የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች (ክፍል ሁለት)

0
1049

የምግብ እና መድኃኒት አስተዳደርን እና ቁጥጥርን በተመለከተ ረቂቅ አዋጅ ወጥቶ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተመርቷል። ኢሳያስ መኮንን ረቂቁን ተመልክተውና ከነባሮቹ አዋጆች እና አሠራሮች አንጻር በመገምገም ሙያዊ ትችታቸውን ያቀረቡበትን መጣጥፍ ሁለተኛ እና የመጨረሻ ክፍል እነሆ።

 

(ካለፈው የቀጠለ)
የቅሬታ እና የይግባኝ ሥርዓት
አስተዳደራዊ ቅጣቶች ላይ የይግባኝ ሥርዓት መዘርጋቱ የተሻለ ሆኖ ሳለ የይግባኝ ሥርዓቱ ግን መልሶ በቅሬታ መልክ ለተቋሙ በሚሰጥ መልኩ መደራጀቱ እንዲመጣ የተፈለገውን ፍትሕ ለማምጣት መሰናክል ሊሆን ይችላል። በተለይ በአገራችን ‘ኮዲፋይድ’ የአስተዳደር ሥነ ሥርዓት የሕግ ማዕቀፍ የሌለ በመሆኑ፥ የአስተዳደር ፍርድ ቤትም ያልተደራጀ በመሆኑ ችግሩን የሚያባብስ ይሆናል። በውሳኔ ላይ ቅር የተሰኙ ወገኖች ቅሬታቸውን የሚያቀርቡበት ሥርዓትም በዚህ ሕግ ላይ አለመካተቱ ቅሬታ አቅራቢዎች ይግባኛቸው በምን አግባብ እንደሚታይ ግልጽ አይደለም። እዚህ ጋር ግንዛቤ ሊያዝ የሚገባው እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች በዝርዝር ሕግም የሚሸፈኑ ሳይሆኑ በፍሬ ነገር ሕግ በአዋጅ ደረጃ ብቻ የሚታዩና መብት እና ግዴታን የሚፈጥሩ የሕግ ድንጋጌዎችን በሚመለከት በሕግ አውጪው ብቻ በግልጽ መደንገግ የሚገባው ነው።
በአስተዳደራዊ ውሳኔ ላይ ያላቸውን ቅሬታ በይግባኝ መልክ ለማቅረብ የተሻለው አሠራር ከላይ የተጠቀሰው አዋጅ ለዚህ መፍትሔ ይሆናል የሚል ሐሳብ አለ። በፌዴራል የታክስ አስተዳደር አዋጁ ላይ በማናቸውም የግብር ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያለው አካል ቅሬታውን በገቢዎች ሚኒስትር ወይም በገቢዎች ኤጀንሲ እና በሥሩ በተደራጁ የተለያዩ ንዑስ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ውስጥ የተደራጁ ቅሬታ ሰሚ አካላት ስላሉ ለዚህ መፍትሔ ሆኖ ያገለግላል። የቅሬታ አሰማሙ በምን ዓይነት አግባብ እንደሆነ፣ ቅሬታው መቼ መቅረብ እንዳለበት፣ ውሳኔ በምን አግባብ እንደሚሰጥ እና ሌሎችንም ድንጋጌዎችን የያዘ ነው። በጸሐፊው እምነት የግብር ውሳኔ አስተዳደራዊ ቅሬታ አቀራረብ መንገድ ያለው አሠራር በዚህ ተቋምም ያለው አስተዳደር አካል በሚወስነው ውሳኔ ላይ የቅሬታ እና የይግባኝ አቀራረብ መንገድን ማካተት ያለበትና በሕግ አውጪው ብቻ የሚወጣ ሕግ ከመሆኑ አኳያ በዚሁ ሕግ ተካቶ መውጣት ይገባዋል።
የወንጀል ቅጣቶች ድንጋጌዎች አቀራረጽ ችግሮች
