ማኅበራት በኤጀንሲው ትእዛዝ ብቻ እንዳይዘጉ ሊደረግ ነው

0
491

በጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲሁም ሌሎች ሲቪል ማኅበራት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ፤ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኀበራት ኤጀንሲ ትእዛዝ ብቻ እንዳይዘጉ የሚያደርግ ረቂቅ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ። በሕግ ፍትሕና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ጫላ ለሚ ስለ ረቂቅ አዋጁ በተደረገ ገለፃ ከዚህ በፊት አናቂ የነበሩ የሕግ አሰራሮችን በማስቀረት አዲስ እና አካታች ስርዓትን ለመፍጠር ነዉ ተብሏል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በተቀበለቻቸዉ ዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች የተረጋገጠዉን የመደራጀት መብት በተሟላ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ ሕግ ማዉጣት በማስፈልጉ ይህ ረቂቅ አዋጅ እንደቀረበ ተገልጿል። በሌላም በኩል በአገሪቱ ልማትና ዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያላቸዉ ሚና እንዲጎለብት ለማድረግም ረቂቅ አዋጁ የጎላ ሚና እንዳለዉ ተጠቁሟል።
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኀበራት ኤጀንሲ ሕዝብ ግንኙነት መስፍን ታደሰ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ረቂቅ አዋጁ ገለልተኛ በሆነ አካል የተጠና እንደሆነና ከዚህ በፊት ይታዩ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ ጥረት ተደርጓል። ሕዝብ ግንኙነቱ አያይዘዉ እንደጠቀሱት በቀደመዉ ጊዜ ማንኛዉም ሰዉ የመደራጀት ሙሉ መብቱ የተገደበ እንደሆነ ገልፀዉ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ግን የመደራጀትን መብት በሰፊዉ ያስቀመጠ እና አዋጁ ከአዲሱ ለዉጥ ጋር እንዲሄድ ታስቦ የተሰራ ነዉ ብለዋል። መስፍን በጎ አድራጎት ድርጅቶች እና መኅበራት የሚጠበቁበት የሕግ ማዕቀፍ እምብዛም እንዳልነበረ ገልፀዉ በኤጀንሲዉ በሚወሰድባቸዉ እርምጃም ወደ ፍርድ ቤት ሄደዉ ይግባኝ የሚሉበት አሰራር እንዳልነበር አክለዋል። ይህን ምክኒያት አድርጎ በኢትዮጵያ ዉስጥ የሚንቀሳቀሱት የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ቁጥር ከጎረቤት አገራት ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ተገልጿል።
አብዛኛዉን ቁጥር የሚይዙት የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት እንዲሁም የዉጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ከፍርድ ቤት ዉጭ በኤጀንሲዉ ዉሳኔ ብቻ ሊዘጉ እንደሚችሉ ተደንግጓል። በኢትዮጵያዉያን ኢትዮጵያ ዉስጥ የተቋቋሙ ድርጅቶች ከ10 በመቶ በላይ ከዉጭ ገንዘብ በማግኘታቸዉ ምክንያት ምዝገባም ሆነ ዕድሳት ቢከለከሉ፣ ከምዝገባ ቢሰረዙ ወይም ሌላ ዕርምጃ በኤጀንሲዉ ቢወሰድባቸዉ ለፍርድ ቤት ይግባኝ የማቅረብ መብት የተነፈጉ መሆኑ በሕገ መንግስቱ የተረጋገጠዉን በሕግ ፊት እኩል የመሆን እና ፍትሕ የማግኘት መብት የሚጥስ ፣ አድሏዊ አሰራር ሆኖ ተገኝቷል። በዚህ አዋጅ መሠረት ግን ኤጀንሲዉ ድርጅቶችን መመዝገብ፣ መደገፍ ፣ሥራቸዉን ማሳለጥና የማስተባበር ተግባራት ያሉት ሲሆን በሥልጣን ደረጃ ደግሞ ድርጅቶች ሥራቸዉን በሕግና በአግባቡ ማከናወናቸዉን ለማረጋገጥ አስፈላጊዉን ክትትልና ቁጥጥር ማድረግ ይገኝበታል።
ከዚህ በፊት በነበረዉ ሕግ መሠረት የኢትዮጵያ ነዋሪዎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች 10 በመቶ የሚሆነዉን ገቢያቸዉን ከአገር ዉጭ ቀሪዉን 90 በመቶ ደግሞ ከአገር ዉስጥ ለጋሾች እንዲሰበስቡ የሚደረግበት የሕግ አሰራር ነበር። ከዚህም ጋር ተያይዞ 10 በመቶ በላይ የሚሆነዉን ገቢ ከዉጭ የሚያገኙ ከሆነ ወይም ደግሞ የዉጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶች ሴቶች እና ሕፃናት፣ በህግና ዲሞክራሲ ግንባታ፣ የሰብኣዊ መብት አጠባበቅ እና መሰል ጉዳዮች ላይ እንዳይሰማሩ ይደረግ ነበር።
በሌላ በኩል ደግሞ የዉጭ በጎ አድራጎት ድርጅቶች የባንክ ሒሳብ ለመክፈት ከኤጀንሲዉ የድጋፍ ደብዳቤ ያስፈልጋቸዋል የሚል አሰራር ነበር። ስለዚህም ጉዳይ መስፍን ሲናገሩ በእርዳታ ሰበብ ወደ አገር ዉስጥ የሚገባዉን ገንዘብ መንግሥት መቆጣጠር ስላለበት አሰራሩን በዚህ መንገድ ዘርግቶት እንደነበር ገልፀዋል። በዚህም በኩል አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ድርጅቶች በየአመቱ ለኤጀንሲዉ ዓመታዊ የሒሳብ መግለጫ ማቅረብ እንደሚገባዉ ተቀምጧል።
ከገቢ አሰባሰብ ጋር በተያያዘ ድርጅቶች ከዚህ ቀደም ገቢ የሚያገኙበት መንገድ የጠበበ እንደነበር እና በዚህም ምክንያት በገንዘብ እጦትና በሌሎች ምክንያቶች በየዓመቱ በአማካኝ ከመቶ ያላነሱ ድርጅቶች የሚዘጉ ሲሆን ከእነዚህም ዉስጥ አብላጫዉን ቁጥር የሚይዙት አገር በቀል ድርጅቶች እንደሆኑ ተጠቁሟል። ይህን ታሳቢ በማድረግ በረቂቅ አዋጁ ላይ የሥራ ነፃነት ለድርጅቶች በሰፊዉ የተደነገገ ሲሆን በዚህም መሰረት ማንኛዉም ድርጅት የተቋቋመበትን ሕጋዊ ዓላማ ለማሳካት በየትኛዉም ሕጋዊ ሥራ ላይ የመሠማራት መሉ መብት እንዳለዉ ተገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ የዉጭ ድርጅቶች በተቻለ መጠን ከአገር በቀል ድርጅቶች ጋር በአጋርነት በመሥራት የአገር በቀል ድርጅቶችን አቅም እንዲጎለብት ድጋፍ ማድረግ ይችላሉ። አዲሱ የሲቪል መኀበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ወይይት ከተደረገበት በኃላ ወደ ህግ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ በሙሉ ድምፅ ተመርቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here