የተክለብርሃን አምባዬ ቤተሰብ አባል ሀብት የሆነዉና በተክለብርሃን አምባዬ ኮንስትራክሽን(ታኮን) የተገነቡት ዘመናዊ የሰንራይዝ ሪል እስቴት ቤቶች ለኖህ ሪል እስቴት መሸጣቸዉን የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገለጹ። ሽያጩ መካሄዱን አዲስ ማለዳ ከኖህ ሪል እስቴት የሽያጭ ሰራተኖች ለማረጋገጥ ችላለች። ሽያጩ መንግሥት በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ዘመቻ ከመጀመሩ ጋር ተያይዞ በባለቤቶቹ ሪል እስቴቱን እንደሸጡት የአዲስማለዳ ምንጮች ይገልጻሉ።
የሪል ስቴቱ ሽያጩ በተከናወነ በወሩ ሠራተኛዉ መስማቱን የተገኘዉ መረጃ ያመላክታል። የታኮንም ሆነ የሰንራይዝ ሠራተኞች ጉዳዩ ካለቀ በኋላ እንደተነገራቸዉ ለአዲስ ማለዳ ጋዜጣ አስታዉቀዋል።
በዚህ ጉዳይ አዲስ ማለዳ የሰማችዉን መረጃ ይዛ ወደ ኖህ ሪል እስቴት ስልክ በመደወል እና በአካል በመገኘት የተለያዩ የሥራ ክፍል ኃላፊዎችንና የሽያጭ ሰራተኞችን ለማነጋገር ሞክራለች። ሆኖም ገዢዉ ኖህ ሪል እስቴት መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆኑ ያለዉን አጠቃላይ የግዢ ሂደት ለማወቅ አልተቻለም።
ቅጽ 3 ቁጥር 136 ሠኔ 5 2013