በመሠረቱ በወንጀል ሕግ አቀራረጽ መርሕ መሰረት የሕጉ አወቃቀር በጣም ጠቅላላ ከሆነ ክፍል ጀምሮ ወደ አነስተኛ ነጥብ ወይም ንዑስ ቁጥር የሚወርድ ነው። ሕጉ በተለያዩ ክፍልፋዮች የሚዋቀረው ከጠቅላላው ክፍል አንስቶ እስከ ንዑስ ቁጥር ድረስ በተዘረዘሩት ጉዳዮች መካከል አንድነትና ልዩነት ስለሚኖር ነው። ይኸውም በታላቅ ክፍል ውስጥ የተዘረዘሩት ጉዳዮች ተመሳሳይነት ያላቸው ሲሆኑ የሕጉ ክፍልፋይ ወደታች እየወረደ ሲሔድ በእያንዳንዱ ክፍልፋይ መካከል ልዩነት ስለሚኖረው ነው። ሕጉ ሥርዓት ባለው መንገድ መዋቀሩንና በእያንዳንዱ መደብ የሚገኙ ጉዳዮች በመካከላቸው ቅርበት ወይም የእርስ በርስ ግንኙነት ስላላቸውም ጭምር ነው። ሕጉም በእያንዳንዱ ክፍልፋይ አርዕስት የሚሰጠው ሲሆን ከክፍልፋዮቹም አርዕስት ብቻ ለጉዳዩ አግባብነት ያለውን ቁጥር በቀላሉ ማግኘት ከማስቻሉም በላይ በክፍልፋዩ የተመሠረተው ሕጉ ጥበቃ በሚያደርግለት መብት ዓይነት ስለሚሆን ጥቃት የደረሰበትንም መብት ምን እንደሆነ ለመለየት ስለሚያስችልና አለመግባባትን ስለሚያስወግድ ነው። በተጨማሪም ድርጊቶች በየትኛው ድንጋጌ እንደሚያስቀጡ ከታወቀ የሚከተለው ጥያቄ በአንድ መደብ ከተመደቡ ወንጀሎች መካከል ለአንድ ጉዳይ በጣም አግባብነት ያለው የትኛው ቁጥር ወይም ንዑስ ቁጥር ነው የሚለውን ለመለየት ይረዳናል። ይህም አስፈላጊ የሚሆንበት ምክንያት አንድን ወንጀለኛ መክሰስ ወይም መቅጣት የሚቻለው ወንጀሉ የተደራራቢነት ጠባይ እስከሌለው ድረስ አግባብ ባለው አንድ ቁጥር ወይም ንዑስ ቁጥር ብቻ መሆን ስላለበት ነው።
በሌላ በኩል የወንጀል ሕግ ኅብረተሰብን ከጉዳት ለመጠበቅ ሲሆን እንደ ወንጀል የሚቆጠሩ ድርጊቶችና ለነዚህ ድርጊቶች ተገቢ የሆኑ ቅጣቶች ተዘርዝረው የሚገለጹበት ሕግ ነው። የወንጀል ሕግና የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር መሠረታዊ ዓላማዎችም የወንጀል ዓይነቶችን አስቀድሞ በማስታወቅ የአንድ ኅብረተሰብ አባላት ይህን አውቀው ከጥፋት እንዲታቀቡ ማድረግና ይህን ማስጠንቀቂያ በማይከተሉ ላይ ቅጣትን መፈፀም ናቸው። በዚህም መሰረት የተከለከሉ ድርጊቶችን ወጥነት ባለው በግልጽ በመዘርዘር የወንጀል ሕግ የአንድ ኅብረተሰብ አባላት መብታቸውንና ግዴታቸውን የሚያውቁበት መሣሪያ ጭምር ሆኖ ያገለግላል።
በረቂቅ አዋጁ ላይ በአንቀጽ 66 ላይ የተመለከቱት ንዑስ አንቀጾች አቀራረፅ ወጥነት የጎደለውና የወንጀል ድርጊቶቹን ዓይነት በዓይነት ዘርፍ በዘርፍ ለይቶ የማያስቀምጥ ነው። እነዚህ ድንጋጌዎች ከላይ ለአስተዳደር ቅጣቶች በተቀመጠው አግባብ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሲያስቀምጥ የወንጀል ቅጣቶችን የሚያስከትሉ ወይም የሚያስወስዱ ጥፋቶችን ምንነት ግልጽና በዘርፍ ዘርፍ በመለየት ማስቀመጥ ይገባው ነበር። በዚህም መነሻነት በጸሐፊው እምነት ረቂቅ አዋጁ የወንጀል ቅጣት ድንጋጌዎች ራሱን በቻለ ንዑስ ክፍል ተደራጅቶ ንዑስ አንቀጽ 1፣ 2፣ 3 እና 10 የምርት ደኅንነት አጠባበቅ ጥሰትን በአንድ አንቀጽ፣ ንዑስ አንቀጽ 4፣ 5 እና 16 ከብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ድንጋጌዎች ጥሰትን በአንድ አንቀጽ፣ ንዑስ አንቀጽ 7፣ 8፣ 11 እና 12 ስለ መድኃኒት እና የሕክምና መሣሪያ ሽያጭ እና ሥርጭት ድንጋጌዎች ጥሰት፣ ንዑስ አንቀጽ 6፣ 25 እና 17 የጤና ተቆጣጣሪዎች ሥራን ማሰናከል እና ሪፖርት የማድረግ ድንጋጌዎች ጥሰት በአንድ አንቀጽ ከንዑስ አንቀጽ 20 እስከ 24 የትንባሆ እና የአልኮል ምርቶት ሽያጭ እና አጠቃቀም ክልከላዎች በአንድ አንቀጽ፣ ንዑስ አንቀጽ 18 እና 19 የማስታወቂያ ፕሮሞሽንና የስፖንሰርሺፕ ድንጋጌዎችን ጥሰትን በአንድ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 14 እና 15 የደም እና የደም ተዋፅዖ አሰጣጥ እና ደኅንነት ድንጋጌዎች ጥሰትን በአንድ አንቀጽ ማድረግ ሌሎች አንቀጾችን ደግሞ ራሳቸውን በቻሉ አንቀጾች ማስቀመጥ የተሻለ አቀራረብ ነው።
በአገራችን ከዚህ ቀደም የወንጀል ቅጣቶችን አስመልክቶ የሚደረጉ ሕጎች ከዚህ ረቂቅ አዋጅ ጋር ሲተያይ የተሻለ አቀራረብ ያላቸው ናቸው። ለአብነት ያህል የታክስ አስተዳደር አዋጅን ብንመለከት የአስተዳደራዊ እርምጃን ሲደነግግ የሕጉ አንድ ምዕራፍ በማድረግ በዘርፍ ዘርፍ የጥፋቶቹን ዓይነት በመለየት የሚያስከትሉትንም የቅጣት ልክ ለይቶ ያስቀምጣል (የፌዴራል ታክስ አስተዳደር አዋጅ 983/2008 አንቀጽ 116 እስከ 133 ያሉትን ድንጋጌዎች መመልከት ይቻላል)።
የወንጀል ቅጣቶች መጠን እና የአጥፊነት ሁኔታን በተመለከተ
በወንጀል ሕግ ልዩ ክፍል ውስጥ ለተዘረዘሩት የወንጀል ዓይነቶች ኃላፊነትንና የቅጣትን ዓይነትና መጠን ለመወሰን ሕግ አውጪው ግምት ውስጥ የሚያስገባቸው ልዩ ልዩ ሁኔታዎች ወይም ምክንያቶች ይኖራሉ። እነዚህ ሁኔታዎች በኹለት ክፍሎች የሚመደቡ ሲሆን ቁሳዊና ግላዊ ሁኔታዎች በመባል ይጠራሉ። ቁሳዊ ሁኔታዎች የአንድን የወንጀል ድርጊት ከባድነት ለመመዘን ግምት ውስጥ የሚገቡና ከወንጀሉ የተነሳ የሚደርሰውን ጉዳት ወይም የሕግ ጥበቃ በሚደረግላቸው መብቶች ላይ ሊደርስ የሚችለውን የጉዳት አደጋ የሚያካትቱ ሁኔታዎች ሲሆኑ፥ ግላዊ ሁኔታዎች ደግሞ የወንጀል አድራጊውን ጥፋተኝነት ለመወሰን በግል መሟላት ያለባቸውን መመዘኛዎች ግምት ውስጥ የሚያስገቡ ሁኔታዎች ናቸው።
ለእያንዳንዱ ወንጀል የሚደነገገው ቅጣትም የወንጀሉን ከባድነት ወይም ጥበቃ የሚደረግለትን መብት ትልቅነትና የወንጀለኛው አደገኛነት ግምት ውስጥ ገብቶ ነው። ሕግ አውጪው ቁሳዊና ግላዊ ሁኔታዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት ለእያንዳንዱ ወንጀል የበላይና የበታች የቅጣት ወሰን የሚደነግግና በተጨማሪም የቅጣት አፈፃፀምን የገንዘብና የእስራት ቅጣት አጠቃላይ የበታችና የበላይ ወሰን አድርጎ የሚቀረጽ ነው።
