በኤሌክትሮኒከስ የሙዚቃ ስልት በአጭር ጊዜ ዝናን ያተረፈው ኢትዮጵያዊው ሙዚቀኛ ‹‹ሮፍናን›› በኮክ ስቱዲዮ አፍሪካ አዲሱ ምዕራፍ ላይ እንደሚሳተፍ ተገለፀ። ኮክ ስቱዲዮ ጥር 3 ቀን ባወጣው መግለጫው በዚህኛው ምዕራፍ ላይ ሮፍናን በፕሮዲውሰርነትና በሙዚቀኛነት እንደሚሳትፍ የተገለፀ ሲሆን ይህም በኮክ ሰቱዲዮ ታሪክ አንድ አርቲስት በሁለት ዘርፍ እንዲሳተፍ ሲደረግ ሮፍናን የመጀመሪያው ነው ተብሏል። ሮፍናን በቅርቡ ‹‹GET TO WORK›› በሚል የሙዚቃ ሥራው ዓለም ዐቀፋዊ ዝናን ማትረፉ በኮክ ስቱዲዮ መግለጫ ተጨምሮ ተገልጿል።
ኮክ ስቱዲዮ ከተለያዩ አህጉር በቀል እና ዓለም ዐቀፍ የሙዚቃ ዝግጅት ባለሞያዎች ጋር የመሥራት ዕድልን የሚፈጥር እና ከተለያዩ የአፍሪካ አገራት የሚገኙ አዳዲስ የሙዚቃ ተሰጥኦዎችን የሚያገናኝ የውድድር ሐሳብ የሌለው መድረክ ነው። ከዚህ ቀደም በርካታ ድምጻውያን ከኢትዮጵያ የተሳተፉ ሲሆን ለአብነት ሳሚ ዳን፣ ቤቲ ጂ፣ እንዲሁም በቡድን ጃኖ ባንድ የሚጠቀሱ ሲሆን ልጅ ሚካኤል በኹለት ዙር መሳተፉ የሚታወስ ነው።
ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011