በፓርቲዎች ውይይት የሚዲያ ተሳትፎ በድምፅ ብልጫ ይወሰናል

0
483

ሰሞኑን የምርጫ ሕጉን ማሻሻያና የ2012 አገር ዐቀፍና አካባቢያዊ ምርጫን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መወያየት የጀመሩት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የፖለቲካ ድርጅቶች ቀጣይ ውይይትና ድርድራቸውን ለመገናኛ ብዙኃን ዝግ ለማድረግ ሐሳብ አቅርበው በየአጀንዳዎቹ ተሳትፏቸው በፓርቲዎች ድምፅ እንዲወሰን ሥምምነት ላይ ደርሰዋል።
የፖለቲካ ድርጅቶች በቀጣይ በሚኖራቸው ውይይትና ድርድር ዙሪያ ከምርጫ ቦርድ ጋር ሐሙስ፣ ጥር 2 ሲወያዩ 32 አጀንዳዎችን አቅርበዋል። ለውይይት ቢቀርቡ በሚል ለምርጫ ቦርድ በጽሑፍ ያቀረቧቸው አጀንዳዎች ሰባት ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳይ፣ ምርጫ ቦርድን የተመለከቱ ጉዳዮች፣ ምርጫ 2012 እና የአካባቢ ምርጫ፣ የዴምክራሲ ተቋማትን የማሻሻል ጉዳይ፣ ሕገ መንግስትና ፌዴራሊዝም እንዲሁም የውጭ ጉዳይ የሚሉት አጀንዳዎች ይጠቀሳሉ።
ይሁንና ቀጣይ ውይይትና ድርድሮች ለመገናኛ ብዙኃን ክፍት እንዳይሆኑ የሚያስችል ሐሳብ መቅረቡ አነጋጋሪ ሆኗል። በተለይም ለውይይት የቀረበው ረቂቅ ላይ በተለየ ሁኔታ ካልተወሰነ በስተቀር ለመገናኛ ብዙኃን ግልፅ እንደማይሆን ለውይይት በቀረበው ‹‹የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ውይይት የሚመራበት ሥርዓትና ደንብ ረቂቅ›› ላይ ተገልጿል።
ረቂቁ የመገናኛ ብዙኃን ሚና በሚለው ርዕስ ስር ‹‹የውይይቱ መድረክ በተለየ ሁኔታ ካልተወሰነ በስተቀር የተፎካካሪ ፓርቲዎች ተከታታይ ውይይቶች ለመገናኘ ብዙኃን ክፍት አይሆኑም›› ይላል። ይህም ውይይትና ድርድሩ በዝግ እንዲካሄድ የሚያደርግ ነው። ይሁን እንጂ ጉባኤው ስለደረሰበት ጉዳይ በየጊዜው በድጋፍ ሰጪ ባለሙያ መግለጫ እዲሰጥ እዲሁም፣ መድረኩ ‹‹ጉልህ የሆነ ስምምነት ላይ ሲደርስ›› ሁሉን አካታች መግለጫ እዲጠራ የሚል ሐሳብም ተካቷል።
እስከ መጭው መጋቢት በውኅደት ይመሰረታል ለተባለው አዲሰ ፓርቲ ሲባል በቅርቡ የከሰመው የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር የሺዋስ አሰፋ ‹‹እያንዳንዱን ውይይታችንን ለመገናኛ ብዙኃን ክፍት ማድረግ የለብንም›› ብለዋል። ነገር ግን ተወያይተን ውሳኔ ላይ ስንደርስ ለመገናኛ ብዙኃን ክፍት እናደርጋለን ሲሉም ለአዲስ ማለዳ ስለረቂቅ ሐሳቡ ተገቢነት ያስረዳሉ።
የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳ በተለየ ሁኔታ እስካልተወሰነ ድረስ ለማንኛውም የመገናኛ ብዙኃን ክፍት መሆን እንደሌለበት ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
በተያያዘ ዜና የፖለቲካ ድርጅቶች ለአገራዊ ተቋማት ግንባታ ስለሚኖራቸው ፋይዳ የተወያዩ ሲሆን ከወቅታዊ ሁኔታ አንፃርም ሠላምን ለማምጣት በትኩረትና ትብብር እንዲሰሩ ተጠይቀዋል።
በተለይም ፓርቲዎች በአገሪቱ ችግሮችን እያነሱ ከማራገብ ይልቅ አማራጭ መፍትሔዎችን ይዘው መቅረብ እንዲችሉም ምክረ ሐሳቦች ተሰንዝረዋል። ፓርቲዎች ከጥቃቅን ጉዳዮች ይልቅ በአገራዊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት እንዲያደርጉም ተጠይቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here