“የአብዛኞቻችን ምኞት እውነት ከእኛ ጋር እንድትቆም እንጂ፥ እኛ ከእውነት ጎን እንድንቆም አይደለም”

0
901

ብርሃኑ ሰሙ የስኬታማው ነጋዴ ወልደሔር ይዘንጋውን “ፍኖተ ሕይወት” የተሰኘ ግለ ታሪክ መጽሐፍ እንብበው፣ ጠቃሚ ናቸዉ የሚሏቸውን የመጽሐፉን ይዘቶች እነሆ ቅምሻ ይሉናል። እግረ መንገዳቸውንም ከዚህ በፊት በንግዱ ዓለም ውስጥ የነበሩ ሰዎች ገድል እና ግለ ታሪክን የያዙ መጻሕፍትንም ለአንባብያን ይጠቁማሉ።

 

 

“አባቴ፣ በእኔ መሉ እምነቱን ጥሎ የተለያዩ ሥራዎችን በኃላፊነት እንድመራ ከአደራ ጋር አስረክቦኛል። እኔስ በዚህ ዕድሜዬ ይህን አደራ የማስረክበው ትውልድ አገኛለሁ? የዕውቀትና የልምድ ሽግግሩን ከእኛ ለመቀበል የተዘጋጀ ትውልድ አለ? በዘመነ ሉላዊነት ለትውልዱ የምንቀርበው እኛ ወይስ አውሮፓና አሜሪካ? በአገራችን በጎ ሥልጣኔ ሊዳብር የሚችለው መሠረቱን የእኛን ነባር ባሕል፣ ወይስ የአውሮፓን ቢያደርግ ነው? እነ ጃፓን በሥልጣኔ መጥቀው የወጡት፣ በቱባ ባሕላቸው ላይ ዘመናዊ ሥልጣኔን ስለጫኑበት አይደለም ወይ? የዚህች አጭር ግለ ታሪክ መጽሐፌም ዐቢይ ተልዕኮ እኔ ያለፍኩበትን ውስብስብ የሕይወትና የሥራ ልምድ ወደ ትውልዱ ከማሸጋገር በተጨማሪ፣ ትውልዱ ከላይ የሰነዘርኳቸውን ጥያቄዎች እንዲያስተውላቸው ጭምር ነው።”
“ፍኖተ ሕይወት” የወልደሔር ይዘንጋውን ሥራና ልምድ የሚያስቃኝ ግለ ታሪክ መጽሐፍ ነው። በ2010 ለአንባብያን የቀረበው ይህ ጥራዝ፣ የአገራችንን ባለሀብቶች ታሪክ ማዕከል አድርገው የታተሙትን መጻሕፍት ቁጥር በአንድ አሳድጓል። እኔ ባለኝ መረጃ መሠረት ንግድና ነጋዴን ማዕከል ያደረጉ፣ በባለታሪኮቹ የተጻፉና በሌሎች ጸሐፍያን የተሰናዱ 10 ያህል የሕይወት ታሪክ መጻሕፍት አሉ።
እነዚህም የቀኛዝማች ከድር ኤባ “ቀኛዝማች ከድር ኤባ አባያኢ ከ1920-1987”፣ የበላይ ተክሉ “ሀገር መውደድ”፣ (ከታተመ በኋላ ባይሠራጭም) የዘሙ ተክሉ የሕይወትና የሥራ ታሪክ መጽሐፍም አለ፣ የአስፋው ተፈራ “እኔ ማነኝ?”፣ የተስፋ ገብረሥላሴ “ዘመን ተሻጋሪ ባለውለታ” (በወሰን ደበበ የተሰናኘ)፣ የሺበሺ ለማ “በቀለ ሞላ የትጋት አርዓያ”፣ በደመቀ ብርሃነ ተፈራ ተዘጋጅቶ የቀረበው “ሕልመኛው ባለሀብት”፣ የፀጋ አሳመረ “በፈተናና በጥረት የታጀበ ስኬት”፣ ጌታቸው ተድላ(ዶ/ር) የተጻፈው “ተድላ አበበ የዘመናዊ እርሻ ፋና ወጊ”፣ ባለታሪኩ አዘጋጅተውት በበቀለ አበባው የአርትዖት ሥራ የተሰናኘው የፊታውራሪ አመዴ ለማ “የሕይወት ታሪኬ”፣ የሮቤርቶ ያኮና “ሥራ” መጽሐፍ ተጠቃሽ ናቸው።
