የኢትዮጵያ የብድር ጫና ከ50 ቢሊየን ዶላር በላይ ሆነ

0
769

መንግሥት የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማካሄድ በተለያዩ ጊዜዎች ከውጭ እና ከአገር ውስጥ አበዳሪዎች የወሰደው የብድር መጠን 50 ቢሊየን ዶላር ማለፉን የፋይናንስ ሚንስቴር አስታወቀ። ለብድር ጫናው መጨመር የመሠረተ ልማትና ንግድ ብድሮች መጨመር እንደ ዋነኛ ምክንያት ተገልጿል።
ባለፈው ወር መጨረሻ ይፋ ባደረገው ሪፖርቱ ሚንስቴር መሥሪያ ቤቱ፤ የተገለጸው የብድር መጠን በዚህ ዓመት ከተያዘው በጅት ጋር ሲነጻጸር በሦስት ዕጥፍ ሲልቅ የሃገሪቷን ጠቅላላ ምርት 58 በመቶ ያህል መሆኑን ገልጿል።
የሚኒስቴሩ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሃጂ ኢብሳ እንደገለጹት ብድሩ 50 ቢሊየን ዶላር ቢደርስም መንግሥት ከፍተኛ ወለድ የሚጠይቁ የአጭር ጊዜ ንግድ ብድሮች ስላቆመ አገሪቷን አያሰጋም ሲሉ ገልፀዋል።
‹‹ሌላ አቅጣጫ በመንግሥት እስከሚቀመጥ ድረስ፤ በቀጣይ ጊዜያትም ዝቅተኛ ወለድ ያላቸው ብድሮች ውጪ አገሪቷ እንደማትወስድ ገልጸዋል። ለዚህም በቅርቡ አገሪቷ ከዓለም ባንክ እና ከተለያዩ የልማት አጋሮች የወሰደቻቸውን በመቶ ሚሊየን ዶላር ብድሮች እንደ አብነት አንስተዋል።
ከጠቅላላው የአገሪቷ የብድር መጠን 26 ቢሊየን ዶላር የሚሆነው ከውጭ አበዳሪዎች ሲሆን የቀረው ደግሞ የተገኘው ከአገር ውስጥ አበዳሪዎች መሆኑን ሪፖርቱ ገልጿል። የዓለም ባንክ በ 7 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር) ከፍተኛ ብድር ለኢትዮጵያ በመስጠት ቀዳሚ ሲሆን ቻይና እና የአፍሪካ ልማት ፈንድ ይከተላሉ።
በጥቅሉ ደግሞ እንደ ንግድ ባንኮችና አቅራቢዎች ያሉ የግል አበዳሪዎች 6 ነጥብ 8 ቢሊየን ዶላር የባለ ብዙ መንግሥታት ግንኙነት አበዳሪዎች 10 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ብድር ለኢትዮጵያ ሰጥተዋል። በሌላ በኩል የኹለትዮሽ ግንኙነት አበዳሪዎች ወደ 8 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር ለመንግሥት አበድረዋል።
በተጨማሪ፤ እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ያሉ የልማት ድርጀቶች የአገሪቷን 48 በመቶ ብድር ሲሸፍኑ የፌዴራል መንግሥት ተቋማት ደግሞ ቀሪውን ብድር መወስዳቸውን የፋይናንስ ሚንስቴር ሪፖርት አመላክቷል።
ከወር በፊት አይ ኤም ኤፍ የተባለው የኢንተርናሽናል ሞንታሪ ፈንድ የተባለው አለም ዐቀፍ ተቋም ባወጣው ሪፖርት የኢትዮጵያ ብድር አገሪቷ ካላት አቅም ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ መሆኑን መግለጹ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ በየጊዜው ከዓለም አበዳሪ ተቋማት እና አገራት የምትወስደውን ገንዘብ በጊዜው መመለስ ባለመቻሏ፣ በአበዳሪዎች ዘንድ በጥርጣሬ መታየት ከጀመረች ሰንበትበት ብሏል ሲሉ የተለያዩ ሪፖርቶች አመላክተዋል።
በያዝነው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት ብቻ 369 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶላር የሚሆነውን ብድሯን፤ የወለድ ክፍያን ጨምሮ፤ ኢትዮጵያ የከፈለች ሲሆን በቀሩት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ1 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር በላይ ለአበዳሪዎች ይከፈላል ተብሎ ይጠበቃል።
ይሁን እንጂ አይ ኤም ኤፍ የተባለው ተቋም ለኢትዮጵያ የሰጣት ደረጃ እንደሚያሳየው አገሪቷ ብድር ለመክፈል አጣብቂኝ ውስጥ እንዳለች የሚያመለክት መሆኑ የተቋሙ መረጃ ያሳያል። እንደ ተቋሙ መረጃ፤ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ከፍተኛ ብድር ጫና መደብ ውስጥ የሚካተቱ አገራት በቢሊየን ብሮች የሚጠይቁ የመሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን በራሳቸው አቅም ካልገነቡ የብድር ወጥመድ ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ያስጠነቅቃል።
መንግሥት በኹለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን የያዛቸውን ዕቅዶች ለማሳካት በአጠቃላይ 119 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው መረጃዎች ያሳያሉ።
ይህንን ከወጪ ንግድና ከአገልግሎት ዘርፍ፣ ውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ከሚላክ ገንዘብ፣ ከቀጥታ የውጭ ኢንቨስትመንት እና ከውጭ ብድር 115 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ይሰበሰባል ተብሎ ታቅዷል። አሁን መንግሥት ባለው አቅም ይህንን ማሳካት አዳጋች መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here