ስደተኞች የኢትዮጵያ ዜግነት መብት ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ

0
1087

ስደተኞችን ኢትዮጵያዊ ዜግነት የሚያስገኘዉ እና በሥራ ላይ ተሰማርተዉ ሀብት ማፍራት የሚያስችለዉ ረቂቅ አዋጅ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ፀድቋል። አዲሱ አዋጅ የስደተኞችን መብት ከፍ በማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ የዜግነት ጥያቄ እስከ ማቅረብ እና መስፈርቶችንም ካሟሉ ዜግነት ማግኘት እንደሚችሉ አስቀምጧል። በዚሁ አዋጅ ላይ ስደተኞች ኢትዮጵያዊ ዜግነት ማግኘትን በሚመለከት በደንብ ተብራርቶ የተቀመጠ ሲሆን ‹‹አግባብነት ያላቸው የኢትዮጵያ የዜግነት ሕግ ድንጋጌዎች የተቀመጡትን መስፈርቶች የሚያሟላ ማንኛውም እውቅና ያገኘ ስደተኛ ወይም ጥገኝነት ጠያቂ የኢትዮጵያን ዜግነት በሕግ ለማግኘት ማመልከት ይችላል›› ሲል ይደነግጋል። ይህም ደግሞ በአዋጁ ላይ እንደተጠቀሰዉ የዜግነት ጥያቄው ተቀባይነት ካገኘ እንደ ስደተኛ መቆጠር የሚያበቃበት ሁኔታ ይፈጠራል።
ረቂቅ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት በአዋጁ ላይ ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በተደረገ ውይይት የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ ባቀረበው ማብራሪያ በአሁኑ ሰዓት ከሃያ ስድስት አገራት የመጡ 955ሺሕ ስደተኞች በኢትዮጵያ ዉስጥ በተለያዩ የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ። ከእነዚህም አገራት መካከል በስደተኛ ብዛት ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሊያና ኤርትራ ከአንድ እስከ ሦስት ያለውን ደረጃ ይይዛሉ ሲል መግለጫው ያትታል።
ኤጀንሲው በመግለጫው እንዳብራራው ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው የስደተኛ ቁጥር እየጨመረ እንደመጣና አዲስ ሕግ ማውጣትም ያስፈለገበት ምክንያት በነባሩ ሕግ ተጨማሪ ስደተኞችን ማስተናገድ ችግር እንደሚፈጥር የታመነበት ስለሆነ ነው ተብሏል።
አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ስደተኞች በኢትዮጵያ ዉስጥ የመሥራትና ሀብት የማፍራት መብትንም የሚያረጋግጥ ነው። ከዚህም ጋር በተያያዘ ማንኛዉም ዕውቅና ያገኘ ስደተኛና ጥገኝነት ጠያቂ በኢትዮጵያ ዉስጥ በሕግ አግባብነት ባለው መሠረት በእርሻ፣ ኢንዱስትሪ፣ ዕደ ጥበብ ላይ መሰማራት ቢፈልግ ለውጭ ዜጉች ከተሰጡት መብቶች የተሻለውን ተጠቃሚ እንደሚሆን በተብራራ መልኩ ይገልፃል። የክልሎችን ስምምነት መሰረት በማድረግ የመሬት አጠቃቀሙ በሊዝ ዋጋ ሆኖ በየሰባት ዓመቱ የሚታደስ እንደሚሆን ተገልጿል። በረቂቅ አዋጁ ስደተኞች ወይም ማንኛውም ጥገኝነት ጠያቂ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ዐቀፍ ማኅበረሰብ ጋር በጋራ በመሆን ሰደተኞችን እና ኢትዮጵያዊያንን ተጠቃሚ ለማድረግ በሚሰራቸዉ ሥራዎች እንደ እርሻ፣ አካባቢ ጥበቃ፣ ኢንዱስትሪ አነስተኛና ጥቃቅን ዘርፎች ላይ ተሳተፊ እንዲሆኑ እና አብረው ከሚሰሩት ኢትዮጵያውያን ጋር ዕኩል አያያዝ እንደሚደረግላቸዉ አዋጁ ይገልፃል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዋጁ ለውይይት በቀረበበት ወቅት ተቃውሞዎች ተሰምተዋል። ‹‹ሌሎች አገራት አቅማቸውን አገናዝበው ነው ስደተኛ የሚቀበሉት የእኛ አካሄድ ግን ከዚህ የተለየ ነው›› ሲሉ የምክር ቤት አባሉ ኡጁሉ ኦባንግ የተቃውሞ ሐሳባቸውን አሰምተዋል። ኡጁሉ ‹‹የክልሎች ፍላጎት ባልተጠየቀበትና ባልተዋያዩበት ሁኔታ አዋጁ እንዲወሰን ማድረግ አግባብ አይደለም ብለው የስደተኞች ነባራዊ ሁኔታንም ታሳቢ ያደረገ አይደለም›› ብለዋል። የስደተኞች ሁኔታ በጋምቤላ አካባቢ ያለውን የፀጥታ ችግር ያባብሳል ሲሉ ደግሞ አወቀ አጥናፉ ለምከር ቤቱ ገልፀዋል። የምክር ቤት አባሉ ጨምረው በስደተኞች ዙሪያ የሚሠሩ ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች የፀጥታ ችግር ያስነሳሉ እየተባለ ስለሆነ ይህም ከግምት ውስጥ ቢገባ በማለት አሳስበዋል። በሌላ የምክር ቤት አባል የተነሳው ደግሞ ስደተኛ ማለት ደኻ ብቻ አይደለም በሰላም ዕጦት ምክንያት በስደት የሚገቡት ሀብታቸውን ይዘው ስለሚመጡ ከቀረጥ ነፃ የሚለው ነገር ቢቀር የሚል ሐሳብ አንጸባርቀዋል።
ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱት አስተያየቶችና ጥያቄዎች የሕግ፣ ፍትሕና ዲሞክራሲ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ፎዚያ አሚን ምላሽ ሲሰጡ ሕጉን አርቅቆ ወደ ምክር ቤት ያመጣው አካል ክልሎች እንደተወያዩበት እርግጠኛ ነው ብለዋል። አያይዘዉም በቋሚ ኮሚቴው ኹለት ጊዜ የሕዝብ ሐሳብን የሚሰማበት ሁኔታን አመቻችቶ ክልሎች እንዲገኙ ጥሪ ቢያደርግም ሊገኙ አልቻሉም ሲሉ ተናግረዋል። ቀረጥን በተመለከተ ለተነሳው ጥያቄ ሰብሳቢዋ ሲመልሱ ‹‹ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ስደተኞች በጣም ትንንሽ ዕቃ ይዘው እንደሚመጡ ገልፀው ከዛም ላይ ቀረጥ እንዲከፍሉ ማድረግ ሰብዓዊነት አይደለም›› ብለዋል ። የስደተኞች ጉዳይ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 34/2010 በሦስት ተቃውሞ እና በአንድ ታዕቅቦ በአብላጫ ድምጽ ፀድቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here