የደምቢዶሎው ተጠርጣሪ ከሕግ ውጭ በአስደንጋ ጭ ሁኔታ መገደሉን ኢሰመኮ አስታወቀ

0
638

በኦሮሚያ ክልል ቄለም ወለጋ ዞን አማኑኤል ወንድሙ የተባለ የወንጀል ተጠርጣሪ በአስደንጋጭ ሁኔታ በፀጥታ ኃይሎች በአደባባይ መገደሉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) ተጠርጣሪው አማኑኤል ወንድሙ በሚያስደነግጥ ሁኔታ በጸጥታ ኃይሎች በአደባባይ መገደሉን አስታውቋል:: ጉዳዩ በአስቸኳይ ተመርምሮ በአጥፊዎች ላይ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድም ጠይቋል::
ኢሰመኮ ተጠርጣሪው ማክሰኞ ግንቦት 3 ቀን 2013 ዓ/ም ከሕግ አግባብ ውጭ በሆነ አስደንጋጭ ሁኔታ ሕዝብ እያየ በአደባባይ መገደሉን ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ የወጣት አማኑኤል ወንድሙ ግድያ ጉዳይ የማህበራዊ ሚዲያዎች መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል፡፡
ወጣቱ ከፍተኛ ድብደባ እና እንግልት እንደደረሰበት የሚያሳዩ የምስል እና የተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) ማስረጃዎችም ሲዘዋወሩ ነበር፡፡ በቪዲዮዎቹ ወጣቱ የፊጥኝ (ወደ ኋላ) ታስሮም ይስተዋላል፡፡ ከሕግ ውጭ የሚደረጉ የትኞቹንም ዓይነት ግድያዎች አወግዛለሁ ያለው ኢሰመኮም ሁሉም ሕግ የማስከበር ዘመቻዎች በሕግ አግባብ እንዲፈጸሙ አሳስቧል፡፡
ግድያዎቹ በህግ የበላይነት ላይ እምነትን ከማሳጣትም በላይ የተገኙ ውጤቶችን እንደሚቀለብሱም ነው ኢሰመኮ ያስታወቀው፡፡
በመሆኑም የአማኑኤል ወንድሙ ግድያ ጉዳይ በአስቸኳይ ተመርምሮ በአጥፊዎች ላይ ተገቢው እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቋል፡፡
ኮሚሽኑ ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተልኩ ነው ያለ ሲሆን፣ የሚደርስበትን እንደሚያሳውቅ ገልጿል፡፡ ኢሰመኮ ከአሁን ቀደምም በኦሮሚያ ክልል ባለው የመብት አያያዝ በተለይም የእስረኞች አያያዝ ሁኔታ መስጋቱን በመግለጫ አስታውቋል፡፡ ሆኖም የክልሉ መንግስት “መግለጫዎቹ ሚዛዊነት የሚጎድላቸው ናቸው” ሲል ኮሚሽኑ አለ ያለውን የመብት አያያዝ ችግር ማስተባበሉ የሚታወስ ነው፡፡


ቅጽ 3 ቁጥር 132 ግንቦት 7 2013

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here