ሕግን የተቃወሙ አሽከርካሪዎች ወቀሳን እያስተናገዱ ነው

0
682

ከሰሞኑ በአማራ ክልል አንዳንድ ከተሞች የኤስኤምኤስ የትራፊክ ደኅንነት መቆጣጠሪያ መጀመር ተገቢ አይደለም በሚል ተቃውሞ ውስጥ የገቡት የተሸርከካሪ ባለቤቶችና አሽከርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎትን ለሰዓታት ከማቋረጥ መንገድ እስከመዝጋት መድረሳቸው ተገልጋዮችን አስቆጥቷል፡፡
በፌዴራል መንግሥት መግባባት ላይ ተደርሶ ጥር 1/2011 መተግበር እንዲጀመር ታስቦ የነበረው አዲሱ የትራፊክ ደኅንነት መቆጣጠሪያ አሽከርካሪዎች ጥፋት ሲፈጽሙ በአንድ የመረጃ ቋት እንዲሰባሰብ የሚያደርግ ሥርዓትን የሚዘረጋ ነው፡፡ በዚህም የጥፋት ድግግሞሹ ታይቶም እንደየደረጃው እርምጃ ይወሰዳል፡፡ ይሁንና ዘመናዊ የተባለው አሰራር ጥር 1 አለመጀመሩን ያስገነዘበው የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን አዲሱን ሥርዓት በመቃወም አድማ ካደረጉት መካካል በምዕራብ ጎጃም ዞን መርዓዊ ከተማ የሚገኙ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች እንደሚጠቀሱ አሳውቋል፡፡ ኮሚሽኑ ክልሉ ዝግጅቱን ባለመጨረሱ አዲሱ አሰራር በተባለው ዕለት አለመጀመሩን ገልጾ አሽከርካሪዎች አገልግሎቱን እንዲሰጡ አሳስቧል፡፡ ይህን ተከትሎም ከሰዓታት አድማ በኋላ አሽርካሪዎች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡
በተመሳሳይ የአዊ ብሔረሰብ ዞን መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ለዞኑ የሕዝብ ትራንስፖርት ባለሀብቶችና አሽከርካሪዎች በሚል ባወጣው ማስታወቂያ ‹‹ከዚህ በፊት በኤስኤምኤስ ይደረግ የነበረው ቁጥጥር ወጥነት ባለመኖሩ በዚህ ወር በአገር ዐቀፍ ደረጃ ይጀመራል የሚለውን በተለያዩ ውይይት መድረኮች መግባባት ያልተደረሰበት ስለሆነ እንዲቆይ ስለተባለ ይህን አውቃችሁ ስምሪቱን ያለምንም ስጋት በዞናችን በሚገኙ ወረዳዎች የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንድትጀምሩ እንገልጻለን›› ሲል ጽፏል፡፡
ይሁንና የትራፊክ አደጋንና ደኅንትን ለማቆጣጠር ያግዛል በሚል በአገር ደረጃ ሊተገበር የታሰበውን አሰራር መቃወም ‹‹ከሰው ሕይወት ይልቅ ለራስ ጥቅም ቅድሚያ መስጠት ነው›› በሚል ብዙዎች የአሽርካሪዎችን ድርጊት በማኅበራዊ ትስስር ገጾች ሳይቀር እያወገዙት ይገኛሉ፡፡ የትራፊክ ፖሊሶችም የአሽከርካሪዎቹ ተቃውሞ ‹‹ጥፋት ማጥፋት አለብን፣ ስናጠፋም ልንጠየቅ አይገባም›› የሚል ትርጉም የሚሰጥ አሳፋሪ ድርጊት ሲሉ አውግዘውታል፡፡
አሰራሩ ዘመናዊና ሕጋዊ አገልግሎት ለመስጠትና የሕዝብን ደኅንነት ለመጠበቅ የሚያስችል እንጂ ማንንም ለመጉዳት ታስቦ የተዘጋጀ ባለመሆኑ የአሽከርካሪዎች ተቃውሞ ከራስ ወዳድነት ያለፈ ትርጉም እንደማሰጠው የሚገልጹም አሉ፡፡
በኢትዮጵያ በየቀኑ በአማካይ ከ11 በላይ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ሲያጡ በርካቶች ለአካል ጉዳትና ንብረት ውድመት እንደሚዳረጉ ሪፖርቶች ያስረዳሉ፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 9 ጥር 4 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here