ከግማሽ በላይ የወጣቶች የተዘዋዋሪ ፈንድ ብድር አልተመለሰም

0
587

ከዛሬ ኹለት ዓመት በፊት ይፋ በሆነው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ ለማስፈፀም፤ የፌዴራል መንግሥት እስካሁን ወደ 8 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብድር ለተጠቃሚዎች በክልሎችና ማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት አስፈጻሚነት ቢያቀርብም መመለስ የነበረበት ከግማሽ በላይ ብድር እስካሁን ተመላሽ እንዳልሆነ ታወቀ።
የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለመፍታት በሚል ዓላማ የፌዴራል መንግሥት 10 ቢሊየን ብር ከመደበ በኋላ ለተጠቃሚዎች የተሰጠው ብድር በተቀመጠለት ጊዜ መሰረት ባለመመለሱ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የሥራ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ እንዳሳደረም ተገልጿል።
በፌዴራል ደረጃ የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚንስቴር እንዲከታተለው የተደረገው ይህ ብድር ይፋ ከሆነ አንስቶ፤ የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር እስከ ካለፈው ሩብ በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ወደ 8 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር አሰራጭቷል።
የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራ እና የምግብ ዋስትና ኤጀንሲ የዕቅድ እና ክትትል ዳይሬክተር የሆኑት መነን መለሰ እንደገለጹት በአገሪቷ ዴሞክራሲና ለውጥ እንዲመጣ ላበረከትነው አስተዋፅኦ ሽልማታችን ነው በማለት ቁጥራቸው ቀላል የማይባል የፈንዱ ተጠቃሚ የሆኑት ወጣቶች (ተበዳሪዎች) ብድሩን አንመልስም ማለታቸውን ገልጸዋል።
‹‹ከዚህ በተጨማሪ ብድሩ ከመሰጠቱ ቀደም ብሎ፤ ለተጠቃሚዎች የገበያ ትስስር አለመፈጠሩ፣ የመስሪያ ቦታ አለመዘጋጀቱ እና ክህሎታቸውን ለማሳደግ በቂ የሆነ ሥልጠና አለመሰጠቱ ተጠቃሚዎች ውጤታማ ሆነው ብድራቸውን በአግባቡ እንዲመልሱ እንቅፋት እንደሆነባቸው›› ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ እነዚህ ችግሮች ባይፈቱም፤ ተዘዋዋሪ ፈንዱን ለማስፈጸም በያዝነው በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሦስት ወራት ብቻ ወደ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን በ9 ክልሎችና ኹለት መስተዳድሮች መሰራጨቱን የኤጅንሲው መረጃ ያሳያል። ችግሮቹ ሳይፈቱ ፈንዱ መሰራጨቱ ስራቸው ላይ መስተጓጎል እንደፈጠረባቸው የማይክሮፋይናንስ ተቋማት ኃላፊዎች ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
እንደ ጀማል ዋሪቱ፤ የኦሮሚያ ብድር እና ቁጠባ ተቋም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ፤ ገለጻ ያለ ጠንካራ ዋስትና መሰጠቱ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማትን የችግሩ ገፈት ቀማሽ አድረጓቸዋል ብለዋል።
የብድሩ በአግባቡ አለመመለስ በከተሞች ላይ ከፋ ያለ መሆኑን የገለጹት ጀማል የወረዳዎች አመራሮች መቀያየርና የወጣቶች ክህሎት አናሳ መሆኑ ችግሩን አብሶታል ብለዋል።
በተጨማሪም፤ የቀድሞው ፕሬዝደንት ሙላቱ ተሾመ ብድሩን ካስተዋውቁ ጊዜ አንስቶ የወጣቶች ፈንድ መባሉ የሚመለስ ብድር እንዳይመስል እንዳደረገውና ወጣቶችም ይህንን በመጥቀስ አንመልስም እያሉ እንደሆነ ገልጸዋል።
ለአብነትም እስካሁን ተቋማቸው ወደ 2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በተዘዋዋሪ ፈንዱ መመሪያ መሰረት ለወጣቶች ቢያቀርብም፤ መመለስ ከነበረበት የተመለሰው 56 በመቶ የሚሆነው ብድር መሆኑን ገልጸዋል።
በተመሳሳይ የአማራ ብድር እና ቁጠባ ተቋም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አያልነህ ምህረቱ እንደገለጹት፤ ብድር አመላለስ ላይ ችግሩ ሳይፈታ አሁንም መቅረቡ የድርጅታቸውን የፋይናንስ አቋም ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ብድሩ ከኹለት እስከ አምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ተከፍሎ ማለቅ ያለበት መሆኑ ጋር ተያይዞም ችግሩ ከአንድ ወይም ከኹለት ዓመታት በኋላ የበለጠ ሊታይ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።
እስካሁን ባለው የኤጀንሲው መረጃ፤ ኦሮሚያ (3 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር)፣ አማራ (2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር) እና ደቡብ (1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር) ክልሎች የብድሩ ከፍተኛ ተጠቃሚ በመሆን ቀዳሚ ናቸው። አዲስ አበባ እና ድሬዳዋ መስተዳድሮች 418 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር እና 43 ነጥብ 9 ሚሊየን ብር ከፌዴራል መንግሥት ወስደዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here