀነስ በግልጽ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ እንደ አብነትም መንግሥት እንደ ኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ግድቦች፣ ስኳር ፋብሪካዎችንና ሌሎችንም በመንግሥት ይዞታ ሥር ያሉ ድርጅቶችን ለግል ባለሀብቶች ለማስተላለፍ መወሰኑን ገልጸው ነበር።
በዚህም አላበቁም። የዘገዩ በተለይ በተለምዶ ‘ሜቴክ’ በተባለው ከኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሥር የነበሩ ፕሮጀክቶችን፣ በግንባታ ላይ የነበሩትን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን እና የስኳር ፋብሪካዎችን ጨምሮ ሌሎችንም እንዲቀሙ አድርገዋል። ከዚህ በፊት የተጀመሩት ሳይጠናቀቁ ተጨማሪ ግንባታ እንዳይካሄድም መንግሥታቸው ወስኗል።
በአንድ በኩል፣ ይህ የመንግሥት ወጪ እንዲቀንስ እንዲሁም የበጀት ጉድለቱ እንዳይጨምር ትልቅ ሚና ቢጫወትም፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳድሯል። መርካቶ ላይ ለተፈጠረው የንግድ መቀዛቀዝ አንድ ምክንያት መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ፕሬዘደንትና የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት ጣሰው ወልደሀና (ፕሮፌሰር) “በዚህ ዓመት የተመደበው የካፒታል በጀት አነስተኛ መሆን ከመንግሥት ግንባታዎች መቀዛቀዝ ጋር ተዳምሮ ለተፈጠረው መቀዛቀዝ ዋነኛ ምክንያት” ነው ብለዋል።
“በዚህም የተነሳ፣ መንግሥት ኢኮኖሚ ውስጥ የለቀቀው የብር መጠን ስላነሰ ፍላጎት አልተፈጠረም፤ በተጨማሪም ነጋዴዎችና ተጠቃሚዎች እጅ ያለው ገንዘብ መጠን አንሷል። ይህም መቀዛቀዝ እንዲከሰት ያደርጋል” ብለዋል።
ይህ በኢትዮጵያ ያሉ የግል ባለሀብቶች ከፖለቲካው አለመረጋጋት ጋር ተያይዞ ገንዘባቸውን በሥራ ላይ ለማዋል ካላቸው አነስተኛ ፍላጎት ጋር ተዳምሮ የንግዱን እንቅስቃሴ ደካማ እንዳያደርገው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይሰጋሉ።
በርግጥ ከዚህም በላይ የአዲስ ማለዳውን የምጣኔ ሀብት ተንታኝ ዓለማየሁ ገዳን (ዶ/ር) የሚያሰጋቸው በቅርቡ መንግሥት በሙስና የተጠረጠሩ ባለሥልጣናትና ሌሎች ነጋዴዎች ላይ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ የሚፈጠረውን ክፍተት ነው። ይህንን ተከትሎ ድንጋጤ በመፈጠሩ ምክንያት ምጣኔ ሀብቱ ላይ ያላቸው ተሳትፎ ወዲያውኑ የከሰመ አለ። በተለያዩ ሕገ ወጥ ተግባራት ላይ ተሠማርተው የነበሩ ቢኖሩም እንኳን፥ በኢኮኖሚው ላይ ያላቸው ተፅዕኖ የማይካድ ነው። እነዚህ ሰዎች ሲወጡ ንግድ መቀዝቀዙ አይገርምም።
መርካቶም ይሁን ምጣኔ ሀብቱ እንዴት ይነቃቁ?
“በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ’ እንዲሉ፣ በቅርቡ ከ43 እጥፍ በላይ የኪራይ ዋጋ ጭማሪ የተደረገባቸው በመርካቶ ያሉ እንደ ሚሊዮን ያሉ ከቤቶች ኮርፖሬሽን የተከራዩ ነጋዴዎች፥ መንግሥት ሰላም ማስከበር ባለመቻሉ ምንም ዓይነት ለውጥ በንግድም ሆነ በምጣኔ ሀብቱ ጉዳይ ማምጣት ባልተቻለበት ወቅት የኪራይ ማስተካካያ ዋጋ ማድረጉ እሳት ላይ ነዳጅ ከማፍሰስ አይተናነስም። ጥናት እንኳን በአግባቡ ሳያደርግ፣ ሕዝቡን ሳያማክሩና የአገሪቷን ፖለቲካዊና የንግድ ሁኔታ ከግምት ውስጥ ሳይስገቡ ኪራይ መጨመሩ የበለጠ መቀዛቀዙን ያባብሰዋል” ሲሉ ሚሊዮን ያስጠነቅቃሉ።
ሌላው የንግድ መቀዛቀዝ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ነው ብለው የሚያምኑት የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ተኬ ዓለሙ በበኩላቸው፣ ችግሩን በአጭር ጊዜ ለመፍታት አዳጋች ነው ብለዋል። መንግሥት ለግሉ ዘርፍ ማነቆ የሆኑ ችግሮችን በመፍታት የወጪ ንግድ ገቢውን መጨመር ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ያሳስባሉ።
ይህንን ማድረግ እንደተሳነው የተረዱ ባለሙያዎች በበኩላቸው መንግሥት የገቢ ንግድ በመቀነስ ከውጭ የሚመጡ ዕቃዎችን አገር ውስጥ ማምረት ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለበት ይመክራሉ።
በሌላ በኩል የምጣኔ ሀብት ጉዳዮች ተንታኙ ዓለማየሁ መንግሥት በቅርቡ የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ከገበያ የወጡ ሕገወጥ ነጋዴዎች ያላቸውን ሚና በመረዳት፣ ክፍተት እንዳይፈጠር፣ መንግሥት በወጡት ፈንታ ለመተካት እርምጃ መውሰድ አለበት። ምጣኔ ሀብቱ ላይ ያለውንም ሚና ቀስ በቀስ እንጂ በአንድ ጊዜ ማቋረጥ እንደሌለበት ያሳስባሉ።
ጣሰውም በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። በመንግሥት የሚመሩ ፕሮጀክቶችን መቀነሱ ተገቢ ቢሆንም የግሉ ዘርፍ እስኪጠነክርና እስኪተካ ድረስ ማቋረጡን በሂደት ኢኮኖሚው ላይ ክፍተት ሳይፈጥር መሆን ይገባዋል ይላሉ። ነገር ግን ከዚህ በላይ አሳሳቢ የሆነው ነገር የአገሪቷ ሠሰላም መሆን ነው ይላሉ ጣሰው።
‘’አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ውስጥ ያለው ማን ነው? ከሚለው በላይ የአገሪቷ ሰላም ወሳኝ ነው’’ ያሉት ጣሰው ነጋዴዎች፥ ወደ ውጭ የሚልኩትን ጨምሮ፣ ንግዳቸው እየተቋረጠ ወይም እየተስተጓጎለ መሆኑን ያስረዳሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 8 ታኅሣሥ 27 ቀን 2011