ሕግ አውጪው ወንጀለኞችን በአካል አስቀርቦ የሚመረምርና የእያንዳንዱን ወንጀለኛ አደገኛነት የሚያረጋግጥ አካል ባለመሆኑ የተወሰኑ መመዘኛዎችን በመጠቀም ለተለያዩ ወንጀሎች የተለያዩ ቅጣቶችን ይደነግጋል። እነዚህ የቅጣት ድንጋጌዎች የወንጀሉንና የወንጀለኛውን አደገኛነት ግምት ውስጥ የሚያስገቡ ሲሆኑ ለአንድ ወንጀል ድርጊት የሚደነገገው ቅጣት ቁርጥ ያለና በግልጽ የተወሰነ ሳይሆን በተወሰነ አነስተኛና ከፍተኛ ወሰን ውሰጥ የሚገኝ ወይም በአማራጭ የሚደነግግ ነው።
በረቂቅ አዋጁ ላይ የተቀመጡት የወንጀል ድንጋጌዎች ሁሉንም አጥፊዎች በአንድ ፈርጅ የሚያስቀምጥ ከወንጀል ሕግ መርሕ አንጻር ተገናዝቦ የቀረበም አይመስልም። የእርምጃው ልክም ዝቅተኛ፣ መካከለኛ ወይም ከባድ የሆኑትን በአግባቡ ለክቶ እና ለይቶም የማስቀመጥ ችግሮች ይታይበታል። በሌላ አገላለጽ ረቂቅ አዋጁ በአንቀጽ 66 ላይ ስለ ቅጣቶች ሲደነግግ ጥፋቱን፣ የጥፋቱ ጥልቀትንም ሆነ የእርምጃ አወሳሰድ ልኮችን በአንድ ላይ በዐሥር ንዑስ አንቀጾች አጭቆ የያዘ ነው። ይህ ዓይነት አቀራረብ በአሠራር ላይ ትልቅ ክፍተት የሚፈጥር ይሆናል። ለትርጉምም ክፍት የሚሆን ነው። በወንጀል ሕግ አንቀጽ 1 ሥር በግልጽ እንደተደነገገውም የወንጀል ሕግ ግቡ ወንጀል እንዳይፈፀም መካላከል ሲሆን ይህንን የሚያደርገው ስለ ወንጀሎችና ስለቅጣታቸው በቅድሚያ ማስጠንቀቂያ በመስጠት ማስጠንቀቂያነቱ በቂ ባልሆነበት ጊዜ ወንጀል አድራጊዎቹ ተቀጥተው ሌላ ወንጀል ከመፈፀም እንዲቆጠቡና ለሌሎች ማስተማሪያ እንዲሆኑ ወይም እንዲታረሙ በማድረግ ወይም ተጨማሪ ወንጀሎች እንዳይፈፀሙ እርምጃዎች እንዲወሰዱባቸው በማድረግ ነው።
የቅጣት ልኮቹም የፋብሪካ ባለንብረትን፣ ጅምላ አከፋፋይን እና ቸርቻሪን በአንድ ላይ ደማምሮ ተመሳሳይ ቅጣትም አዝሎ የተቀመጠ ነው። እንዲሁም የቅጣት ልኮቹ የተጋነነ ሲሆንም ይታያል። የወንጀል ሕጉ ላይ ራሱ በቀላል የሚያስቀጣን ጉዳይ በዚህ ላይ ከፍተኛ ቅጣት የሚያስጥል ነው። እንዲህ ዓይነት አቀራረብ ከማስተማር እና ከማስጠንቀቅ ይልቅ ከፍተኛ ቅጣትን በመጣል አስፈራሪ ይዘት ያለው ነው። ይህ ዓይነት ድንጋጌዎች ኢንቨስትመንትን የማያበረታታም ይሆናል። በተለይም ባለሀብቶች ከሚያነሱት የተለያዩ ችግሮች አንጻር ነገሮችን ይባስ እየተወሳሰቡ እንዲሔዱ የሚያድርግ ይሆናል።
ለአብነት ያህል በንዑስ አንቀጽ 17 እና 25 ላይ የጤና ተቆጣጣሪ ሥራን ማሰናከል ጋር የተያያዙ ድርጊቶችን ለአንደኛው ጥፋት ከሦስት ወር በማያንስ ቀላል እስራት ሲቀጣ በሌላኛው ደግሞ ከአንድ ዓመት እስከ ሦስት ዓመት ቅጣት ያስቀምጣል። በሌላ በኩል ደግሞ ረቂቁ በንዑስ አንቀጽ 6 ላይ የጤና ተቆጣጣሪን ሥራ ከማሰናከል ጋር አያይዞ ሲደነግግ ማሰናከሉ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት ቅጣትን ያስከትላል ይልና በጤና ተቆጣጣሪው ላይ የሚደርስ ጉዳት ካለ የደረሰው ጉዳት ምንም ይሁን ምን ከሦስት ዓመት እስከ ዐሥራ አምስት ዓመት ቅጣት ጥሎ ይታያል።
