በማይካድራ በአሰቃቂ መንገድ ተገድለው የተገኙ ሰዎች ቁጥር 700 እንደሚደርስ ተነገረ

0
453

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አፈጻጸም መርማሪ ቦርድ በማይካድራ የተጨፈጨፉ ሰዎች ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል አስታውቋል።
በማይካድራ በአሰቃቂ መንገድ ተገድለው የተገኙ ሰዎች ቁጥር 700 እንደሚደርስ ፣ ነገር ግን በየጫካው እስካሁን ያልተገኙ አስከሬኖች ሊኖሩ እንደሚችሉና በዚህም የሟቾቹ ቁጥር ሊያሻቅብ እንደሚችል የቦርዱ ሰብሳቢ ለማ ተሰማ ገልጸዋል፡፡
ቦርዱ በባህርዳር፣ ጎንደር፣ ዳንሻ፣ ሁመራና ማይካድራ ከተሞች የመጀመሪያውን ዙር የመስክ ምልከታ ማድረጉን ያስታወቀ ሲሆን ፣ በአከባቢው “በጁንታው” የሕወሓት ቡድን የተፈጸመውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አብራርቷል፡፡
በሪፖርቱ ላይም “የጁንታው ቡድን” በሁመራና በማይካድራ ከተሞች የአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ ትኩረት በማድረግ እጅግ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ማድረጉን አመላክቷል፡፡
“ሳምሪ” የተባለው የወጣቶች ቡድን ይህንን አሰቃቂ ወንጀል ቢፈጽምም ፣ በአንጻሩ የትግራይ ተወላጅ ከሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል ገዳዩ ቡድን ሲያሳድዳቸው የነበሩ ሰዎችን በቤታቸው፣ በቤተክርስቲያንና በእርሻ ቦታዎች በመደበቅ የብዙ ሰዎች ሕይወት እንዲተርፍ ማድረጋቸውን መርማሪ ቦርዱ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ሪፖርቱ እንደጠቆመው ከሆነም በዳንሻ የሚገኙ የመከላከያ ሠራዊት ቤተሰቦችን በማፈን እንግልት ተፈጽሞባቸዋል፡፡
“ከሃዲው ቡድን” ለጥፋት ያሰለፋቸውና በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የዋሉ የትግራይ ልዩ ኀይልና የሚሊሻ አባላት ሰብኣዊ አያያዝ እየተደረገላቸው መሆኑንም መርማሪ ቦርዱ አስረድቷል፡፡
ቦርዱ ጉብኝቱን የጀመረባቸው የባህርዳርና የጎንደር የሲቪል አየር ማረፍያዎች ላይ የደረሰው ጉዳት አነስተኛ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ለማ ተሰማ እንዳስረዱት ከሆነም በከተሞቹ በሚገኙ ሆስፒታሎች ለመከላከያ ሠራዊትም ሆነ “ከሃዲው ቡድን” ለጥፋት አሰልፏቸው ለቆሰሉ የትግራይ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ አባላት ተመሳሳይ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው ነው፡፡

ቅጽ 2 ቁጥር 110 ታህሳስ 3 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here