ከምርጫ በፊት አገር ትቅደም!!

0
340

ምርጫን በአግባቡ ጊዜውን በጠበቀ እና ፍትሀዊ በሆነ መንገድ ማካሔድ አንደኛው የዲሞክራሲያዊ መንግሥት መገለጫ ነው። ይህ ዲሞክራሲያዊ መንግሥት ምርጫን እና የምርጫን ጊዜ ይፋ አድርጎ አስገዳጅ እና አገርን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ችግር ሲገጥመው እና ሊገጥም ይችላል ብሎ ሲያስብም በምርጫ ማካሔድ ላይ የራሱን የቻለ ውሳኔ ሊያሳልፍ ይችላል አገሪቱን ሕገ መንግሥታዊ አካሔድን በተከተለ መልኩ ።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የሚያኮራ ፍጹም ፍትሀዊ ምርጫዎችን አካሒዳለች ማለት ሚከብድ ነው። ይህንንም ተከትሎ በበርካታ ሰዎች ዘንድ አገራዊ ምርቻ ሲታወስ ሕዝብ ስልጣኑን ተጠቅሞ ይሆነኛል፣ ይመራኛል፣ ያስተዳድረኛል የሚለውን የፖለቲካ ፓርቲ በዲሞክራሲያዊ መንገድ መርጦ ስልጣን ላይ ማስቀመጥ ወይም የማውረድ አይደለም። አንዲያውም በአንጻሩ የግርግር፣ የእስር እና ግድያ ታሪኮች ናቸው ቀድመው የሚመጡት ። ይህ ደግሞ ኣመት ሔዶ ዓመት ሲመጣ ሊስተካከል ቀርቶ ጭራሹኑ የሕዝብ ድምጽ እየተዘረፈ እና እየተቀሸበ ምርጫን እውነተኛ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገለጫ ሆኖ መታሰቡ ቀስ በቀስ እንዳይዳፈንም ያስፈራል።

ይህ የምርጫ እና ተያያዥ ጉዳዮች በመጪው ምርጫ 2013 ላይ እንዳይደገሙ እና ወደ ዲሞክራሲያዊ አገር ግንባታ ግስጋሴያችን እንዳንደናቀፍ ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል። ይህም ማለት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ታሪክን መሰረት ያደረጉ ፣ ባህልን መሰረት ያደረጉ፣ ቋንቋን መሰረት ያደረጉ እና ሌሎችም ጉዳዮችን መሰረት ያደረጉ ጉዳዮች ላይ ጋራ መግባባት አይታይም። በእነዚህ ምክንያቶችም ደግሞ ብሔራዊ አለመግባባቶች አገሪቱ አሁን ያለችበትን ሁኔታ የምናየው ጉዳይ ነው። ኢትዮጵያ ከጫፍ ጫፍ ሳትናጥ እና ሳትደማ ፣ ሳትፈናቀል፣ ሳትጋጭ የታየችበት እና የረጋ አገር ለማየት ያልታደልንበትም በእነዚህ ጉዳይ ነው።

አገርን በተደጋጋሚ ሲያጋጩ እና በሕዝቦች መካከል ያልጠራ እና ብዥታ ያለባቸውን ጉዳዮች አግዝፈው እና ለራሳቸው የፖለቲካ ጠቀሜታ በማዋል ሲያጋጩ የሚኖሩ እና ያሉ አካላት ከመኖራቸው ጋር ተያይዞ መጪው ምርጫ ጉዳይ በትኩረት ሊጤንበት ይገባል። ምርጫን ከአቅም በላይ በሆነ መንገድ በተያዘለት ጊዜ ገደብ እንዳይካሔድ ከመደረጉ ጋር ተያይዞ ምን አይነት ችግር እና ከባድ ውጥንቅጥ ውስጥ በተለይም ደግሞ ከሕወሓት ጋር ተገብቶ እንደነበር የሚታወስ ነው አሁንም ከኹነቱ ችግር አልወጣንም። ይህ ጉዳይ ግን አሁንም ደግሞ መልኩን ቀይሮ ሌላ ሳንካ ከፊት የተጋረጠ ለመሀኑ አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። ጉዳዮ ደግሞ በመጀመሪ ደረጃ አገርን ለማስተዳደር እና አገርን በምርጫ አሸንፈው ለመምራት የሚዘጋጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገዢውንም ፓርቲ ጨምሮ እርስ በራሳቸው ስምምነት ሊኖራቸው ይገባል።

የእርስ በርስ የፖለቲካ ሽኩቻቸው ወደ ሕዝብ ወርዶ በየዕለቱ የሚሆነውን እና ሚደርሰውን እየታዘብን እንገኛለን። ይህን ይዘን እና ባለመግባባት የተራራቁ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተይዘው ወደ ምርጫ ለመግባት መሞከር አገርን ከማፍረስ እና ከባድ ችግር በምርጫ ማግስት እንዲፈጠር መንገድ መክፈት እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ስለሆነም ከምርጫ በፊት ብሔራዊ መግባባቶች መደረጋቸውን አዲስ ማለዳ አጥብቃ ትደግፋለች። ይህ ማለት አገርን አስቀድሞ ምርጫን በተረጋጋ እና በሰከኑ ፓርቲዎች መካከል ማድረግ ጥቅሙ እና አወንታዊ ጎኑ በእጅጉ የበዛ ነው የሚሆነው።

