የዕርቃን ዳንስ ቤቶችን ሰደድ፥ ‘ሳይቃጠል በቅጠል’

0
794

ሉላዊነት ከየትኛውም የሰው ልጆች የታሪክ ዘመን የበለጠ አሁን ዓለምን አቀራርቧል። የሰው ልጅ የአዕምሮ ውጤት በመሆኑ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በመታገዝ በአንዱ የዓለም ጫፍ የተተነፈሰ በዛው ቅጽበት ወይም በደቂቃዎች ልዩነት የተቀረው ዓለም ሊዳረስ ይችላል። ዕድሜ ለሰው ልጆች ሥልጣኔ!
ሉላዊነት የዓለም ሕዝቦችን እንዲቀራረቡ በማድረግ በባሕል፣ በንግድ፣ በፖለቲካና በመሣሰሉት የሰው ልጆች ፍላጎቶችን መሠረት ያደረገ ትስስር በመካከላቸው እንዲኖር አድርጓል። ትስስሮቹ በጎ የሆኑትን ያህል ምንም እሴት የማይጨምሩ፣ ከባሕል፣ ከሕግ እንዲሁም ከሞራል ያፈነገጡ በተለምዶ “መጤ” ባሕሎችም እንዲበራከቱ አድርጓል።
መዲናችን አዲስ አበባ በተዘዋዋሪ ሉላዊነት ከሚያደርስባት አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ ባሻገር የበርካታ መንግሥታት ዲፕሎማቶችና ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ መሆኗ አዳዲስ ባሕሎች/ልምዶች፣ የኑሮ ዘይቤ እንዲኖር በር ከፍቷል።
ይህ ከተቀረው ዓለም መቀራረብ ለመልካም ዕሴቶች ልውውጥ የሚጠቅመውን ያህል “መጤ” ለሚባሉና ጎጂ ባሕሎች/ልምዶችም ማጋለጡ አይቀርም። በሕግ ያልተፈቀዱ፣ የብዙኃኑን ሞራልና የሥነ ምግባር የማያከብሩ ወይም የሚያጎድሉ፣ ዕሴት የማይጨምሩ፣ ሰብኣዊ ክብርን የሚያዋርዱ በተለይ ለኢትዮጵያ እንግዳ የሆኑ የባሕል ወረራዎች በስፋት ይስተዋላሉ። ከእነዚም መካከል የምሽት ራቁት ዳንስ ቤቶች አንዱ ነው።
አዲስ ማለዳ በምሽት የራቁት ዳንስ ቤቶች ዙሪያ የራሷን ዳሰሳና ቅኝት በማድረግ እንዲሁም መረጃና ማስረጃዎችን በማሰባበብና በመተንትን ለተደራስያን በሐተታ ዘ ማለዳ ዐምድ ላይ አቅርባለች። በአዲስ አባበ በተለያዩ አካባቢዎች ውስጥ ጋዜጣዋ ባደረገችው ቅኝትና ባሰባሰበችው መረጃ መሠረት የራቁት ዳንስ ቤቶች የመበራከት አዝማሚያ እንዳለ ተረድታለች። አንዳንዶቹ የምሽት ራቁት ዳንስ ቤቶች ከዕርቃን ዳንስም በዘለለ ልቅ የአደባባይ ወሲብ መፈፀሚያ ለመሆናቸው የአዲስ ማለዳ የስውር ቅኝት አረጋግጧል።
‹ራስ አሲዞ የመንግሥት ያለህ! የሕግ ያለህ!› የሚያስብል ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋልም ትላለች። የሆነው ሆኖ አዲስ ማለዳ እነዚህን ልቅ የዕርቃን ዳንስ ቤቶች የመስፋፋት ዝንባሌ ለመግታት አስፈፃሚ አካላት ጥርስ የሌለው አንበሳ ሆነው መገኘታቸውን ተረድታለች። የተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ስውር እጆችም በተጨማሪ ምክንያትነትም ይጠቀሳል።
ለራቁት ዳንስ ቤቶቹ መበራከት እንደምክንያት የሚጠቀሰው የሕግ ክፍተት መኖሩን ነው። ጎጂ “መጤ” ባሕልን በመከላከል ረገድ የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊነት ሲኖርበት፥ የንግድ ፈቃዳቸውን በተመለከተ ደግሞ የከተማው ንግድ ቢሮ ኃላፊነት አለበት። ይሁንና እነዚህ ኹለት የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት በሕግ የተሰጣቸውን ሥልጣን እስከምን ድረስ ነው እየተጠቀሙ ያለው የሚለው ጥያቄ መመለስ ያለበት ጉዳይ ነው።
በተለያዩ የኃላፊነት የእርከን ደረጃዎች የሚገኙ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት የላላ ክትትልና ቁጥጥር መኖር ወይም ከነአካቴው ቁጥጥር እና ክትትል አለማድረግ አንዱ ምክንያት ነው። አዲስ ማለዳ እነዚህ አካላት ሥራቸውን ባለመወጣታቸው መጠየቅ አለባቸው ትላለች።
በኹለተኛ ምክንያትነት የሚጠቀሰው ደግሞ የእነዚሁ የራቁት ዳንስ ቤቶች ተጠቃሚዎች ወይም ባለቤቶች ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚያሳድሩ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች መሆናቸው እንዳይፈፀም አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ዙሪያ ባደረገችው ቅኝት ለመረዳት ችላለች።
በምሽት የዕርቃን ዳንስ ቤቶች ውስጥ ለመሥራት በዋነኛነት ተጋላጭ የሆኑት ሴቶች ሲሆኑ ማኅበራዊ ዳራቸውም ድህነት፣ ሥራ አጥነትና ከገጠር ወደ ከተማ መፍለስ ናቸው። በተጨማሪም ከዐረብ አገራት የተመለሱ ሴቶች እንደሚበዙበት የአዲስ ማለዳ ቅኝት ያመለክታል።
እየተበራከተ የመጣውን የዕርቃን ዳንስ ቤቶች ለመቀነስ በዋነኛነት የሚያስፈልገው የሕግ ተፈፃሚነት እንዲኖር ማድረግ ነው። በተለይ የአዲስ አበባ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው በተለያየ የኃላፊነት እርከን ከሚገኙ የመንግሥት አስፈፃሚ አካላት ጋር በመተባበር የተቀናጀ ሥራ መሥራት ይጠበቅበታል። በአጭሩ ሥራው መሬት እንዲረግጥ ከምንም ነገር በላይ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያስፈልጋል።
አዲስ ማለዳ በተለይ ሴቶች የሚደግፉ መንግሥታዊ የሆኑም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የተቀናጀ ሥራ በመሥራት ሰብኣዊ ክብርን የሚነካ ሥራ የሚሠሩትን ሴቶች ከዚህ አስከፊ ሕይወት ሊያላቅቋቸው ይገባል ትላለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here