በአዲስ አበባ ከሚገኙ አንድ ሺሕ 407 ትምህርት ቤቶች 78 በመቶዎቹ የሚጠበቅባቸውን ደረጃ ሳያሟሉ እያስተማሩ እንደሚገኙ የከተማዋ የአጠቃላይ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ሬጉላቶሪ ኤጀንሲ ገለጸ።
አዲስ ማለዳ ከኤጀንሲው ያገኘችው መረጃ እንደሚያሳየው በከተማዋ በግል፣ በመንግሥትና በሕዝብ የሚተዳደሩት የቅድመ መደበኛ፣ አንደኛ እና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አጠቃላይ ብዛት አንድ ሺህ 407 ሲሆን የሚጠበቅባቸውን ደረጃ ያሟሉት 301ዱ ብቻ ናቸው። ይህም ከ21 በመቶ መዝለል እንዳልቻለ ያመለክታል።
በአንጻሩ አንድ ሺሕ 106ቱ ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ቢሆኑም በመማር ማስተማር ሥራው ላይ ተሰማርዋል። ይህም 78 ነጥብ ስድስት በመቶ ድርሻን ይዛል።
ትምህርት ሚኒስቴር በ2006 ያወጣው ‹‹አገር አቀፍ የአጠቃላይ ትምህርት ኢንስፔክሽን ማዕቀፍ›› የትምህርት ጥራትን እና የትምህርት ቤቶችን መሻሻልና አፈጻጸም በተመለከተ የተጠያቂነት አሠራርን መዘርጋት እንደሚያስፈልግ በመጠቆም ትምህርት ቤቶች ላይ ቁጥጥር ማድረግ ዋነኛ ከሚባሉት ሥራዎች አንዱ መሆኑን ይጠቅሳል። በዚህም ትምህርት ቤቶችን በግብዓት፣ በሒደትና በውጤት መለካት እንደሚጠበቅ ያነሳል። ሰነዱ በምዘናና ደረጃ ማውጣት ሥራ ዋነኛ መመዘኛዎች የሚላቸውም የትምህርት ቤቶቹ የሰው ኃይል፣ ሕንፃዎች፣ የገንዘብ ምንጮችና የግብዓት አቅርቦት፣ ምቹ የመማሪያ አካባቢ፣ የመማር ማስተማር ሒደት፣ ትምህርት ቤቶቹ ከወላጆችና ኅብረተሰቡ ጋር ያላቸው ግንኙነት፣ የተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባር ናቸው።
የትምህርት ተቋማቱ በእነዚህ ዋነኛ መስፈሪያዎች ተመዝነው ከመቶው ከ50 በታች ካመጡ ደረጃ አንድ ሲባሉ፣ ይህም እጅግ የከፋው ውጤት ማለት ነው። ከ50 እስከ 69 ነጥብ 99 ያሉትም ደረጃ ኹለት በሚል ምድብ ውስጥ ይግቡ እንጂ በቂውን መሰፈርት እንዳላሟሉና ከደረጃ በታች እንደሆኑ ይወሰዳሉ። በአንጻሩ ከ70 እስከ 89 ነጥብ 99 የሚያገኙት ደረጃ ሦስት በሚል ይመደባሉ። ይህን ውጤት የሚያገኙትም ደረጃውን እንዳሟሉ ይወሰዳሉ። ከ90 እስከ 100 የሚያገኙት ደግሞ በሞዴልነት የሚገለጹና ደረጃ አራት የሚል ምደባ የሚሰጣቸው ሲሆን ኤጀንሲው እስከ ሰኔ 2010 ባደረገው ምዘና ውጤት መሠረት ይህን ደረጃ አሟልተው የሚገኙት ኹለት የግል ትምህርት ቤቶች ብቻ መሆናቸውን የኤጀንሲው የአጠቃላይ ትምህርት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር ዘመነ አብዩ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በአጠቃላይ ምዘናው ግን ከደረጃ በታች በሚል ከተካተቱት ውስጥ የግል ትምህርት ቤቶች ይበዛሉ። 49 የግል ትምህርት ቤቶች ደረጃ አንድ ውስጥ ሲካተቱ፣ 817 የግል ትምህርት ቤቶች ደግሞ ደረጃ ኹለት መሆናቸውን ሪፖርቱ ያመለክታል።