የጤና ተቆጣጣሪ ራሱ ጉዳት ደርሷል በሚል ድፍን ያለ መሥፈርት እስከ ዐሥራ አምስት ዓመት የሚደርስ ቅጣት ማስቀመጥ ተገቢ ያልሆነ እና እጅግ ከፍተኛ የሆነ ነው። በድንጋጌዎቹ ላይ ቅጣቶች ሲጣሉ ረቂቅ አዋጁ ምን ዓይነት መሥፈርት እንደተከተለ ግልጽ አይደለም። በተጨማሪም በንዑስ አንቀጽ 13 ላይ ደምን የገንዘብ ወይም ሌላ ጥቅም በማግኘት የሰጠን ሰውን እስከ ሦስት ዓመት ቅጣት መጣሉ ይህ ደም የሚሰጠው ሰው የለመደ እና መተዳደሪያ አድርጎት ከሆነ ከሦስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ ቅጣትን የሚጥል ነው። በጸሐፊው እምነት የሰውነቱ አካል የሆነን ደም ሸጠኻል ተብሎ አንድን ሰው እስከ ሰባት ዓመት የሚደርስ ቅጣት መጣል ተገቢ ያልሆነ የተጋነነ ቅጣት ነው። በመሠረቱ ይህ ንዑስ አንቀጽ በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ ቁጥር 573 ላይ ያለ እና የተደገመ ሕግ ነው። በወንጀል ሕጉ ቁጥር 573 ላይ ራሱ የተቀመጠው የቅጣት ልክ በቀላል እስራት ወይም በመቀጮ የሚቀጣ መሆኑን ልብ ይሏል።
የድንጋጌዎች መደገም
የረቂቅ አዋጁ በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ እና ከዚያም በኋላ በተለያዩ አዋጆች የወጡ የወንጀል ድንጋጌዎች ላይ የወጡ ጥፋቶችን አካቶ ይዞ ይገኛል። ረቂቅ አዋጁ ይህንን ሲያደርግ በአንቀጽ 70 (3) ላይ በዚህ አዋጅ ከተደነገጉት ጉዳዮች ጋር የሚቃረን ማንኛውም ሕግ፣ ልማድ ወይም አሠራር ተፈፃሚነት አይኖረውም በሚል ብቻ ለመሻር ጥረት የሚያደርግ ነው። ይህ ዓይነቱ አቀራረብ የወንጀል ኃላፊነትን የሚመለከት ድንጋጌን ለመሻር ወይም ለማሻሻል መጠቀም ለትርጉም ክፍተት የሚፈጥር ለወደፊትም ያለመግባባት ችግር መነሻ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት አለ። የወንጀል ሕጉ ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎችን ለመለወጥ ረቂቅ አዋጁ መነሻ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በማብራሪያ ሰነዱ ላይ ስለማይገኝ ለመገመት አስቸጋሪ ያደርገዋል።
ይህንን አስተያየት በዝርዝር ምሳሌ ለማስቀመጥ ያህል በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 66 ንዑስ አንቀጽ 1፣ 2፣ 3 እና 10 ላይ ስለ ምርት ደኅንነት የሚደነግገው ሕግ በኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 527 ላይ ያለ ሕግ ነው። ኹለተኛ በንዑስ አንቀጽ 6 ላይ የጤና ተቆጣጣሪዎችን ሥራ ማሰናከል ጋር በተያያዘ የተቀመጠው ድንጋጌ በወንጀል ሕጉ ቁጥር 438 እና 441 ላይ ያለ ነው። ሦስተኛ በንዑስ አንቀጽ 9 በሙስና ወንጀሎች አዋጅ ቁጥር 881/2015 በግልጽ እና በማያሻማ መልኩ የተደነገገ ነው። አራተኛ በንዑስ አንቀጽ 13 ላይ ስለ ደም በገንዘብ ወይም በሌላ ጥቅም መነሻነት የተቀመጠው ድንጋጌ በወንጀል ሕግ ቁጥር 573 ላይ ያለ ነው። እንዲሁም በንዑስ አንቀጽ 7፣ 8፣ 15 ከመድኃኒት ማዘዣ፣ የመድኃኒት እና የሕክምና ዕቃዎች አጠቃቀም እና ዕውቅና ያልተሰጠው የሕክምና ሙከራም በወንጀል ሕግ ቁጥር 535 ላይ ያለ ሕግ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ጸሐፊው የረቂቅ አዋጁን በሚመለከትበት ወቅት ለመረዳት እንደቻለው የባለሥልጣኑ የሕግ ክፍል በተደጋጋሚ የሕግ መተላለፍ ፈፅመዋል ብሎ በፍርድ ቤት ክስ እንዲመሠረትባቸው ባደረጋቸው ጉዳዮች አፈፃፀም ላይ በተደጋጋሚ እንደተስተዋለው ምንም እንኳን ጥፋቶቹ መፈፀማቸውን በማስረጃ ማረጋገጥ ቢቻልም አዋጅ 661 በጉዳዮቹ ዙሪያ በቂ እና ተያያዥ የሆነ የፍሬ ነገር እና የወንጀል ቅጣት ሳያካትት በመቅረቱ የሕግ አፈፃፀም ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ስላሳደረ ተጓዳኝ ጉዳዮችን በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ማካተቱን ነው። ነገር ግን እነዚህ በረቂቅ አዋጁ ላይ የተቀመጡትና እና ከላይ በወንጀል ሕጉ ላይ የተጠቃለሉ ድንጋጌዎች መጀመሪያውኑም የነበሩ መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የወንጀል ሕጉ ላይ ያሉ ድንጋጌዎች መሠረት ተደርጎ ክስ ለማቅረብ እና ለማስጠየቅ የተደረገው ጥረት ያጋጠመውም ችግር ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። እንደሚባለው በሥራ ላይ ያለው አዋጅ በወንጀል ሕጉ በተሸፈኑ ነጥቦች ላይ ባሉ ኃላፊነቶች ላይ በተግባር ያጋጠመው ነገር ምንም እንደሆነ ለማወቅ የሚያስቸገር ነው። የወንጀል ሕጉንም ክፍተቶች ለማየት ውስብስብ የሚያደርግ ይመስላል። አንድ ሕግ መቀየር ያለበት ሕጉ በትግበራ ደረጃ ያጋጠሙትን ችግሮች ለመፍታት መሆን እንዳለበት የሕግ ሰነድ አዘገጃጀት ላይ የሚያትቱ ሰነዶች እና የዘርፉ ባለሙያዎችም የሚያምኑበት ነጥብ ነው። ይህም ሲሆን ዝርዝር ፍተሻ ተደርጎበት እንጂ እንዲሁ በደፈናው የሚሻሻል እና የሚለወጥም እንዳልሆነ የሚታወቅ ነው።
የወንጀል ቅጣቶችን ስለመደንገግ
በረቂቅ አዋጁ ላይ የወንጀል ቅጣቶችን ሲደነግግ በተለያዩ ንዑስ አንቀጾች ላይ በዚህ አዋጅ እና ይህንን አዋጅ ለማስፈጸም በሚወጣ ሕግ መሠረት በሚል አገላለጽ ‘ወደፊት ይወጣሉ’ በሚባሉ መሥፈርቶች ቅጣትና ጥሰት መሆናቸውን ያስቀምጣል። በዚህ ጉዳይ ላይ የረቂቅ አዋጁን አንቀጽ 66 ንዑስ አንቀጽ 4፣ 5፣ 8፣ 12፣ 14፣ 19፣ 20፣ 21፣ 22 እና 25 መመልከት ይቻላል። ይህ ዓይነት አቀራረብ ለትርጉም ክፍት ከመሆኑም በላይ በአዋጅ ላይ ተጠቃሎ መውጣት ያለበት ሥልጣኑም የሕዝብ ተወካይ የሆኑት የሕዝብ እንደራሴዎች ፊት ብቻ ተፈትሾ መጽደቅ ያለበት እንጂ ይህ ሥልጣን ወደፊት በሚኒስቶች ምክር ቤትም ሆነ በአስፈፃሚው አካል መውጣት የሚገባው አይደለም። ይህ ሕግ የወንጀል ኃላፊነቱን ሲያስቀምጥ በዚያው አያይዞ የጥፋቱ መነሻ የሆነውን ነገር በዚሁ ሕግ ላይ አካቶና ጨርሶ መሔድ ይገባዋል።