የኢትዮጵያ የባለሀብቶችን የሕይወት ታሪክ መጻሕፍት ቁጥር በአንድ ያሳደገው “ፍኖተ ሕይወት” ከምንም ተነስተው ያሰቡበትና የተመኙት ላይ መድረስ የቻሉት የአቶ ወልደሔር ይዘንጋውን የሕይወት ውጣ ውረድ፣ የኑሮ ዝቅና ከፍታ፣ ሰዋዊ ሥጋትና ተስፋን… በስፋት ያስቃኛል። እንደማንኛውም ገጠር ተወልዶ እንዳደገ ልጅ በእረኝነት፣ በቆሎ ተማሪነት፣ ቤተሰብን በተለያዩ ሥራዎች በመርዳት… ውስጥ አልፈዋል።
ለንግድ ሥራ የተፈጠረ መክሊት እንዳላቸው በግላቸውም፣ በሌሎችም ዘንድ ከታወቀ በኋላ በርካታ ሊባሉ የሚችሉ ትናንሽ የንግድ ሥዎችን ሞክረዋል። ሲራራ ነጋዴነት አልፈውበታል። ቼንች መንዝረዋል። የጦር መሣሪያ ንግድ ላይ ተሳትፈዋል። ከአፋሩ ሡልጣን ዓሊ ሚራህ ጋር በጋራ ነግደዋል። የደርግ ዕዝ ኢኮኖሚ የፈጠረው የሸቀጣ ሸቀጥ እጥረትን እንደ ዕድል ተጠቅመው የንግድ ሥራቸውን ለማሳደግ ተጠቅመውበታል። ኮንትሮባንድም እነግድ ነበር የሚሉት በግልጽነት ነው። ግልጽነትን በተመለከተ በመጽሐፉ ገጽ 301 የሚከተለውን ሐሳብ አስፍረዋል፦
“በዚህ አጭር ግለ ታሪክ ላይ አሁን ላለውና ለመጭው ትውልድ ማስተላለፍ የፈለግሁት፣ ግዮን ኢንዱስትሪያልና ኮመርሻል ኩባንያ እስከ ተመሠረተ ድረስ ስለነበረው ሁኔታና ስላደረግነው አስቸጋሪና ውስብስብ የዕድገት ጉዞ ነው። በዚህ ረገድ ይኸኛው ያሳፍራል፣ ያኛው ደግሞ ያስደስታል፣ ሳልል ሁሉንም በታሪክነቱ፣ በቅደም ተከተል አስቀምጫለሁ። ያለፍኩበት መንገድ ስለሆነ ዝቅ ባለው አላፍርበትም፣ ከፍ ባለውም አልገበዝበትም፣ አንዱ መነሻ፣ ሌላው ደግሞ መድረሻ ሆነው የዛሬውን ማንነቴን የፈጠሩ ናቸውና!” ይላሉ።
አተርፋለሁ ብለው የከሰሩባቸው ገጠመኞች ብዙ ናቸው። በደርግ ዘመን ጨው ወደ ኬንያ መላክ አትራፊ ሥራ ነበር። አቶ ወልደሔር ይዘንጋው በዚህ የሥራ ዘርፍ ለመሠማራት በማዕድን ሚኒስቴር በኩል ውል ፈፅመው፣ ግማሽ ክፍያ ከፍለው፣ ጨውን ከኤርትራ ለማስጫን ሲዘጋጁ ምፅዋ በሻቢያ በመያዙ ምክንያት ለኪሳራ ተዳርገዋል።
ባመኗቸው ሰዎች የተካዱበት በርካታ ታሪክና ገጠመኞችም አሏቸው። አስገራሚው ነገር የተካዱትን ለማስመለስ፣ ሕጋዊ አካሔዱ አላዋጣ ሲላቸው በግላቸው ክትትል አድርገው፣ ወልደሔር ይዘንጋው ለድርድር መታገድ የሚገባው ሰው ነው የሚሉትን አግተው፣ ለእገታው የጦር መሣሪያ አገልግሎት ላይ አውለው፣ የተከራዩት የአልቤርጎ ክፍል እንደ እስር ቤት ተጠቅመው ያገቱትን ሰው በማሰር… መብታቸውን ማስከበራቸውን በዚህ መልኩ ምስክርነታቸውን በመጽሐፉ አስፍረዋል፦
“አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው፣ በዚያች ቀን በደረሰብኝ መታለል የተሰማኝ ብስጭት ከባድ ነበር። በተለይ ገንዘቤን ለማስመለስ ከጧት እስከ ማታ በእልህ ያደረግሁት ሩጫ ቀላል አልነበረም። በመጨረሻም በዚያች ዕለት ገንዘቤን እንዴት እንደተቀበልሁ ዘወር ብዬ ሳስበው በእጅጉ ይገርመኛል። ይህም ሥራዬ እሥራኤላውያን ኡጋንዳ ላይ የታገቱ ዜጎቻቸውን ለማስለቀቅ ያደረጉትን ተጋድሎ የሚያሳየውን ‘ዘጠና ደቂቃ በእንቴቢ’ የተሰኘውን ፊልም ያስታውሰኛል።”
እንዲህ ዓይነት ያልተለመደ ግልጽነት በስፋት የሚታይበት የአቶ ወልደሔር ይዘንጋው “ፍኖተ ሕይወት” ግለ ሕይወት ታሪክ መጽሐፍ፣ አንባብያንን የሚያስተምሩ፣ የሚያዝናኑ፣ የሚያስደምሙ፣ የሚያወያዩ… በርካታ መረጃዎች ቀርበውበታል። ከአቶ ወልደሔር ይዘንጋው ሥራዎች ጋር በተያያዘ መጽሐፉ ለአንባብያን ካኖራቸው መረጃዎች አንዱ የጧፍ ፍጆታን የሚመለከት ነው። በ220 አብያተ ክርስቲያናት በየዕለቱ የሚበራዉ ጧፍ ብዛት 2227 ኪሎ ግራም እንደሚደርስ በጥናት ደርሰውበታል። ይህ ለጥናትና ምርምር አድራጊዎች ቀላል የሚባል መረጃ አይደለም። መረጃው ባለታሪኩን “ግዮን ጋዝ” ፋብሪካን እንዲያቋቁሙ ምክንያት ሆኗቸዋል።
“የዕድል ፈጣሪ ምንጊዜም የግለሰብ ጥረትና ትጋት ነው። ያለጥረት የሚመጣ ዕድል ዘለቄታ የለውም። በመልካም ሥራቸውና በታታሪነታቸው ያገኙትን ዕድል የማይጠቀሙ ሰዎች ከፊት ለፊታቸው የሚጠብቃቸው ውድቀት ነው” የሚል አቋምና መረዳት ያላቸው አቶ ወልደሔር ይዘንጋው ከኑሮና ከሕይወት ልምድ በመነሳት የደረሱባቸው የሚመስሉ፣ ጠንካራና ለጥቅስ የሚበቁ አባባሎችን በመጽሐፋቸው አኑረዋል፦
“በዓለማችን ሐሰት የሚያከናውነውን ያህል፣ እውነት አይፈፅመውም”፤ “የአብዛኞቻችን ምኞት እውነት ከእኛ ጋር እንድትቆም እንጂ፥ እኛ ከእውነት ጎን መቆምን አይደለም”፤ “በዕድሜዬ ደስታን ወደ ቤቴ የማያመጣ ሀብት ተመኝቼ አላውቅም”፤ “እግዚአብሔር የገደለው የለም፣ እግዚአብሔር ገደለኝ የሚልም የለም። በገጠር በሽታና እርጅና፣ በከተማ ደግሞ ካንሰር፣ ልብ ድካም፣ ስኳር ወዘተ… ገደለው ይባላል”፤ “የስኬት ምሥጢሩ መከራ ነው። ስኬት ከብዙ መከራ ይወለዳል። ሳይሰለቹ መሞከር ውጤትን የሚያቀዳጅ ይመስለኛል።”
በመጽሐፉ የምስጋና ገጽ ላይ ሥማቸው የተነሳው አንጋፋ ሰዎች የወልደሔር ይዘንጋው ግለ ታሪክ መጽሐፍ ከመታተሙ በፊት ባነበቡበት ወቅት (ጥራዙ ርዕስ ተሰጥቶት ከነበር) የርዕስን ድግግሞሽ ማስቀረት ቢችሉ ጥሩ ነበር። አንጋፋው ደራሲና ተርጓሚ ሣህለሥላሴ ብርሃነማርያም በ2000 ያሳተሙት ግለ ሕይወት ታሪክ መጽሐፍ “ፍኖተ ሕይወት” በሚል ነበር የታተመው።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here