በተለያዩ ምክንያቶች ከአገራችን ወጥተው በባዕድ አገራት የሚገኙ ቅርሶችን በማጥናት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር በወዳጅነት እና በመግባባት መንፈስ፤ ያም ካልሆነ ዓለም አቀፍ ሕግን ማዕከል አድርጎ ቅርሶቹ ወደ አ”ገራቸው እንዲመለሱ ማድረግን ዓላማው ያደረገ የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ኅዳር 17ቀን 2013 በሸራተን አዲስ ሆቴል ተመስርቷል።
በምስረታ ጉባዔው ላይ ተገኝተው መድረኩን የከፈቱት የኢፌዲሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ክብርት ኂሩት ካሳው (ዶ/ር) “ አገራችን ኢትዮጵያ እንደ ምድረ ቀደምትነቷ የብዙ ባህልና ቅርስ ባለቤት ናት”ያሉ ሲሆን፤ ቀደምት አባቶቻችን በጥበብ የተራቀቁባቸውን ብዙ ቁጥር ያላቸው የአገራችን ቅርሶች፡- ስዕላት፣ ንዋዬ ቅድሳት፣ መጻሕፍት፣ የወታደርና የሢቪል አልባሳት፣ የጦር መሣሪያዎች እና ሌሎችም ቅርሶቻችን በስጦታ፣ በስርቆት እና በጦርነት ዝርፊያ ወደ ውጭ አገራት ሄደዋል ብለዋል።
በተጨማሪም ዛሬ በይፋ የተመሠረተው የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ ተጠሪነቱ ለባህልና ቱሪዝም ሚንስቴር መሥሪያ ቤት መሆኑንና የአገራችንን የቅርስ ሀብቶች ከያሉበት አጥንቶ እንዲያስመልስ ታላቅ አገራዊ አደራ የተጣለበት ብሔራዊ ኮሚቴ ነው ሲሉ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ቅርሶች አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ የራሱ ጽሕፈት ቤት የሚኖረው ሲሆን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር የሚኖሩ የአማካሪዎች ቡድን ይኖረዋል። ሥራውን በአጭር ጊዜ እና በተቀላጠፈ ሁኔታ ለመሥራት ያመቸው ዘንድ የተለያዬ ተግባርና ኃላፊነት ያላቸው አምስት ንዑሳን ኮሚቴዎች በሠሩ የሚያዋቅር ይሆናል። ብሔራዊ ኮሚቴው ከልዩ ልዩ ዘርፎች የተውጣጡ ምሁራን፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፣ ተመራማሪዎች እና ታዋቂ ሰዎችን ያካተተ 19 አባላት ያሉት ኮሚቴ ነው ከነዚህም መካካል ክብርት ዶ/ር ኂሩት ካሳው መጋቢ ሐዲስ እሸቱ ዓለማየሁ እና አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገ/ስላሴ ይገኙበታል።
ቅጽ 2 ቁጥር 108 ኅዳር 19 2013



