ዩኒቨርሲቲው በተማሪዎች ‹‹የማይሆን›› ጥያቄ ትምህርቴ እየተቋረጠ ነው አለ

0
681

አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በሚጠይቁት የማይሆን ጥያቄና አገሪቱን ያላገናዘበ ፍላጎት የመማር ማስተማሩ ሥራ በዘንድሮው ዓመት ብቻ ለኹለተኛ ጊዜ መቋረጡን በመግለጽ አማረረ።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ለሚ ጉታ (ዶ/ር) ሰሞኑን ለመገናኛ ብዙኃን አውታሮች በሰጡት መግለጫ ተማሪዎቹ በነፍስ ወከፍ ላፕቶፕ ተገዝቶ እንዲሰጣቸው እንዲሁም ከተመረቁ በኃላ ሥራ የመቅጠር ዋስትና እዲገባላቸውና ከ90 እስከ 100 በመቶ የማስተርስ እድል እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ እየጠየቁ መሆኑን ጠቅሰዋል። ጥያቄው ‹‹የማይሆን ነገር ነው›› ያሉት ፕሬዘዳንቱ ይህን ለመፈጸም የአገሪቱም ሆነ የዩኒቨርሲቲው አቅም እንደማይፈቅድ አስገንዝበዋል። ዩኒቨርሲቲው ለዚህ ፍላጎት የያዘው በጀት አለመኖሩንም አስታውቋል።
አዲስ ማለዳ በኅዳር ወር በተመሳሳይ ጥያቄ ትምህርታቸውን አንከታተልም በሚል አቋርጠው በነበሩት የአዲስ አበባ እና የአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጉዳይ በሰራችው ወቅታዊ ዘገባ የተማሪዎቹ ፍላጎት የአገሪቱን አቅም ያላወቀ ነው መባሉን ጠቅሳ ዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎቻቸው ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ስለማስጠንቀቃቸው መዘገቧ ይታወሳል። በዚህም ውይይት ተደርጎ የመማር ማስተማሩ ሒደት ቀጥሎ ነበር ተብሏል።
በታኅሣሥ 25 እና 26/2011 በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ሦስት ተማሪዎቸ ሞተው መገኘታቸው ይታወሳል። ተማሪዎቹም የአስከሬን ምርመራው ውጤት እስኪገለጽላቸው አንማርም በማለት አድመው መሰንበታቸውን የገለጹት ፕሬዘዳንቱ ባለፈው ሳምት መጨረሻ ምርመራው ከቅዱሰ ጳውሎስ ሆስፒታል መጥቶ ከተገለጸላቸው በኋላም ወደትምህርታቸው ሊመለሱ እንዳልቻሉ ተናግረዋል። ይልቁንም ሌሎች ተማሪዎች ለመማር በመፈለግ ወደ ክፍል እንዳይገቡ እየቀሰቀሱና እያስፈራሩ ስለመሆኑም አስረድተዋል። ይሁንና ትዕግሰቴ አልቋል ያለው ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹ ከድርጊታቸው ታቅበው ወደትምህርታቸው የማይመለሱ ከሆነ እርምጃ ለመውሰድ ተዘጋጅቻለሁ ሲል አስጠንቅቋል።
መንግሥት ተማሪዎች የምግብና መኝታ አገልግሎት እያገኙ አድማ በመምታት ትምህርትን ማስተጓጎልም ሆነ ትምህርት አቋርጦ ጥያቄ ይመለስልኝ የሚልን አካሄድ እንደማይቀበልና ሕገ ወጥም ጭምር እንደሆነ ከዚህ ቀደም ሲያስገነዝብ ኖሯል።
የኹለቱ ዩኒቨርሲቲ ታማሪዎች ከዚህ ቀደም አንስተውት በነበረው ጥያቄ የጠየቁት መጀመሪያውኑ ከመግባታቸው በፊት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት የተገባላቸውን ቃል እንደሆነ ሲያነሱ ሚኒስቴሩ ስለሚባለው ቃል እንደማያውቅ መግለጹ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 10 ጥር 11 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here