እንደ ዘመነ ማብራሪያ የትምህርት ቤቶች ምዘና (‹‹ኢንስፔክሽን››) ከ2006 ጀምሮ እየተካሄደ ሲሆን ውጤቱ የተወሰነ የመሻሻል ለውጥ ያሳይ እንጂ አጥጋቢ ባለመሆኑ የትምህርት ቤቶች የቤት ሥራ የበዛ እንደሆነ አመላካች ነው። ዘመነ ይህን ይበሉ እንጂ የኤጀንሲው የ2009 እና የ2010 ዓመት ሪፖርቶች የሚያሳዩት ግን ውጤቱ ከዚህም በታች ማሽቆልቆሉን ነው። እስከ ሰኔ 2009 በሚሸፍነው ሪፖርት ከደረጃ በታች የነበሩት ትምህርት ቤቶች 74 ነጥብ ስምንት የነበሩ ሲሆን በ2010 አኀዙ ወደ 78 ከፍ ብሏል።
የ2010 ምዘና ውጤት እንደሚያሳየው ካሉት ትምህርት ቤቶች 57ቱ እጅግ የከፋው ምድብ ውስጥ ናቸው። በተለይም በዚህ ምድብ ወይም ደረጃ አንድ ውስጥ የሚካተቱት ትምህርት ቤቶች በመማርና ማስተማር ሒደቱ ላይ መቆየታቸው የትምህርት ጥራትና ተጓዳኝ ጉዳዮቸ ላይ ከሚያስገኙት በጎ ነገር ይልቅ የሚያሳድሩት አሉታዊ ጎን እንደሚበረታ ይገለጻል። በምዘና ውጤቱ መሠረት ትምህርት ተቋማትን እስከ መዝጋት የሚደርስ ሥልጣን የተሰጠው ኤጀንሲው ስለወሰዳቸው እርምጃዎች የጠየቅናቸው ዘመነ አልሻሻል ባሉ ትምህርት ቤቶች ላይ በእውቅና ምዝገባና እድሳት ወቅት የሚሰረዙ መኖራቸውን በመጥቀስ የመዝጋት እርምጃው ላይ በስፋት እንዳልተኬደ ገልጸዋል። ምክንያት ያሉትም ‹‹መንግሥት መጀመሪያ ሥራውን ስላልተወጣ ነው›› የሚል ነው። አማራጭ ሳይኖር ትምህርት ቤቶቹን መዝጋት በተማሪዎችና ወላጆቸ ላይ መፍረድ እንደሆነ የሚያምኑት ዳይሬክተሩ ዘመነ በዚህ ዓይነት ትዕግስት ግን እንደማይቀጥሉ ተናግረዋል። በተለይም ደረጃ አንድ ላይ የሚገኙ 57 ትምህርት ቤቶች እስከ ሰኔ 2011 መጨረሻ ድረስ ወደ ደረጃ ኹለት ከፍ እንዲሉና ትምህርት ቢሮም እንዲከታተል ካልተሻሻሉ ግን የመዝጋት እርምጃ እንደሚወሰድ ከቢሮው ጋር ስምምነት መፈራረማቸውን አክለዋል። የ2011 ምዘና እስከ መጪው ሰኔ የሚቀጥል እንደሆነም ነግረውናል።
ኤጀንሲው ከደረጃ በታች በሚሆኑት ትምህርት ቤቶች ላይ ስላለው አቋም እንዲነግሩን የጠየቅናቸው የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር መረጃ ለማግኘት በደብዳቤ መጠየቅ ግዴታ እንደሆነ በገለጹልን መሰረት በደብዳቤ ብንጠይቅም ለምክትል ዋና ዳይሬክተሯ መርተውታል። ምክትሏም መረጃውን ለመሥጠት ሥራ እንደሚበዛባቸው ገልጸው የቀጠሮ ቀናትን በመስጠታቸው ለጊዜው የኃላፊዎቹን ሐሳብ ማካተት አልቻልንም።
ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011