በረቂቅ አዋጁ ማብራሪያ ላይ “ባለሥልጣኑ አዋጅ ቁጥር 661ን ለማስፈፀም ያወጣቸውን ብዛት ያለቸውን የአፈጻጸም መመሪያዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አቅርቦ ነበር። ቋሚ ኮሚቴውም መመሪያዎቹን ከገመገመ በኋላ በሰጠው አስተያየት በመመሪያዎቹ የተካተቱ ብዛት ያላቸው ጉዳዮች በአዋጅ 661 ስር በግልጽ ያልተካተቱ ስለነበሩ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ ማስገባት ተገቢ መሆኑን ለአስፈጻሚ አካሉ በሰጠው ምክረ ሐሳብ አስታውቋል። በዚህ መሰረት ቁጥጥር የሚደረግባቸውን ምርቶች በበቂ ሁኔታ የፍሬ ነገር ድንጋጌ እንዲኖራቸው ተደርጓል። በእርግጥ እነዚህን ጉዳዮች በአግባቡ ለመቆጣጠር ተጓዳኝ በሆኑ በአዋጅ ደረጃ በሚደነገጉ የወንጀል ቅጣቶች እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች መደገፍ ስለሚኖርባቸው ረቂቅ አዋጁ ውስጥ መካተታቸው ተገቢ ነው። በዚህ መሰረት የምግብ ደኅንነትን የሚመለከቱ 15 የሚሆኑ አዳዲስ ድንጋጌዎች እንዲሁም የመድኃኒት እና ሕክምና መሣሪያ ደኅንነት፣ ጥራት እና ፈዋሽነትን/ውጤታማነት የሚመለከቱ 15 ሌሎች ድንጋጌዎች እንዲካተቱ ተደርጓል” በሚል በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ቁጥር 661 ከወጣ በኋላ ሲታዩ የነበሩ ችግሮች መልሰው መከሰቱም አይቀሬ የሚያደርገው ነው።
ይህ ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄም ሊያስነሳ ይችላል። በተለይም አገራችን ላይ የአስተዳደራዊ ሕግ አወጣጥ ሥነ ሥርዓት ሕግ ማዕቀፍ በሌለበት ሁኔታ በአንድ ተቋም የሚወጣን መመሪያ መጣስ የወንጀል ሕግ መጣስ ተደርጎ የሚቆጠር ከሆነ የወንጀል ሕግ መሠረታዊ መርሕ የሆነውን የሕጋዊነት መርሕ በግልጽ የሚቃረን ይሆናል።
በሌላ ዕይታ በወንጀል ሕግ አስተሳሰብ መሠረት በአንድ የወንጀል ሕግ ውስጥ የሚካተቱ የወንጀል ዓይነቶች በመሠረቱ ተመሳሳይ ባሕርያት ያላቸው ሲሆኑ ወንጀሎቹ ኅብረተሰቡ እንዲፈፀሙ የሚያደርጋቸው ተፈጽመው ከተገኙም በወንጀል ሕግ የሚያስቀጡ ናቸው። አንዳንድ ወንጀሎች ራሳቸውን ችለው የሚቆሙ ሳይሆን በዋናው የወንጀል ሕግ ጠቅላላ ድንጋጌዎችና በሌሎች አካላት በሚወጡ ሕጎች ዝርዝር መመዘኛዎችን የሚቋቋሙ የሚሆኑበት ሁኔታ አለ። እንደነዚህ ዓይነት ወንጀሎች የደንብ ተላላፊነት ወንጀሎች ተብለው ይጠራሉ። ሕግ አውጪ እነዚህ ዓይነት ወንጀሎችንና ሌሎች ዋና ወንጀሎችን ሲለይ ዋና ወንጀሎቹ ለምሳሌ ሰው መግደል፣ ስርቆት፣ አስገድዶ መድፈር… ወዘተ በተፈጥሯቸው ወንጀል የሆኑና ማንም ሰው ያውቃቸዋል ተብለው የሚገመቱ ሲሆኑ ሌሎቹ ድርጊቶች በተፈጥራቸው ወንጀል ባይሆኑም እነዚህን ድርጊቶች መፈፀም የአንድን ኅብረተሰብ የግብረገብነት እሴት የማይነካ ድርጊቶቹም በሕዝብ ዘንድ በወንጀልነት በሥፋት የማይታወቁ ከመሆናቸው የተነሳ ሕግ አውጪው የኅብረተሰቡን አጠቃላይ ጥቅም ለመጠበቅ ሲል በወንጀልነት የሚፈርጃቸው በደንብ ተላላፊነት የሚቆጠሩ ወንጀሎች ናቸው።
ከእነዚህ ወንጀሎች መካከል በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 66 ንዑስ አንቀጽ 4፣ 5፣ 8፣ 12፣ 14፣ 19፣ 20፣ 21፣ 22 እና 25 የተመለከቱት ድርጊቶች ተጠቃሽ ናቸው። ምክንያቱም እነዚህ ድርጊቶች የዘመናዊ ኑሮ ውስብስነት ከሚፈጥራቸው ችግሮች የተነሳ አንዳንድ ችግሮች በተናጠል ጉዳት የማያደርሱ ቢሆንም በመደጋገም በአንድ ወይም በብዙ ሰዎች ሲፈጸሙ ግን በኅብረተሰቡ ላይ የከፋ ጉዳትን ሊያስከትሉ ስለሚችሉ እነዚህ ጉዳዮችን ለመደንገግ ቁጥጥር ማድረግ በማስፈለጉ የቁጥጥር ሕጎች በማውጣት የሚደነገጉ የደንብ ተላላፊነት ወንጀሎች ወይም የቁጥጥር ሕግ ወንጀሎች ናቸው። እነዚህ ዓይነት ወንጀሎች በቅጣት መጠንም እንደ ዋና ወንጀሎች በእኩል ዓይን የሚታዩ አይደሉም። በረቂቅ አዋጁ አንቀጽ 66 ንዑስ አንቀጽ 4፣ 5፣ 8፣ 12፣ 14፣ 19፣ 20፣ 21፣ 22 እና 25 የተመለከቱት ድርጊቶች የቅጣት መጠናቸው ሲታይ በዋና ወንጀል ደረጃነት የተቀመጡ ቢመስሉም የወንጀል ድርጊቶቹ አቀራረጽ ግን የደንብ ተላላፊነት ሕግ ቅርፅ የያዘ በመሆኑ በአግባቡ ሊፈተሽ ይገባቸዋል።
ማጠቃለያ
ስለ ምግብ እና መድኃኒት አስተዳደር በሚል የተዘጋጀውና በሥራ ላይ ያለውን አዋጅ ቁጥር 661/2002 የሚለውጠው አዲሱ አዋጅ በቀድሞው አዋጅ ላይ ሲታዩ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት እና አዋጁም ከወጣ በኋላ በአፈፃፀም ደረጃ ሲታዩ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት የቀረበው ረቂቁ አዋጅ በተነፃፃሪነት የተሻሉ ድንጋጌዎች ይዞ የመጣ እና የኅብረተሰብ ጤናንና ደኅንነት ለመጠበቅ እና ለማስጠበቅ ቁጥጥር የሚያስፈልጋቸው ምርቶችንና ተግባሮችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ይሆናል። ረቂቅ አዋጁ ከሥያሜ ጀምሮ የአቀራረጽ እና የይዘት ችግሮች የሚስተዋልበት በተለይም በአስተዳደር እና በወንጀል ቅጣቶች ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች በደንብ በጥልቀት መፈተሽ ያለበት ስለሆነ ረቂቅ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት መስተካከል ያለባቸውን ድንጋጌዎች ሊፈትሽ ይገባል።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here