ተማሪዎቹ ባሕር ዳርን ለቀው እንዲወጡ ክልሉ አሳሰበ

0
890

በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ያጋጠመውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ ባሕር ዳር ከተማ በመሄድ የተጠለሉ ከኹለት ሺህ 500 በላይ የአማራ ክልል ተወላጅ ተማሪዎች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ የክልሉ መንግሥት ማሳሰቢያ ሰጠ።
ተማሪዎቹ ዩኒቨርሲቲው እስኪረጋጋ ድርስ ለአንድ ወር ያህል በከተማው ሕዝብ ጭምር እተየደገፉ በመጠለያ መቆየታቸውን ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት የክልሉ መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አሰማኸኝ አስረስ፥ ተማሪዎቹ ያቀረቡት በክልሉ በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ተመድበን እንማር ጥያቄ ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰው ክልሉ የተመደቡበት ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ስለተረጋጋ ወደዚያው እንዲያቀኑ መልስ መስጠቱን አስረድተዋል።
ክልሉ ውስጥ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ላይ መመደብ አይቻልም ያሉት የሥራ ኃላፊው በየትኛውም ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን የሚያስተዳድራቸው የፌደራሉ መንግሥት በመሆኑ የተማሪዎቹን ደኅንነት የማስጠበቅም ኃላፊነት ስላለበት ተማሪዎቹ ወደነበሩበት ቦታ መመለስ እንዳለባቸው መክረዋል። ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ ፀጥታውን አረጋግቶና 75 በመቶ ተማሪዎቹን በድጋሜ መዝግቦ ትምህርት ስለመጀመሩ እየተናገረ ስለሆነም ባሕር ዳር ያሉት የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች የተሰጣቸው አማራጭ ወደ ቡሌ ሆራ እንዲጓዙ መሆኑንም አሰማኸኝ ተናግረዋል። በዚህ ካልተስማሙ ‹‹ተማሪዎቹ ቤተሰብ አላቻው ተፈናቃዮች አይደሉም›› ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ወደ ቤተሰቦቻቸው ሄደው የራሳቸውን አማራጭ መከተል እንጂ ከተማውን መበጥበጥ እንደማይፈቀድላቸው አስጠንቅቀዋል።
ይሁንና ተማሪዎቹ ጥያቄቸውን በኃይል ለማስፈጸም በመፈለግ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ገብተው አመጽ ለማስነሳት መሞከራቸውን ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሚፈልጉት መንገድ የአመፃቸው ተባባሪ ባለመሆናቸውም ከኹለት ሺህ 500 የሚልቁት ተማሪዎች በባሕር ዳር ከተማ በመንቀሳቀስ የኤቲኤም ማሽኖችን፣ ሱቆችንና ሆቴሎችን ሲሰባብሩ እንደሰነበቱ አሰማኸኝ አክለው ገልጸዋል። ከዚህ ባሻገርም ከተሽርካሪዎች ላይ እህል ሲዘርፉና በጸጥታ አካላት ላይ ድንጋይ ሲወረውሩ እንደነበርም አንስተዋል። ተንከባክቦ ባቆያቸው ሕዝብ ላይ ‹‹የጋጥወጥነት›› ተግባር መፈጸማቸውን የጠቀሱት አሰመኸኝ ድርቱ ተገቢ ባለመሆኑ ከተጠለሉበት መጠለያ በአስቸኳይ እንዲወጡ መመሪያ ተላፎላቸዋልም ብለዋል።
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሙሉቀን አየሁ በበኩላቸው ከቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የመጡ ተማሪዎችን ሕዝቡ ከኹለት ሳምንት በላይ ተንከባክቦ እንዳስቀመጣቸው በመግለጽ የክልሉ መንግሥትም ከተማሪዎች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመምከር ውሳኔ ቢያስቀምጥም ተማሪዎቹ ውሳኔውን ባለመቀበል ከነሱ የማይጠበቅ ተግባር ሲፈጽሙ መሰንበታቸውን አመልክተዋል። ተማሪዎቹ ከከተማው አቅም በላይ በመሆናቸው ከተማዋን ለቀው ሊወጡ እንደሚገባም ስጠንቅቀዋል። ‹‹ተማሪዎቹ በፍቅር የተቀበላቸውን ማኅበረሰብ እጁን አመድ አፋሽ አድርገውታል›› ሲሉም ከንቲባው ወቅሰዋል።
ሰሞኑን ተማሪዎቹ ፈጥረውት የነበረው ችግር ከመንግሥት ባለፈ የከተማውን ወጣቶች ቁጣ የቀሰቀሰ ሲሆን ወጣቶቹም ሲረብሹ የነበሩትን ተማሪዎች ፈጥነው አደብ እንዳስገዟቸውም ተሰምቷል።
ከአማራ ክልል በቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡት ተማሪዎች ቁጥር ሦስት ሺህ ሲሆን በፀጥታው ችግር ወደ ባሕር ዳር የሄዱት ቁጥር ከኹለት ሺህ 500 እንደሚበልጥ አሰማኸን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ቡሌ ሆራ ዩኒቨርሲቲ በታኅሣሥ ወር ባጋጠመው ችግር ትምህርቱን ለጊዜው ጋብ አድርጎ ችግሩን ለመፍታት በመወሰኑ ተማሪዎች ለቀናት ወደ ቤተሰቦቻቸው መሄድ አልያም በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ሆነው መጠባበቅ እንደሚችሉ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወሳል። ይሁንና ዩኒቨርሲቲው ችግሬን ፈትቻለሁ በማለት ተማሪዎቹ ከጥር 1/2011 ጀምሮ እንዲመለሱና ምዝገባ አካሂደው ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል። በዚህም 75 በመቶ ተማሪዎቹ ወደ ትምህርት ገበታቸው መመለሳቸውን የተናገሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ጫላ ዋታ (ዶ/ር) እየተመለሱ መንገድ ላይ ያሉና እንዲጠብቋቸው በስልክ ጭምር የጠየቁ ተማሪዎቸ መኖራቸውን በመጥቀስ በትዕግስት እንደሚጠብቋቸው አክለው ገልጸዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here