በነገሌ ምርጫ ክልል ለህዝብ ተወካዮች እና ለክልል ምክር ቤቶች የሚወዳደሩ ዕጩዎች ምርጫ ዛሬ ጠዋት ከ12 ሰዓት ጀምሮ እየተካሄደ ይገኛል።
የነገሌ ምርጫ ክልል ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ አማኑኤል ብርሃኑ ከ150 በላይ ታዛቢዎችና የምርጫ አስፈጻሚዎች መመደባቸውን ገልጸዋል።
ዛሬ ጠዋት በተጀመረው የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ የኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነትን ለመከላከል ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
በነገሌ ምርጫ ክልል ለሁለቱም ምክር ቤቶች ሁለት በግል፣ አንድ ከኢዜማ እንዲሁም አራት ከብልጽግና ፓርቲ ዕጩዎች ለውድድር መቅረባቸው ተመላክቷል።
ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ሊካሄድ የነበረው ምርጫ አንድ የግል እጩ ተወዳዳሪ ባቀረቡት ቅሬታ በብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ እንዲቋረጥ መደረጉን የነገሌ ምርጫ ክልል ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ አማኑኤል ብርሃኑ አስታውሰዋል።
በምርጫ ክልሉ ስር ከሚገኙ 139 ምርጫ ጣቢያዎች መካከል ድምጽ ያለተሰጠባቸው 30 የምርጫ ጣቢያዎች ቦርዱ ሐምሌ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ድምጽ እንዲሰጥ በወሰነው መሰረት እየተካሄደ መሆኑን አስታውቀዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል።




