ኦነግ በመከላከያ የአየር ድብደባ ደርሶብኛል ሲል የመንግሥትን መግለጫ አጣጣለ

0
637

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በቄለም ወለጋ ዞን በጊዳሚ ወረዳ በቄለም ከተማና አካባቢዋ በሦስት የተለያዩ ቦታዎች በሚገኙ የጦር አባላቶቹ ላይ ያነጣጠረ ለኹለት ተከታታይ ቀናት ጥር 4 እና 5 የቆየ የአየር ጥቃት ደርሶብኛል አለ።
ኦነግ መግለጫውን ያወጣው የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ይልማ መርዳሳ (ብርጋዴር ጄኔራል) በአካባቢው ከምድር ውጊያ እና ከሰፈር ግጭት ያለፈ የጦር አውሮፕላን መጠቀም የሚያስገድድ ሁኔታ ስሌለ የጦር አውሮፕላን አልተጠቀምንም ባሉ ማግስት ሲሆን የተካሔደውን የአየር ድብደባ ለመካድ መሞከር ማለት “ግመል ሰርቆ ኣጎምብሶ” እንደሚባለዉ ዓይነት ሊደበቅ የማይቻለውን እውነታ ለመሸፈን የሚደረግ ከንቱ ልፋት ነው በማለት አጣጥሎታል።
በተጨማሪም የመከላከያ ሠራዊትን ‹‹የኢሕአዴግ እግረኛ ጦር ሠራዊት›› ብሎ የሚወነጅለው ኦነግ ከአየር ድብደባ በተጨማሪም ‹‹የኢሕአዴግ እግረኛ ጦር ሠራዊት በዚሁ አካባቢ ሰላማዊውን ሕዝብ በመግደል፣ መኖሪያ ቤቶቹን በማቃጠል፣ ንግድ ቤቶቹን በማፈራረስና ንብረት በመዝረፍ እንዲሁም ሰዎችን በጅምላ በማሰርና በማሰቃየት እኩይ ድርጊቶች ላይ ተጠምደዋል›› ሲል ወንጅሏል።
በተቃራኒው መንግሥት የአየር ጥቃት ፈፅሟል ተበሎ የሚወራው ሠራዊቱን ለማጥላላት የተሰራ ሴራ ነው ያሉት ብርጋዴር ጄኔራሉ ጥር 4 እና 5 በምዕራብ ወለጋ፣ ቄለም ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ ከ17 በላይ የባንኮች ቅርንጫፎች እንደተዘረፉና ንብረታቸው እንደወደመ እንዲሁም የወረዳ ጽሕፈት ቤቶች እንደወደሙ መዘገቡ አይዘነጋም። እንደ ክልሉ መንግሥት የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ መግለጫ ይህ የተፈፀመው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና በኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንክ ቅርንጫፎች እንዲሁም በኦሮሚያ ብድርና ቁጠባ ተቋም ላይ ነው።
የመንግሥት ባለሥልጣናት ዝርፊያውን የፈፀሙት የኦነግ ታጣቂ ኃይሎች ናቸው ቢሉም ይህ የመንግሥት ክስ ፍፁም ከእውነት የራቀ ነው ሲል ኦነግ አጣጥሏል። ‹‹ኦነግ የለውጡን ሒደት ለማሳካት በሙሉ ልቡ እየሠራ ባለበት ሁኔታ የተለያዩ እንቅፋቶችን በመፍጠር ከመንግሥት ጋር ያደረገውን ሥምምነት ተግባራዊ እንዳያደርግ መሰናክል የፈጠረው ራሱ ኢሕአዴግ ነው›› ሲል ኦነግ በመግለጫው አስቀምጧል።
በሌላ በኩል በምዕራብ ኢትዮጵያ ታጥቀው ሰላም ሲያውኩ ነበር ያላቸውን 835 ታጣቂዎች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን የምዕራብ ኢትዮጵያ ኮማንድ ፖስት የገለጸ ሲሆን በማኅበራዊ ሚዲያው ግነት በተሞላበት መልኩ ይህን ያህል ባንክ ተዘረፈ እና አውሮፕላን ድብደባ አደረገ የሚለው የሰሞኑ ዘገባ ሐሰት ነው ሲል ይህን ያጣጣለው ኦነግ በጊዳሚ ወረዳ ውስጥ በአየር ኃይልና በእግረኛ ጦር በተካሔደው በዚህ ጥቃት እስካሁን የተረጋገጡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት የሰባት ሰላማዊ (‹‹ትጥቅ-ኣልባ››) ዜጎች ሕይወት ማለፉን ገልጿል። ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የተደረሰበት ሥምምነት በሰላማዊ መንገድ ተግባራዊ ሆኖ አገርና ሕዝብም ሰላም ያግኙ ዘንድ ይህ ጦርነት በአፋጣኝ መቆም አለበት ሲልም ኦነግ አሳስቧል። የኹለቱም ወገን ስሞታና ቅሬታዎች በገለልተኛ ወገን ተመርምሮና ተጣርቶ ሀቁ እንዲወጣ በማሳሰብ ኦነግ መግለጫውን አጠቃሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here