ከሰሞኑ የፌስቡክ መንደር ጎን ለጎን በተቀመጡ ትይዩ ፎቶ ግራፎች ደምቆ ሰንብቷል፡፡ መነሻው በውል ያልታወቀው ይኸው የፎቶ ልጠፋ ሳምንት አንድ ሰው ከ10 ዓመት በፊት የነበረውንና ዛሬን የሚያነፃፅሩ ፎቶ ግራፎቹን እየለጠፈ ‹‹10 years challenge›› ሲል ሰንብቷል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ ታዲያ ከሚለጠፉት ልዩነት ሰፊ ፎቶ ግራፎች ይልቅ በአስተያየት መስጫ ሳጥኖች ላይ ሰፍረው የሚገኙት አስተያየቶች የበለጠ ቀልብ ሳቢ ሆነው ሰንብተዋል፡፡
በሌላ በኩል ፌስቡክንም ሆነ ፎቶግራፍ የመነሳትን ብሂል ዘግይተው የተቀላቀሉ ፌስ ቡከኞች ከ10 ዓመት በፊት የነበራቸውን መልክ የሚያሳይ ቅሪት ባለመያዛቸው ሲቆጩም ተስተውለዋል፡፡
በተመሳሳይ ‹‹የ10 ዓመታት መልክ ልዩነቴን በፎቶ ለማሳየት ብፈልግም ከ10 ዓመት በፊት መንፈስ እንጂ ሥጋ ስላልነበረኝ አልቻልኩም›› በሚል የፌስ ቡክ ግድግዳቸውን ብዙዎችን ፈገግ ለማሰኘት የተጠቀሙበትም አልጠፉም፡፡ የከፍተኛ ባለሥልጣናት የዓመታት ልዩነት ፎቶግራፎች እየተለጠፉም የሳቅ ምንጭ ሆነው ሰንብተዋል፡፡
በብዙዎች ዘንድ በሺዎች የሚቆጠሩ ጋርዮሾችን ያገኘው ተያያዥ ሰሞነኛ የፌስ ቡክ ልጠፋ ግን ‹‹የስምንት ዓመቱ ልጅ ‹10 years challenge› በሚል ፎቶ ለጠፈ›› የሚለው ሽርደዳ ነው፡፡
ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011