በሌላ በኩል ደግሞ አመራሮቻቸው በዕስር ላይ ሚገኙ ፓርቲዎች ጉዳይ እና በየጊዜው የሚወጡት መግለጫ የሚመለከተው አካል በትኩረት ሊሰማው እና ፍጹም ጆሮ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው። ጉዳያቸው በሕጋዊ መንገድ መታየቱ እና መዳኘቱ የሚስመሰግን ቢሆን ነገር ግን አሁንም ከመጪው ምርጫ ጋር ተያይዞ ሚኖራቸው መስተጋብር እና ምህዳሩን ከማስፋት አንጻር እንዴት ሊታይ እደታሰበ አዲስ ማለዳ ማብራሪያዎች ወደ ሕዝብ መቅረብ ይኖርባቸዋል ስትል ትጠይቃለች።

ከዚህ ባለፈ በዋናነት ዘርን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች በአስቸኳይ መንግሥት ሊያስቆማቸው እንደሚገባም አዲስ ማለዳ ታሳስባለች። ከጥቂት ስፍራዎች ውጪ ዜጎች ይገደላሉ፣ ይፈናቃሉ፣ ይደበደባሉ ሰርቶ በሰላም መኖር ቅንጦት የሆነበት ጊዜ ላይ መደረሱንም በየዕለቱ የሚወጡ ዘግናኝ መረጃዎች አመላካች ናቸው። በቤንሻነጉል ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ፣ በኮንሶ፣ በትግራይ እና በሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች አሁንም የዜጎች ደኅንነት አደጋ ላይ ነው። አገር እንደ አገር መቀጠል ካለባት እና አንድነትን አስጠብቆ በፍጹም አገራዊ አንድ አገራዊ አጀንዳን ይዞ ለመሔድ የአገር ወቅታዊ ጉዳይ እንጂ ሌላ ሊቀድም የሚገባ ጉዳይ እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል።

ምርጫን ለማድረግ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ቢሆኑ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ተዘዋውረው ቅስቀሳ አድርገው አላማቸውን ሸጠው እና በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት አግኝተው መመረጥ መብታቸው ቢሆንም በአሁኑ ነባራዊ ሁኔታ ግን የፖለቲካ ፓርቲዎች ተዘዋውረው ምረጡኝ ቅስቀሳዎችን ማድረግ ሚችሉበት ደረጃ ላይ እንዳልሆኑ ማሳያዎች እየወጡ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ትገነዘባለች። ይህ ደግሞ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመመስረት ብቻም ሳይሆን አገርን እንደ አገር ለማስቀጠል የሚደረገውን አካሔድ ከወዲሁ የሚያቀጭጭ እንደሆነ ሊታወቅ ይገባል። በአሁኑ ወቅት ሰብኣዊ መብቶች ጥሰት በተለያዩ ክልሎች መከሰታቸው የመንግሥትን የዜጎችን ደኅንነት ያማስጠበቅ ድክመትም ማሳያ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። አገርን አስቀድሞ ከአገር በኋላ ወይም በአገር ውስጥ ሊካሔዱ የሚችሉ ኹነቶችን ማስከተል እየተቻለ ለነባራዊው አገራዊ ጉዳይ አፋጣኝ መፍትሄ ሳይሰጥ መፃኢውን እና ሊቀየር የሚቻለውን ጉዳይ ላይ ትኩረት መስጠት ተገቢ አይደለም።

በሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሳምንቱ መገባደጃ ላይ የወጣው ሪፖርት እንደሚያመለክተው በአምስት ወራት ውስጥ በቤንሻነጉል ክልል መተከል ዞን ብቻ ከ500 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ይፋ አድርጓል። ይህ ሪፖርት አገር ወዴት እያመራች እንደሆነች እና ነገ ደግም ጉዳዮች ባልጠሩበት ሁኔታ ወደ ምርጫ በሚገባበት ወቅት ይዞት ሊመጣ የሚችለው መዘዝ እጅግ አስፈሪ እንደሚሆን መናገር ለቀባሪው ማርዳት ነው የሚሆነው። በመሆኑም በብሔራዊ መግባባት አገርን እና ወገንን ሊያገኙት ሚገባቸውን ሰላም ከተረጋገጠ በኋላ ምርጫን ማካሄድ ለአገር ማሰብ ዋነኛው ጉዳይ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ታምናለች። ከምርጫም፣ ከውክልናም፣ በትረ ስልጣንን ከመያዝ አስቀድሞ ሁሉም ባለድርሻ አካል የአገራዊ መግባባቶች እና የጦር አውርድ ሐሳብን መተው ግድ ነው፤ ምርጫ ከአገር በታች ነው።

ቅጽ 2 ቁጥር 118 ጥር 8 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here