የሕወሓት ቡድን በፈፀመው የሀገር ክህደት ወንጀል በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በሚገኙ ታላላቅ መሰረተ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት በማድረሱ ከአገልግሎት ሊገኝ የሚገባ ከ2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ተቋማት እንዲያጡ ማድረጉን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ኮሚሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ጁንታው የህወሃት ቡድን የሀገሪቱን ዋና ዋና የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ታላላቅ የመሰረተ-ልማት አውታሮች ላይ ባደረሰው ጥቃት በሀገር ሀብትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት አድርሷል።
በሰሜን ዕዝ የመከላከያ ሰራዊትና የመንግስት ተቋማት ጥበቃ ላይ በነበሩ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ላይ በፈፀመው የሀገር ክህደት ወንጀል በኢትዮ-ቴሌኮም፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድና ኤርፖርቶች ድርጅት እንዲሁም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሚገኘው የደደቢት ማይክሮ ፋይናንስ ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ገልጿል።
በዚህ መሰረት በአካባቢው በሚገኙ የኢትዮ-ቴሌኮም መሰረተ-ልማቶች ላይ ጁንታው ባደረሰው ጉዳት ተቋሙ ማግኘት ከሚገባው 1 ቢሊዮን 370 ሚሊዮን 828 ሺህ 689 ብር ከ35 ሳንቲም በላይ ማጣቱ በምርመራ መረጋገጡን አመልክቷል።
በተጨማሪም በተቋሙ ላይ ከ39 ነጥብ 8 ቢሊዮን በላይ የተፈፀሙ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን ማክሸፍ መቻሉ ጠቅሷል።
በተመሳሳይ በሰሜን በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መሰረተ-ልማቶች ላይ ጁንታው የህወሃት ቡድን ባደረሰው ጉዳት ከ 329 ሚሊዮን 167 ሺህ 524 ብር በላይ ማጣቱ ተረጋግጧል።
በዚሁ ጥቃት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በወልቃይት፣ በማይጨው፣ በአላማጣ እና በአሸጎዳ መቀሌ ሰብስቴሽኖች ላይ ውድመት የደረሰ መሆኑን የገለጸው ኮሚሽኑ፤ “በእነዚህ ንዑስ የኤሌክትሪክ ማሰራጫ ጣቢያዎች ላይ የደረሰውን ጉዳት የምርመራ ቡድኑ በገንዘብ መጠን አስልቶ ወደፊት ይገልጻል” ብሏል።
በኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት ላይ ጁንታው የህወሃት ቡድን ባደረሰው ጉዳት 14 ሚሊዮን 49 ሺህ 70 ሊትር ነዳጅ ከመቀሌ ነዳጅ ዴፖ በህገ-ወጥ መንገድ ተቀድቶ በመወሰዱ ድርጅቱ ማግኘት የሚገባውን 258 ሚሊዮን 190 ሺህ 998 ብር ከ64 ሳንቲም ማጣቱ በምርመራ እንደተረጋገጠ ገልጿል።
ቅጽ 2 ቁጥር 119 የካቲት 6 2013


